ሆንግ ኮንግ ኤክስፕረስ አየር መንገድ፡ ተሳፋሪዋን የእርግዝና ምርመራ በማስደረጉ ይቅርታ ጠየቀ

ሆንግ ኮንግ ኤክስፕረስ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አየር መንገዱ ለአጋጣሚው ያለምንም ማመንታት ይቅርታ ጠይቋል

የሆንግ ኮንግ ኤክስፕረስ አየር መንገድ ከሆንግ ኮንግ ወደ አሜሪካዋ የፓስፊክ ግዛት ለመብረር የተሰናዳችውን መንገደኛ የእርግዝና ምርመራ እንድታደርግ በማስገደዱ ይቅርታ ጠየቀ።

የ25 ዓመቷ ሚዶሪ ኒሽዳ የሰሜን ማሪያና ደሴቶች አካል ወደ ሆነችው ሳይፓን ደሴት ለመብረር የተሰናዳችው ባሳለፍነው ህዳር ወር ነበር።

አሁን በቶኪዮ የምትኖረው እና በሳይፓ የተወለደችው ኒሽዳ ከበረራዋ ቀደም ብላ በተሰጣት መጠይቅ ላይ ነፍሰ ጡር አለመሆኗን አሳውቃለች።

ይሁን እንጂ አንድ የአየር መንገዱ ሰራተኛ ከበረራዋ በፊት እርግዝናን ጨምሮ ሌሎች ምርመራዎችን እንድታደርግ ያስገድዳታል። ተሳፋሪዋ በሁኔታው ደስተኛ ባትሆንም ወደ መታጠቢያ ቤት እንድትሄድ ተደርጋ በሽንት አማካኝነት በፍጥነት እርግዝናን በሚመረምረው ቁስ የእርግዝና ምርመራ አድርጋለች።

ውጤቱም ነፍሰጡር አለመሆኗን አሳይቷል። ከዚያም ወደ አውሮፕላኑ እንድትሳፈር ተፈቀደላት።

ኒሽዳ አጋጣሚውን "በጣም የሚያዋርድና የሚያበሳጭ" ስትል ገልፀዋልች። አየር መንገዱም ላሰማችው የመጀመሪያ ቅሬታ ምላሽ እንደነፈጋት ተናግራለች።

የውጭ አገር ዜጎች የአሜሪካ ዜግነት ለማግኘት ሲሉ ለመውለድ ወደ ሥፍራው ማቅናታቸው የተለመደ ነው። በመሆኑም አየር መንገዱ ተሳፋሪዎች የአሜሪካ የስደት ሕጎች እንዳይጣሱ ለማድረግ ሲሞክር ነበር ተብሏል።

መንገደኛዋን የእርግዝና ምርመራ እንድታደርግ ማስገደዱም፤ ለመብረር ትችላለች ወይ? የሚለውን ለማወቅ የነበረ ቢሆንም አየር መንገዱ ለተፈጠረው አጋጣሚ ይቅርታ ጠይቋል።

እንደ ግዛቷ መረጃ ከሆነ፤ በፈረንጆቹ 2018 በቁጥር ከነዋሪዎቹ የሚበልጡ የውጭ አገር ዜጎች በሰሜናዊቷ ማሪያና ደሴቶች ወልደዋል።

ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነውም በግዛቷ ለመውለድ ከቻይና የሚሄዱትን ጨምሮ በሌሎች የውጭ ዜጎች ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።


አየር መንገዱ ምን ምላሽ ሰጠ?

አየር መንገዱ ለኤን ቢ ሲ ኒውስ በሰጠው መግለጫ "በዚህ ዓይነት ተመሳሳይ አጋጣሚ የተጎዳችሁ በሙሉ ይቅርታ ልንላችሁ እንፈልጋለን" ብሏል።

አየር መንገዱ በሰሜናዊ ማሪያና ደሴቶች ባለሥልጣናት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ድርጊቱን መፈፀሙን በመጥቀስ፤ "የአሜሪካ የስደት ሕግ አለመጣሱን ለማረጋገጥ ከፈረንጆቹ የካቲት 2019 ጀምሮ ወደ ሳይፓ ደሴት የሚደረጉ በረራዎች ላይ እርምጃዎች ወስደናል " ሲልም ተናግሯል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ