በለንደን ማራቶን ቀነኒሳ በቀለና ኪፕቾጌ ተፋጠዋል

ኪፕቼጎ እና ቀነኒሳ Image copyright Getty Images

ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ እና ኬንያዊው ኤልዩድ ኪፕቾጌ ዘንድሮ በሚካሄደው የለንደን ማራቶን ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉ ከወዲሁ ተገምቷል።

ቀነኒሳ የዓለም የማራቶን ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት የያዘ ሲሆነ ኪፕቾጌ ደግሞ በ2 ሰከንድ ልዩነት የዓለምን ክብረ ወሰን በአንደኛነት ተቆናጦታል።

ገና በ21 ዓመቱ በዘጠኝ ቀናት ልዩነት የ 5 ሺ እና 10 ሺ ሜትር ሪከርዶችን የሰባበረው የ37 ዓመቱ ቀነኒሳ ባሳለፍነው መስከረም በርሊን ማራቶንን ሲያሸንፍ የኪፕቾጌን የዓለም ማራቶን ክብረ ወሰን ለመስበር 2 ሰከንዶች ብቻ ነበር የቀሩት።

"ከዚህ በፊት ከኪፕቾጌ ጋር ብዙ ፉክክሮችን አድርገናል፤ ወደፊትም እንደምንወዳደር አስባለሁ። እኔ ጠንካራ አትሌት እንደሆንኩ ሁሉም ሰው ያውቃል፤ በትራክ ላይ 15 ዓመታትን አሳልፌያለው። በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ጤንነት ይሰማኛል" ሲል ስላለበት ሁኔታ ቀነኒሳ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች በመሮጥ የመጀመሪያው አትሌት እንደሆነ ይታወቃል። ኪፕቾጌ ሩጫውን ለመጨረስ አንድ ሰዓት ከ59 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ፈጅቶበታል።

የ34 ዓመቱ ኬኒያዊ አትሌት 42.2 ኪሎ ሜትር ለመሮጥ የፈጀበት ሰዓት እንደ ዓለም ክብረ ወሰን እንደማይመዘገብለት ተገልጧል። ለዚህም ምክንያት ነው የተባለው የተጠቀማቸው አሯሯጮች፤ እየተፈራረቁ የሚያሯሩጡት አትሌቶች መሆናቸውና ለሁሉም ክፍት የሆነ ውድድር ባለመሆኑ ነው።

በውድድሩ ሌላኞቹ ኢትዮጵያውያን ሞስነት ገረመው እና ሙሌ ዋሲሁን ከቀነኒሳ ጎን እንደሚሰለፉ ይጠበቃል። ውድድሩ ሚያዚያ 18/ 2012 ይካሄዳል።

ቀነኒሳ በቀለ እና ኤልዩድ ኪፕቾጌ ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው 20 ውድድሮች በ13ቱ ቀነኒሳ ያሸነፈ ሲሆን ቀሪዎቹን 7 ውድድሮች ኪፕቾጌ አሸንፏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ