የትራምፕን የክስ ሂደት በቀላሉ እንዲገነዘቡ የሚረዱ 5 ወሳኝ ጥያቄዎች

(ከግራ ወደ ቀኝ) በሴኔቱ የዲሞክራቶች መሪ ቸክ ሹመር፣ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና በሴኔቱ የሪፓብሊካን መሪ ሚች ማክኮኔል። Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ (ከግራ ወደ ቀኝ) በሴኔቱ የዲሞክራቶች መሪ ቸክ ሹመር፣ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና በሴኔቱ የሪፓብሊካን መሪ ሚች ማክኮኔል።

በአሜሪካ ታሪክ ሶስተኛው ፕሬዝደንት ከስልጣናቸው እንዲነሱ የክስ ሂደት ተጀምሮባቸዋል።

ይህ የክስ ሂደት ፕሬዝደንት ትራምፕን ከስልጣናቸው ከማስወገዱም በተጨማሪ ዘብጥያ እስከመውረድ ሊያደርሳቸው ይችላል።

የትራምፕ ከስልጣን መነሳት (ኢምፒችመት) ችሎት ሂደትን በቀላል እንዲገነዘቡ 5 ወሳኝ ጥያቄዎች ተመልሰዋል።

1)'ኢምፒችመንት' ምንድነው?

'ክስ' የሚለው ቃል ሊተካው ይችላል።

በቀላሉ ስልጣን ላይ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ወንጀል ፈጽመው ከሆነ ተጠያቂ የሚደረጉበት የሕግ ስርዓት ወይም አካሄድ ማለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለዶናልድ ትራምፕ ቅሬታ ምላሽ ሰጡ

እውን ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ተቀስቅሶ እናየው ይሆን? እነሆ ምላሹ

በዚህ ሂደት ፕሬዝደንት ትራምፕ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ኢምፒች" መደረጋቸው ይታወሳል። ይህ ማለት የትራምፕ ጉዳይ ከተወካዮች ምክር ቤት ወደ ሴኔቱ ተላልፏል ማለት ነው።

ትራምፕ በቀረበባቸው ክስ መሠረት ጥፋተኛ ናቸው ወይስ አይደሉም ለሚለው ውሳኔ የሚሰጠው ሴኔቱ ይሆናል።

2) ትራምፕ የቀረበባቸው ክስ ምንድነው?

ትራምፕ በሁለት አንቀጾች ክስ ቀርቦባቸዋል፤ ወይም 'ኢምፒች' ተደርገዋል።

የመጀመሪያው 'ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል' የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 'የምክር ቤቱን ስራ አደናቅፈዋል' የሚል ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2020 ምርጫ የመመረጥ እድላቸውን ለማስፋት በተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ላይ ምረመራ እንዲካሄድ የዩክሬን ፕሬዝደንት ላይ ጫና አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ጆ ባይደን የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ሳሉ ወንድ ልጃቸው በዩክሬን የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነበር። ታዲያ ትራምፕ፤ ተቀናቃኛቸውን ሊያሳጣ የሚችል መረጃ ለማግኘት የዩክሬን ፕሬዝደንት ላይ ጫና በማሳደር ሥልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሁለተኛው ደግሞ ትራምፕ ለሚደረግባቸው ምርመራ መረጃዎችን ለመስጠት ተባባሪ ባለመሆናቸው የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ በሚለው ክስ ላይ ድምጽ ሰጥተዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን የቀረቡባቸውን ክሰቦች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋሉ።

3) ሴኔቱ ምን ይጠበቃል?

በሴኔቱ የችሎቱን ወይም የክሱን አካሄድ የሚወስኑ ሁለት ቁልፍ የሴኔቱ አባላት አሉ። በሴኔቱ የሪፓብሊካን መሪ የሆኑት ሚች ማክኮኔል እና የዲሞክራት መሪው ቸክ ሹመር ናቸው።

ሁለቱ መሪዎች ማስረጃዎች ለሴኔቱ በምን አይነት መልኩ ይቀርባሉ? የምስክሮች እማኘነትስ እንዴት ይስማሉ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ቀድመው መስማማት አለባቸው።

ትራምፕ ጥፋተኛ ናቸው ለማለት እና ከስልጣን ለማስነሳት የሴኔቱ 2/3 ድምጽ ያስፈልጋል። ይህ ማለት ከ100 የሴኔት መቀመጫ 67ቱ ትራምፕ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል።

የትራምፕ አጋር የሆኑት ሪፓብሊካኖች በሴኔቱ አብላጫ የሆነ 53 መቀመጫ አላቸው።

የትራምፕ ተቀናቃኝ የሆኑት ዲሞክራቶች በሴኔቱ ያላቸው መቀመጫ 47 ብቻ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ትራምፕ ላይ የተነሳው ክስ ውድቅ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ገምተዋል።

ከተገመተው ውጪ ሆኖ ትራምፕ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ፤ ከስልጣን ይባረራሉ፤ ከዚያም ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ መንበረ ስልጣኑን ይረከባሉ።

በዚህ ብቻ ሳይወሰን፤ የትራምፕ ጉዳይ በወንጀል ሕግ ታይቶ ከስልጣን በኋላ ዘብጥያ ሊወርዱም ይችላሉ።

4) ትራምፕ በሴኔቱ ፊት ቀርበው መከላከያቸውን ያቀርቡ ይሆን?

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሴኔቱ ፊት ቀርበው መከላከያዎቻቸውን ማቀረብ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ጠበቆቻቸው እንጂ እሳቸው ከሴኔት ፊት ይቀርባሉ ተብሎ አይገመትም።

ዶናልድ ትራምፕን ከዝነኛው ፊልም ማን ቆርጦ ጣላቸው?

ዶናልድ ትራምፕ በመከሰስ ሶስተኛ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆኑ

ትራምፕ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሴኔቱ ፊት ቀርበው እንዲመሰክሩላቸው አጥብቀው ይሻሉ። ዲሞክራቶች በበኩላቸው፤ የቀድሞ የብሔራዊ ደህንነት ኃላፊ ጆህን ቦልተን ጨምሮ ከፍተኛ የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይፈልጋሉ።

5) የዚህ ጉዳይ ማብቂያ መ ይሆን?

ማንም በእርግጠኝነት መናገር ባይችልም የክስ ሂደቱ ለሳምንታት ሊዘልቅ ይችላል። የቢን ክሊንተን የክስ ሂደት አራት ሳምንታት ወስዷል።

ዲሞክራቶች በተቻለ መጠን የክስ ሂደቱ እንዲጠናቀቅ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም በ2020 ምርጫ ዲሞክራቶችን ወክሎ የሚወዳደረውን እጩ መምረጥ ይፈልጋሉና።