የሶሪያ ጦርነት፡ የማህበረሰብ መሪዎች በበርሊን የምስጢር የሰላም ጉባዔ አካሄዱ

መንግሥት በደማስቆ ላይ የአየር ድብደባ ካደረሰ በኋላ በቦታው ላይ የነበረ የሰዎች ስሜት Image copyright Reuters

በዚህ ሳምንት ጥቂት የሶሪያ የማህበረሰብ መሪዎች በበርሊን በምስጢር ተገናኝተዋል። የተገናኙበት ዓላማ አገራቸውን የደም እምባ እያስነባ ላለው የእርስ በርስ ክፍፍል እልባት ለመስጠት ነው።

በዚህ ጉባኤ ላይ አንዳንዶቹ የራሳቸው ወታደሮች ያሏቸው የሱኒ ጎሳ መሪዎች፤ ከበሽር አላሳድ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው እና ከፍተኛ ኃፊነት ያላቸው ሰዎች ጋር ፊት ለፊት ተቀምጠዋል።

ክርስቲያኖችን፣ ኩርዶችን፣ ዱሩዜ፣ ሱኒ እና አላውቴስን ጨምሮ ከሶሪያ በጣም ወሳኝ ከሆኑ ቤተሰቦች፣ ጎሳዎች እና ማሕበረሰብ የተውጣጡ ወደ 20 የሚጠጉት ቁልፍ ሰዎች፤ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ነበር የተወያዩት።

‘ቤቴን ከ28 ስደተኞች ጋር እጋራለሁ’

በጦርነት የተጎሳቆሉ ስደተኞች መዳረሻቸው የት ነው?

በሶሪያ በበሽር አላሳድ መንግሥትና በታጠቁ ኃይሎች የሚሰራጨውን እርስ እርስ የሚያጋጭ ትርክት ለመዋጋት ወደ ጀርመን በርሊን ያቀኑ ግለሰቦች በሶሪያ ማሕበረሰብ አሉ የሚባሉ መሪዎች ናቸው።

አብዛኞቹ ለሶሪያ መንግሥት ቅርበት ያላቸውና ሙሉ በሙሉ ባይደግፉትም ከደማስቆ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በፕሬዚደንት በሽር አላሳድ አገዛዝ ሥር መከራን የቀመሱ እና ወደ ታጠቀው ተቃዋሚ ኃይል ያልተቀላቀሉ ናቸው።

አንዳንዶቹ ደግሞ ጦርነትን ሸሽተው በስደት ተቀማጭነታቸውን ጀርመን ያደረጉ ናቸው።

"እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የሚያዩት ከታጠቁ ኃይሎችም ሆነ ከመንግሥት ጋር እንዲሁም በአገራቸው ውስጥ ጦርነት ከሚያካሂዱ አካላት ጋር ወገንተኝነት የሌላቸውን 70 በመቶ የሶሪያን ሕዝብ እንደወከሉ ነው።" ሲሉ በመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ ዳንኤል ጌርላች ተናግረዋል። ዳንኤል ጌርላች በጀርመን የሚገኙ ሶሪያዊያንን የሚረዱ እና ይህን ስብሰባ ያስተባበሩ ናቸው።

ጉባዔውን በርሊን ማካሄድ ለምን አስፈለገ?

ስብሰባው በግልና በአውሮፓ መንግሥታት የተደገፈ ሲሆን በበርሊን የመካሄዱ ምክንያት ጀርመን በአንፃራዊ መልኩ ገለልተኛ አገር ሆና በመገኘቷ ነው ተብሏል።

በሶሪያ ጦርነት መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሶሪያዊያን የተሰደዱት ወደ ጀርመን ነበር፤ በመሆኑም ጀርመን አሁን በርካታ ሶሪያዊያን ማሕበረሰብ ያለባት አገር ሆናለች።

በስብሰባው ላይ የነበረው ድባብ አስደሳች ነበር ቢባልም አንዳንድ የስብሰባው ተሳታፊዎች በጉባዔው በመሳተፋቸው ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

በበሽር አላሳድ መንግሥትና በእስላማዊ ታጣቂዎች ዐይን እንደ ክህደትም ሊታይ ይችላል። በቀል ይደርስብናል ከሚለው ስጋት ውጭም አንዳንዶች በምስጢር ወደ በርሊን ያቀኑ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች የእጅ ስልካቸውንም መግቢያው በር ላይ ትተው ወደ ጉባኤው በመግባታቸው ስጋት አድሮባቸዋል።

አቶ ለማ ለምን ዝምታን መረጡ?

"ህክምና የሚጀምረው ከአመኔታ ነው" የ23 ዓመቱ ዶ/ር አቤኔዘር ብርሃኑ

ከኢራቅ ጋር በሚዋሰነው የሶሪያ ድንበር በሚገኘው ሰፊው የሱኒ አረብ ጎሳ መሪ የሆኑት ሼህ አሚር አል ዳንዳል፤ በጦርነቱ ወንድማቸውን አጥተዋል። ታዲያ "በግጭቱ ከተሳተፉ ሰዎች ጋር እንዴት መነጋገር ቻሉ?" ተብለው ተጠይቀው ነበር።

"ሁላችንም ተሸናፊዎች ነን፤ ስለዚህ ቁስላችንን ማከም እንፈልጋለን፤ ይህ ግጭት ይቀጥላል ማለት ሌላ ኪሳራ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አዲስ የገቡት ቃል ምንድን ነው?

በፈረንጆቹ ኅዳር 2017 የዚህ ቡድን መስራቾች መጀመሪያ 'ኮድ ኦፍ ኮንዳክት ፎር ሲሪያን ኮኤግዚስታንስ' የተሰኘ የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። ሰነዱ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦች ሊስማሙበት የሚችሉባቸውን ደንቦች ያካተተ ነበር።

ይህም ያለምንም ብሔርም ሆነ ሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ሁሉም ሶሪያዊያን እኩል መሆናቸውን አካቷል።

ባለፈው ረቡዕ ምሽት ከእልህ አስጨራሽ ክርክር በኋላ፤ በሌሎች የሃይማኖት፣ ቤተሰብ እና ብሔር አባላት በተፈፀመው ወንጀል ማንም ሰው ተጠያቂ እንደማይደረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የዚህ ዓላማም በተወሰነ ቡድን ላይ የበቀል እርምጃን ለማስወገድ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ