ማላዊያን የራስተፈሪ እምነት ተከታዮች በድሬድሎክ ት/ቤት እንዲገቡ ተፈቀደላቸው

ፀጉሯን 'ድሬድሎክ' ያደረገች ሴት Image copyright Phil Clarke Hill

ማላዊ፤ ራስተፈሪያን ከነ'ድሬድሎካቸው' ትምህርት ቤት እንዲገቡ ፈቀደች።

የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የራስተፈሪ እምነት ተከታይ ተማሪዎች ከነ'ድሬድሎካቸው' ትምህርት ቤት እንዲማሩ መንግሥት እንዲፈቅድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ጊዜያዊ የሆነው ውሳኔ የተላለፈው፤ ፍርድ ቤቱ የአንዲት ራስተፈሪ እምነት ተከታይ ጉዳይን ተከትሎ ነው።

የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች ፀጉራቸውን በረዥሙ በማሳደግ ይታወቃሉ። ይህ የፀጉር አስተዳደግ ዓይነት 'ድሬድሎክ' በመባል ይታወቃል።

ፍርድ ቤቱ በ'ድሬድሎክ' ምክንያት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመዝገብ የተከለከለችውን ሕፃን ጉዳይ ሲያይ መቆየቱን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ተማሪዋ በትምህርት ቤቱ አስተዳደር 'ድሬድሎኳን' እንድትቆርጥ ተጠይቃ ነበር።

ይህንን የክስ ጉዳይ ሲያዩ የነበሩት ዳኛ ትምህርት ቤቱ ተማሪዋን እንዲቀበልና ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ያለፋትን ትምህርትም ተጨማሪ ጊዜ በማስተማር እንዲያካክሱ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

ታዲያ ፍርድ ቤቱ 'ድሬድሎክ'ን አስመልክቶ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ትዕዛዝ በማላዊ የሚገኙ ዳኞች ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የማላዊ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ፀጉራቸውን 'ድሬድሎክ' ያደረጉ ሁሉም የራስተፈሪ እምነት ተከታይ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መግባት እንዲችሉ መንግሥትን ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

የማህበሩ ፕሬዚደንት ታዳላ ችንክዌዙሌ በመግለጫቸው የትምህርት ሚንስትር ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ለመተግበር መመሪያ ያወጣል? የሚለው በጣም አሳሳቢ ነበር ብለዋል።

"ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ራስ ተፈሪያን ህፃናት በራሳቸው የመኩራት መብት፣ የመማር መብት እና ሃይማኖት በፖሊሲ ተፅዕኖ ሊደረግበት እንዳይገባ ከግምት ውስጥ በማስገባቱ በውሳኔው በጣም ደስተኞች ነን" ሲሉ የተሰማቸውን ገልፀዋል።

ፀጉሯን 'ድሬድሎክ' ማድረጓን ተከትሎ ከትምህርት ቤት የተከለከለችው ተማሪ ጉዳይ ማህበሩ በወካይነት እየተከራከረ ነው።

ፍርድ ቤቱም ጊዜያዊ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን የተማሪዋ የክስ ሂደት እስከሚጠናቀቅ እና የመጨረሻ ብይን እስከሚሰጥ ድረስ ተግባራዊ ይሆናል።

ከዚህ ቀደም ኔሽን ጋዜጣ በማላዊ የሚገኙ የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች በሚደርስባቸው መገለል መንግሥትን እንደሚከሱ ዘግቧል።

በፈረንጆቹ ኅዳር 2018 'ድሬድሎክ' ምክንያት ትምህርት ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎም የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው ነበር።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ