የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ጥር ላይ እንዲካሄድ ተወሰነ

የአፍሪካ ዋንጫ Image copyright Getty Images

ቀጣዩ የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ጥር ወር ላይ እንደሚካሄድ አዘጋጅ ሃገር ካሜሮን አስታወቀች።

የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ይዘጋጅ የነበረው በወርሃ ሰኔ እና ሐምሌ ላይ የነበረ ሲሆን፤ ግን እነዚህ ወራት በካሜሩን ዝናባማ ስለሚሆኑ ወደ ጥር እንዲዘዋወር ተደርጓል ተብሏል።

ይህ ማለት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ እና ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉ ሃገራት ተጫዋቾች እስከ ስድስት የክለብ ጨዋታ ያመልጣቸዋል።

ትናንት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን-ካፍ እና የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ የካፍ ፕሬዝደንት በትዊተር ገጻቸው ላይ "የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ከጥር 1 እስከ ጥር 29 ድረስ ይካሄዳል። የጊዜ ለውጡ በአየር ጠባይ ምክንያት በካሜሮን ጥያቄ መሠረት ተቀይሯል" ሲሉ አስፍረዋል።

የካፍ ምክትል ፕሬዚደንት ቶንይ ባፉኤ በበኩላቸው፤ በቀን ለውጡ ላይ ከካሜሮን ሜትዮሮሎጂ ባለሥልጣናት፣ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ጋር እንዲሁም የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በጥልቅ መወያየታቸውን አስረድተዋል።

ካሜሮን የ2019 ዋንጫን እንድታዘጋጅ ተመርጣ እንደነበረ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ከስታዲየም ግንባታ እና ከአጠቃላይ ዝግጅት ጋር ተያይዞ የነበራት ዝግጁነት ዘገምተኛ ነው ከተባለ በኋላ ነበር ግብጽ እንድታዘጋጅ እድሉ የተሰጣት።

«የኔ ትውልድ ታሪክ እንደሚሠራ እምነት አለኝ» ሎዛ አበራ

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ