የሌሴቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ከቀድሞ ባለቤታቸው ግድያ ጋር በተገናኘ ከሥልጣናቸው ሊለቁ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ Image copyright Reuters

የሌሴቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ ከሥልጣናቸው እንደሚለቅቁ ፓርቲያቸው መግለጹን ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ገዢው ፓርቲ ' ኦል ቦሳቶ ኮንቬንሽን' ቃል አቀባይ የሆኑ አንድ ግለሰብ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ የፊታችን ማክሰኞ ለካቢኔ አባላት የሥራ መልቀቂያቸውን እንደሚያስገቡ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥራቸው የሚለቁበት ምክንያት በይፋ ባይገለጽም፤ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ባለቤታቸው በተገደለችበት አካባቢ ከነበረ ተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር የተደዋወሉበት ማስረጃ እንዳለው በመግለጽ፤ ፖሊስ ለጥያቄ እንደሚፈልጋቸው ማስታወቁ ምክንያቱ እንደሆነ ተገምቷል።

የሌሶቶ ቀዳማዊት እመቤት በፖሊስ እየተፈለጉ ነው

"ዕፀ ፋርስ በመሸጥ ልጆቼን አሳድጋለሁ" የሌሴቶዋ አምራች

ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም ያሉት ነገር የለም።

የሌሶቶ ፖሊስ ከሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የቀድሞ ባለቤት ግድያ ጋር በተያያዘ የአሁኗን ቀዳማዊ እመቤት ለጥያቄ እንደሚፈልጋቸው ቢገልጽም ቀዳማዊት እመቤት ማይሲያህ ታባኔ ግን የት እንደሚገኙ አልታወቀም።

ፖሊስ እንዳለው ቀዳማዊት እመቤት ማይሲያህ ክስ ባይቀርብባቸውም ለጥያቄ ይፈለጋሉ። የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሊፖሌሎ ታባኔ እንቆቅልሽ በሆነ መልኩ መሞታቸው ከተሰማ በኋላ የሃገሬው ዜጎች ሆነ ተብሎ የተሸፋፈነ ጉዳይ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2017 የተገደሉት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ጉዳይን ለማጣራትና የአሁኗ ቀዳማዊት እመቤት የት እንደሚገኙ ለማወቅ የሌሴቶ ፖሊስ የዓለም አቀፍ ሕግ አስከባሪ ተቋማትን እርዳታም ጠይቋል።

እግራቸው አሜሪካ ልባቸው አፍሪካ ያለ የሆሊውድ ተዋንያን

ሟች ቀዳማዊት እመቤት ከባለቤታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ታባኔ ጋር በወቅቱ ተለያይተው የነበረ ቢሆንም ፍቺ ግን አልፈጸሙም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከአሁኗ ቀዳማዊት እመቤት በወቅቱ እጮኛቸው ከነበሩት ማይሲያህ ታባኔ ጋር ግንኙነት መስርተው ነበር።

ሁለቱም ሴቶች እኔ ነኝ ቀዳማዊት እመቤት በሚል ፍርድ ቤት እስከ መካሰስ ደርሰው ነበር።

ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ካጣራ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር ይፋዊ ፍቺ እስካልፈጸሙ ድረስ ሊፖሌሎ ታባኔ ቀዳማዊት እመቤት ሆነው እንዲቀጥሉ ብይን አስተላልፏል።

ተያያዥ ርዕሶች