ሂዩማን ራይትስ ዎች፡ ግማሽ ሚሊዮን ኤርትራዊያን ብሔራዊ ውትድርናን በመሸሸ ተሰደዋል

የኤርትራ ወጣቶች በማዕድን ሥራ ላይ
አጭር የምስል መግለጫ የኤርትራ ወጣቶች በማዕድን ሥራ ላይ

ኤርትራ አሁንም በርካታ ወጣቶች የሚሰደዱባት አገር መሆኑኗን የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

የተቋሙ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ኤርትራዊያን ሁለት ምክንያቶች የስደት ጉዟቸውን እንዳያበቃ አድርጎባቸዋል።

አንደኛው በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት የሚደርሰው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መጨረሻው የማይታወቀው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ናቸው።

ኤርትራ፡"እያስተማሩን ሳይሆን ባሪያ እያደረጉን ነው"

የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ሲታወስ

በአገሪቱ ሕግ መሠረት ለብሔራዊ አገልግሎት ወጣቶች የሚመለመሉት እድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላቸው ነው፤ ነገር ግን በተለይ በከተማ አካባቢ ከዚያም በፊት ታደጊዎች እየታደኑ ወደ ውትድርና ይላካሉ ብሏል- የ2020 የዓለምን ሪፖርት ያጠናቀረው ሂዩማን ራይትስ ዎች።

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ኮሚሽንን ዋቢ በማድረግ ባስቀመጠው መረጃ መሰረት፤ 507 ሺህ 3 መቶ ኤርትራዊያን ከፈረንጆቹ 1993 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። ይህም የአገሪቱን 10 በመቶ የሕዝብ ብዛት ይሸፍናል።

በተለይ ፍላጎት የለኝም ወይም ብሔራዊ ውትድርናውን አልሳተፍም ማለት የማይፈቀድና ብርቱ ቅጣት የሚያስከትል መሆኑ ደግሞ ወጣቶች አገራቸውን ለቅቀው ለመሰደዳቸው አንደኛው ምክንያት ሆኗል።

ከዚህም በተጨማሪ አብዛኞቹ ወጣቶች በአነስተኛ ክፍያ የመንግሥት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንዲሠሩ የሚደረግ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በውጭ ባለሃብቶች በተያዙ የማዕድን ኩባንያዎች ውስጥ ጉልበታቸውን እንዲያፈሱ ይገደዳሉ።

ኤርትራ አፍሪካ ውስጥ እጅግ የከፋ ጭቆና ካለባቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። በተደጋጋሚ የመንግሥታቱ ድርጅት በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለማየት ያደረገውን ሙከራ በመከልከል አገሪቱ ትታወቃለች ብሏል ሪፖርቱ።

እንቅስቃሴ አልባዋ ምጽዋ

በፈረንጆቹ 1993 ራሷን ችላ እንደ አገር ከተመሠረተች ወዲህ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለ27 ዓመታት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን በብቸኝነት ሲቆናጠጡ፤ ምርጫ የሚባል ነገር ደግሞ በአገረ ኤርትራ ታይቶ አይታወቅም።

ከኢትዮጵያ ጋር በፈረንጆቹ 2018 የሰላም ስምምነት ቢያደርጉም የኤርትራ የብሔራዊ የሽግግር ጉባዔ በፈረንጆቹ 1997 ያጸደቀውን ሕገ መንግሥት መተግበር ግን አልቻለም።

በቅርቡ ኤርትራ በሃይማኖት ተቋማት ባለቤትነት ይተዳደሩ የነበሩ ትምህርት ቤቶችን በግድ ወደ መንግሥት ንብረትነት ያዞረች ሲሆን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እጅ የነበሩ የጤና ተቋማትንም ዘግታለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ