ሴቶች የኮረንቲ ገመድ እንዲጨብጡ ያደረገው ጀርመናዊ ሃሰተኛ ዶክተር ተፈረደበት

ሴቶች የኮረንቲ ገመድ እንዲጨብጡ የሚያደርገው ሃሰተኛው ዶክተር ተፈረደበት Image copyright Getty Images

ጀርመናዊው የዶክተር ለምድ የለበሰ ግለሰብ ወሲባዊ ፍላጎቱን ለሟሟላት ሲል ሴቶች የኮረንቲ ገመድ እንዲጨብጡ በማድረጉ 11 ዓመት ተፈረደበት።

ዴቪድ በመባል የሚታወቀው የ30 ዓመቱ ግለሰብ ለሴቶች ብር እየከፈለ የስቃይ ማስታገሻ አለኝ በማለት አታሏል፤ ይህንን ያደረገው ደግሞ ወሲባዊ ፍላጎቱን ለሟሟላት ነው ተብሏል።

ግለሰቡ ተጠቂዎች ቤቱ ውስጥ ያለ የኮረንቲ ገመድ ሲጨብጡ ስካይፒ በተባለው የቪድዮ መደዋወያ ተመልክቷል እንዲሁም ቀርጿል።

የጀርመኗ ከተማ ሚዩኒክ የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ዴቪድ በ13 የግድያ ሙከራዎች ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሎ ነው ፍርድ የበየነው።

አቃቤ ሕግ፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምሩቁ ወንጀለኛ፤ ዶክተር ነኝ በማለት በይነ-መረብ ላይ ያገኛቸውን ሰዎች ለሳይንሳዊ ጥናት እንደሚፈልጋቸው አስመስሎ ኮረንቲ እንዲጨብጡ አድርጓል ይላል።

ግለሰቡ ሴቶችን በበይነ-መረብ ከመለመለ በኋላ በሳይንሳዊ ጥናቱ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ከሆኑ 3325 ዶላር [106 ሺህ ብር] እየከፈለ እንደሚያታልል ተደርሶበታል።

ተጠቂዎቹ ብረት ነክ ዕቃዎችን ከኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጋር እያገናኙ ሲሰቃዩ በስካይፒ ተመልክቷል። ከጠቂዎቹ መካከል አንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ ትገኝበታለችም ብሏል አቃቤ ሕግ።

ዳኛ ቶማስ ቦት፤ ዴቪድ የተሰኘው ግለሰብ ተጠቂዎቹ ብረት ከኮረንቲ እንዲያገናኙ አድርጓል፤ ይህ ማለት ደግሞ ሰዎችን በኤሌክትሪክ ማሰቃየት ነው ብለዋል ብሎ የዘገበው የጀርመኑ ዶች ቬሌ ጋዜጣ ነው።

አቃቤ ሕግ ግለሰቡ ወሲባዊ ፍላጎቱን ለማርካት ነው ይህንን ወንጀል የከወነው ሲል ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ፤ ፍርደ ቤቱም ግለሰቡ ለ11 ዓመታት ከርቸሌ ይውረድ ሲል በይኗል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ