ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ፡ ዩሮቢክ ባንክ ከአንጎላዋ ቢሊየን ጋር ያለውን ግንኙነት አቋረጠ

ቢሊየነሯ ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ በአፍሪካ ቱጃሯ ሴት ናት Image copyright Getty Images

የፖርቹጋል ባንክ ዩሮቢክ ከአፍሪካዋ ቱጃር ሴት ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት እንደሚያቋርጥ አስታወቀ።

የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ልጅ ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ በመሬት፣ በአልማዝ፣ በነዳጅ ዘይት ዘርፍ በመሰማራት የመንግሥትን እጅ በመጠምዘዝ ከድሃ አንጎላዊያን ጉሮሮ እየነጠቀች ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንዳካበተች ይነገራል።

በተለይ አባቷ በመንግሥት ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የኢንቨስትመንት አማራጮች ለእርሷ ብቻ ተብለው የሚከፈቱና የሚዘጉ ነበሩም ይባላል። ሰሞኑን ይፋ እንደሆነ በሚነገረው መረጃ በእነዚህ ሥራዎች እንዴት ለእርሷና ባለቤቷ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸው እንደነበሩና ለመንግሥት መክፈል የነበረባቸውን ገንዘብ እንዴት እንዳልከፈሉ ያሳያል።

'የአፍሪካ ሃብታሟ ሴት' ንብረት በቁጥጥር ሥር እንዲውል ታዘዘ

አገሯን 'በሙስና ያራቆተችው' የአፍሪካ ሃብታሟ ሴት

ታዲያ ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በቢሊየነሯ የተከናወኑ በርካታ አጠያያቂ የሆኑ ጉዳዮች በቢቢሲ እና አጋር ድርጅቶች በተሠራ ምርመራ ከተጋለጠ በኋላ ነው።

ባሳለፍነው ሰኞ የባንኩ የቦርድ አባላት ባደረጉት ስብሰባ ከአክሲዮን ባለድርሻዋ ኢሳቤል ድርጅቶች እና ከዚህ ጋር በቅርበት ግንኙነት ካላቸው ሰዎች ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰኑን አስታውቋል።

ኢሳቤላ ያስተላለፈቻቸው በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች ላይ ምርመራ እንደሚካሄድም ባንኩ አክሏል።

ቱጃሯ ግን የቀረበባትን ክስ ሙሉ በሙሉ ሀሰት ነው ብላለች።

የግለሰቧ የቢዝነስ ትስስር ከአንጎላ የመንግሥት ነዳጅ ዘይት ካምፓኒ ሶናንጎል እስከ ግዙፉ የሞባይል ስልክ አቅራቢ ድርጅት የሚደርስ ነው።

ኢሳቤል፤ በሁለት ድርጅቶቿ ስም በባንኩ 42.5 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ያላት ሲሆን፤ ይህም የባንኩ ከፍተኛ የአክሲዮን ባለድርሻ እንድትሆን አድርጓታል።

ኢሳቤላ በአውሮፓዊያኑ 2017 አባቷ ጡረታ ሲወጡ በአንጎላ የመንግሥት ነዳጅ ዘይት ካምፓኒ ኃላፊ ሆና ለሁለት ወራት ከሠራች በኋላ ተባርራለች።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አፈትልከው የወጡት መረጃዎች እንዳመለከቱትም ኢሳቤል በሶናንጎል የነዳጅ ዘይት ድርጅትን ስትለቅ 58 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ክፍያ ፈቅዳ ነበር።

የተላለፈው ገንዘብም በዩሮቢክ ያለውን የሶናንጎል የገንዘብ ማጠራቀሚያ አካውንት አራቁቶት እንደነበር ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

ማሽተት አለመቻል ምን ይመስላል?

ባለፈው እሁድ አፈትልከው በወጡ መረጃዎች፤ አባቷ በሥልጣን በነበሩበት ጊዜ በመሬት፣ በአልማዝ፣ ነዳጅ ዘይት እና በቴሌኮም ዘርፎች ለመሳተፍ እድሉን እንዴት እንዳገኘች ሊገለጥ ችሏል።

መረጃው የአፍሪካ ቱጃሯ ሴት የገዛ አገሯን በመመዝበርና በሙስና 2 ቢሊየን የሚጠጋ ሀብቷን እንዴት እንዳከማቸች ለማሳየት ሞክሯል።

የአንጎላ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባለሃብቷ ወደ አንጎላ ተመልሳ ለቀረበባት ክስ መልስ እንድትሰጥ እንደሚፈልጉ ገልፀው፤ እርሷን ወደ አገሯ ለመመለስም የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

ኢሳቤል ግን የቀረበባት ክስ በሙሉ ሀሰት አንደሆነና በፖለቲካ ምከንያት በአንጎላ መንግሥት እየተፈለገች እንደሆነ ትናግራለች።

ቢሆንም በሙስና ቅሌት በአንጎላ ባለሥልጣናት የወንጀል ምርመራ ሥር ስትሆን ያላት ሃብቷም እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል።

ኢሳቤል ከዚህ ቀደም ለደህንነቷ ስለምትሰጋ ወደ አንጎላ ተመልሳ እንደማትሄድ አስታውቃ ነበር።

ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ ማን ናት?

  • የቀድሞ የአንጎላ ፕሬዚደንት ጆሰ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ታላቅ ልጅ ናት፤
  • ከኮንጓዊው ነጋዴ ሲነዲካ ዶኮሎ ጋር ትዳር መስርታለች፤
  • አሁን በምትኖርበት ዩናይትድ ኪንግደም ትምህርቷን ተከታትላለች፤
  • 2 ቢሊየን ዶላር ሃብት ያስመዘገበች የአፍሪካ ቱጃር ሴት ሆናለች፤
  • በአብዛኛው በአንጎላና ፖርቹጋል የሚገኙ በነዳጅ፣ በስልክ ኩባንያዎችና ባንክ የአክሲዮን ባለድርሻ አላት።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ