20 ወፎችን በቦርሳው የደበቀው አየር ማረፊያ ላይ ተያዘ

20 ወፎችን በቦርሳው የደበቀው አየር ማረፊያ ላይ ተያዘ Image copyright AFP

ቤልጂየማዊ ዜግነት ያለው ተጓዥ በፔሩ ዋና ከተማ በሚገኘው ሊማ አየር ማረፊያ በእጅ ሻንጣው 20 ወፎችን ደብቆ ከሃገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ሂዮጉ ኮኒንግስ የተባለው የ54 ዓመት ጎልማሳ፤ ወፎቹን በትናንሽ ካርቶኖች ውስጥ ካደረገ በኋላ በእጅ ሻንጣው ውስጥ ደብቆ ከሃገር ሊያስወጣ መሞከሩን የሃገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ ጨምሮ እንደተናገረው፤ ግለሰቡ ወፎቹን ወደ ማድሪድ ስፔን ወስዶ ለመሸጥ አስቦ ነበር።

ወፎቹ ጥበቃ የሚደረግላቸው የላቲን አሜሪካ ብርቅዬ አእዋፋት መሆናቸው ተነግሯል።

20ዎቹም ወፎች በሕይወት እንደተገኙ ይሁን እንጂ ለሰዓታት በትንሽዬ ካርቶን ውስጥ መቆየታቸውን ተከትሎ ላባቸው መርገፉን እና ፈሳሽ ከውስጣቸው እንደተመናመነ ምልክት ማሳየታቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ቤልጂየማዊ አእዋፋትን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር በሚል ክስ ተመስርቶበት በፔሩ እስር ቤት 5 ዓመታትን እንዲያሳልፍ ሊፈረድበት ይችላል ተብሏል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ወፎቹ በትናንሽ ካርቶኖች ውስጥ ነበር በዚህ መልክ የታሸጉት።
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ወፎቹ ለሰዓታት በካርቶን ውስጥ መቆየታቸውን ተከትሎ ላባቸው መርገፉን እና ፈሳሽ ከውስጣቸው እንደተመናመነ ምልክት ማሳየታቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ወፎቹ በፔሩ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ እና በኢኳዶር እና ቦሊቪያ ብቻ እንደሚገኙ ተነግሯል።

በፔሩ ብርቅዬ የሆኑ አእዋፋት በብዛት የሚገኙ ሲሆን ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት አዘዋዋሪዎች ግን የፔሩ ብርቅዬ አእዋፋት ላይ የተጋረጡ ከፍተኛ ስጋት ሆነዋል ተብሏል።

ወፎቹ ቀልብን የሚገዛው የላባቸው ቀለማት በአውሮፓ ገበያ ብዙ ገንዘብ ይጠየቅባቸዋል ተብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ