በትራምፕ የድጋፍ ደብዳቤ ወደ አሜሪካ ያቀናችው የአሲድ ጥቃት የደረሰባት ኢትዮጵያዊት

አፀደ ንጉስ ከአሲድ ጥቃቱ በፊትና በኋላ Image copyright MENBERE AKLILU FB

በአዲግራት ከተማ ተወልዳ ያደገችው አጸደ ንጉሥ 2ኛ ደረጃ ትምርቷን በያለም ብርሃን፤ የመሰናዶ ትምህርቷን ደግሞ በአግአዚ ትምህርት ቤት ተከታትላለች።

አልገፋችበትም እንጂ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃትን ነጥብ አምጥታ ሐዋሳ ዩኒቨርስቲም የዲግሪ ትምህርቷን መከታተል ጀምራ ነበር።

ይሁን እንጅ ከሁለት ዓመት በፊት በገዛ ባለቤቷ የተፈጸመባት አሰቃቂ ጥቃት የሕይወቷን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ለውጦታል።

"እናቴ ብቻዋን ነው ያሳደገችኝ፤ አባቴ ታጋይ ነበር፤ ወደ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የወሰደኝ ኑሮን ለማሸነፍ በሚል ነበር። በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ በሚሠራ አንድ ሕንጻ ውስጥ ሥራ አገኘሁ።" ትላለች።

የደረሰባቸውን ጥቃት በመንገድ ላይ የሚጽፉት የኬንያ ሴቶች

የመደፈሬን ታሪክ ከስልሳ ሰባት ዓመታት በኋላ የተናገርኩበት ምክንያት

አጸደ በዚያ ጊዜ ነበር ሕይወቷን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ያደረገውን ባለቤቷን የተዋወቀችው።

"እሱ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ነበር። በዚያ ወቅት ደግሞ በጅግጅጋ ፖሊስ የፈለገውን ነበር የሚያደርገው፤ ስለዚህ በጣም እፈራው ነበር" ትላለች ጊዜውን ስታስታውስ።

የትዳር ጥያቄውን የተቀበለችው ወዳና ፈቅዳ ሳይሆን በፍርሃት እንደነበረ ታስረዳለች።

የተወሰነ ጊዜ ጅግጅጋ ከቆዩ በኋላ ወደ ጋምቤላ እንደሚሄዱ ነገራት።

በጋምቤላ ከተማ እሱ ባጃጅ እየሠራ እሷ ደሞ ጅግጅጋ ትሠራ እንደነበረው ዓይነት ተመሳሳይ የኮንስትራክሽን ሥራ ውስጥ እየሠራች መኖር ጀመሩ።

በዚያው ዓመት፤ በ2004 ዓ.ም መሆኑ ነው፤ ወንድ ልጅ ተገላገለች።

አጸደ እየቆየች ስትሄድ ግን "ትዳር ማለት የሕይወትን ሸክም ተካፍሎ ማቅለል ነው" የሚለው ትርጉም እውነት ሆኖ አላገኘችውም።

"ባለቤቴ ሞገደኛ ነው፤ በሚረባውም በማይረባውም፤ በትንሹም በትልቁም ይመታኛል፤ ያከራዩኝ ሰዎች ሁኔታችንን ሲያዩ እግዚኦ ይላሉ።" ትላለች የነበረችበትን ሕይወት ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታስታውስ።

ምንም እንኳን ድብደባው ቢበረታባትም፤ አጸደ እሷ ያደገችበትን ሁኔታ ስለምታውቅ ልጇን ያለ አባት ልታስቀረው አልፈቀደችም።

"ልጅ ከወለድኩ በኋላ እኛ አባታችን ስላልነበረ፤ እናታችን እንዴት ተቸግራ እንዳሳደገችን ስለማውቅ ሁሉን ችዬ እኖር ነበር። እንደዚያ ሲደበድበኝ አንድ ቀን እንኳን ለእናቴም ሆነ ለእህቴ ነግሬያቸው አላውቅም፤ አንድም ቀን" ስትል እምባ እየተናነቃት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከልጇ ጋር ሁሉን ችላ መኖሯ ግን የኋላ ኋላ መዘዝ ይዞባት መጣ። "የነበርኩበትን ሁኔታ የሚያውቁ ዘመድ አዝማዶች እናነጋግረው ሲሉኝ 'ተው እንጂ! ምንም ቢሆን እኮ የልጄ አባት ነው' እያልኩ ኑሮዬን ቀጠልኩ" ትላለች።

ነገሮች በዚህ ሁኔታ ቀጠሉ። በ2007 ዓ.ም ልጇን አዲግራት የምትኖረው እናቷ ጋር እንድትወስደው እሷ ደግሞ ከነበረችበት ሥራ ወጥታ በራሷ ሥራ እንድትጀምር ሐሳብ አቀረበላት። የሰጣት ገንዘብ ግን አልነበረም።

ልጇን ትታ መኖሩ እንዳሰበችው ቀላል አልነበረም። ስለ ልጇ ትብሰለሰል ያዘች። ቀኑ ነግቶ አልመሽ አላት።

አንድ ቀን "ወይ ከሥራዬ ወይ ከልጄ አልሆንኩ ምን ተሻለ?" ብላ ትጠይቀዋለች። እርሱ ግን ሀሳቧን እና ጭንቀቷን ከመጤፍ ሳይቆጥር ገንዘብ የሚባል የለኝም፤ የማውቀው ነገር የለም ሲል እንደመለሰላት ትናገራለች።

በዚህ አንድ ሁለት ሲባባሉ በተነሳ ግጭት በቡጢ ስለመታት ፊቷ አብጦ ነበር።

አሲድን እንደ መሳሪያ

መአዛን በስለት ወግቶ ከፖሊስ ያመለጠው አሁንም አልተያዘም

ጋምቤላ ያሉ ዘመዶች እሷና ባሏ ተስማምተው መኖር እንደማይችሉ በመረዳታቸው ተለያይተው እንዲሞክሩት በማሰብ እሷ ወደ አገሯ ሄዳ ሥራ እንደትሰራ ይመክራሉ።

በዚህም ተስማምተው 10 ሺህ ብር ሰጥተው አለያዩኝ ትላለች።

ወደ አዲግራት እንደተመለሰች አረብ አገር የምትኖር እህቷና እናቷ አግዘዋት ትንሽዬ የውበት መጠበቂያ ምርቶች [ኮስሞቲክስ] መሸጫ ሱቅ ከፈተች። ጥሩ መንቀሳቀስ ጀምራም ነበር።

ባለቤቷ ግን ድንገት ወደ አዲግራት ጠቅልሎ በመምጣት በቤተሰብ ግፊት በድጋሚ አብረው መኖር ጀመሩ።

ይሁንና አሁንም ሊስማሙ አልቻሉም። ይባስ ብሎ ሱቋ ውስጥ "ማን ገባ? ማን ወጣ?" እያለ መጨቃጨቅ ጀመረ።

ከዕለታት አንድ ቀን ባለቤቷ ብድግ ብሎ ወደ አረብ አገር ሄደ፤ ሳይነግራት። ከጂቡቲ ድንበር ደውሎ 8 ሺህ ብር ለደላላዎች ላኪልኝ አላት። በሁኔታው የተደናገጠችው አጸደ ከዚያም ከዚህም ብላ ላከችለት።

ከየመን ወደ ሳዑዲ ከተሻገረ በኋላ ደግሞ አረብ አገር ከምትኖረው እህቷ የሒሳብ ደብተር 15 ሺህ ብር እንድታስልክ አደረገ። ሳዑዲ ከገባና ሥራ ከጀመረ በኋላ ግን ጭራሽ መደወል ትቶ እንደተራራቁ ትናገራለች።

ሄድኩ ሳይል እንደወጣው፤ ከእለታት አንድ ቀን ደግሞ መጣሁ ሳይላት መጣ- አዲግራት።

"አሲድ አይቼ አላውቅም"

ቅዳሜ ሐምሌ 8 ቀን 2009 ዓ.ም።

አጸደ እዚያች ኮስሞቲክስ መሸጫ ሱቋ ውስጥ ምሽት ላይ ከጓደኛዋ ጋር እራት በልተው ይጫወቱ ነበር።

በጨዋታቸው መካከልም አንድ አፍታ ባለቤቷ ውልብ ሲል አየችው። በዚያ አካባቢ እሱን ማየቷ ደስ ስላላት ጓደኛዋን ትታ ወደ ቤቷ ጉዞ መጀመሯን ታስታውሳለች።

ጉዞዋ ቤታቸው በር እስክትደርስ ሰላማዊ ነበር።

"ቤታችን ግቢው በር አካባቢ ዝግባና ጥድ አለ። እዚያ ተደብቆ ቆይቶ ድንገት ደፋብኝ። ይሄ ቢጫው ሐያት የሚባለው የዘይት መያዣ ጄሪካን አለ አይደል? በሱ አሲድ ይዞ ነበር፤ ከዚያም ደፋብኝ" ትላለች።

በወቅቱ በመላ አካሏ ምን እንደፈሰሰባት የምታውቀው ነገር አልነበረም።

"የተደፋብኝ ነገር ጋዝ ነበር የመሰለኝ፤ በእሳት ሊያቃጥለኝ ፈልጎ መስሎኝ ነበር" ትላለች።

"ትንሽ ቆይቶ ግን ሰውነቴ መንደድ ጀመረ። ኡኡ እያልኩ ድረሱልኝ ስል ጮህኩ፤ እሱ ግን ባጃጅ አዘጋጅቶ ስለነበር አመለጠ። እናቴም እህቴም ባጃጁን ቢከተሉትም ሊደርሱበት አልቻሉም።"

አሁን ከራስ ቅሏ መላ አካላቷ የፈሰሰው አሲድ መላ አካላቷን ቀይሮታል። የዐይን ብርሃኗን አሳጥቷታል።

በጠዋት በሙሉ አካሏ ትታው የወጣችበት ቤት ማታ ተመርታ ገባች።

አጸደ በሕይወቷ አሲድ አይታ አታውቅም።

"ቃሉንም የማስታውሰው ኬሚስትሪ ስንማር ነው። በጭራሽ አይቼ አላውቅም። ሐኪሙም ግራ ገብቶት ነበር፤ ስለዚህ እርዳታ በቶሎ ማግኘት አልቻልኩም" ትላለች።

በመጀመሪያ አካባቢ ዐይኗ አካባቢ በተደረገላት ሕክምና የተወሰነ ማየት ጀምራ ነበር። ነገር ግን ዕይታዋ ከአንድ ሳምንት አላለፈም።

በዚህ የአሲድ ጥቃት ከዕይታዋ በተጨማሪ አንድ እግሯ፣ ሁለቱም እጆቿ፣ ሙሉ የፊት ገጽታዋ እስከ ደረቷ ድረስ፤ ጸጉሯ፣ የራስ ቅሏ እንዲሁም ጆሮዎቿ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ፆታዊ ትንኮሳን ደርሶብኛል በማለቷ ተቃጥላ እንድትሞት የተደረገችው ወጣት

ለአርባ ቀናት የተመላለሰችበት የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ብዙም እንዳልረዳት ትናገራለች።

ለተሻለ ሕክምና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ከተላከች በኋላም 40 ቀን የቆየ የአሲድ ጥቃት እንዴት አድርገን እንቀበል ብለው እምብዛምም ሊረዷት እንደማይችሉ እንደነገሯት ታስታውሳለች።

ሆኖም በመጨረሻ እኔ ኃላፊቱነት እወስዳለሁ ያለች አንዲት ሐኪም በማግኘቷ እርዳታ ማግኘት እንደቻለች እምባ እየተናነቃት ትናገራለች።

"ዐይንሽ መውጣት አለበት"

አጸደ በ2010 ዓ/ም መጀመሪያ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ታይላንድ ሄዳ ነበር። ለሁለት ወራት በዘለቀው ሕክምና ከ3 መቶ ሺህ በላይ ብር አስፈልጓት ነበር።

ይህንን ወጪ ለመሸፈን አቅሙ ስላልነበራት በተለያዩ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የሌሎች አገር ዜጎች ጭምር ድጋፍ አድርገውላት ሕክምናውን መከታተል ጀመረች።

ሆኖም ሕክምናው እንዳሰበችው አልሆነላትም። ከሁሉም በላይ ይመልሱልኛል ብላ ተስፋ ያደረገችበት እና በጉጉት ትጠብቀው የነበረው የዐይን ብርሃኗ መርዶ ይዞ መጣ።

አብራት የነበረችው ታላቅ እህቷ አንድ እሁድ ጠዋት በግሏ ይዛው ቆይታ የነበረውን ትልቅ ምሥጢር ነገረቻት።

"ኢንፌክሽን እየፈጠረብሽ ስለሆነ መውጣት አለበት ተብሏል አለችኝ" ስትል ዕለቱን በጠለቀ ሐዘን ታስታውሳለች።

እሁድ እሁድ ቤተክርስቲያን እሄድ ነበር፤ "ዐይኔን በሰንበት እንዲያወጡት አልፈልግም፤ አገሬ ውሰጅኝ አልኳት" ለእህቴ ትላለች።

ሕክምናዋን አቋርጣ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰቸው አጸደ፤ በሴቶች ማኅበር አዲስ አበባ በተቋቋመ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ማገገሚያ ማዕከል ለስምንት ወር እንድትቆይ ተደረገች።

"አንድ ሰው በረዳህ ቁጥር ያንተ ቁስል እየሻረ ይሄዳል" ወ/ሮ መንበረ አክሊሉ

በዚህ ማገገሚያ ማዕከል ሳለች በአርቲስት አዜብ ወርቁ በኩል አንዲት እገዛ ልታደርግላት የምትችል ሴት አገኘች፤ ይቺ በጎ አድራጊ ሴት ወ/ሮ መንበረ አክሊሉ ናት።

በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የምትኖረው መንበረ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን በማገዝ ስሟ የሚጠራ በጎ አድራጊ ናት።

በወንዶች የሚፈጸም ጥቃትን ጊዜ ሳትሰጥ የምታግዝበት ምክንያት እርሷም ኢትዮጵያ ሳለች ያለ ፈቃዷ በልጅነቷ ያገባቸው ሰው ያደረሰባት ግፍና መከራን በማስታወስ እንደሆነ ትገልጻለች።

"ሲጋራውን ካጨሰ በኋላ፤ ፊቴ ላይ ይተረኩሰው ነበር፤ አፍንጫዬን እስከመስበር የደረሰ ጥቃት ያደርስብኝ ነበር፤ ሦስት አራት ጊዜ ሊገድለኝ በመሞከሩ በመጨረሻ ቤቴን ለቅቄ እንድጠፋ ሆንኩ። በዚህ ምክንያት ጎዳና ለማደር ሁሉ በቅቼ ነበር በአንድ ወቅት" ትላለች ወ/ሮ መንበረ።

አሁን ያ ጊዜ አልፎ መልካም ትዳርና ጥሩ ሕይወት እየመራች እንደሆነ ትናገራለች።

በአጸደ የደረሰውን የአሲድ ጥቃት በማህበራዊ ሚዲያ በኩል መስማቷን የምትናገረው መንበረ፤ ከባለቤቷ ጋር በመመካከር እሷን ለመርዳት እንደወሰኑ ለቢቢሲ ገልጻለች።

"እሷ ላይ የደረሰውን ስመለከት እንደ ማንኛውም ዜጋ ሐዘን ተሰማኝ። በተለይ ልጅ እንዳላት ስሰማ አዘንኩ። እኔም እናት ስለሆንኩ ራሴን በእሷ ቦታ አስቀመጥኩት፤ በዚህ ልቤ እጅግ ተነካ፤ ከዚህም በተጨማሪ እኔም ያለፍኩበት መንገድ ስለሆነ እሷን ማገዝ አለብኝ ብዬ ተነሳሁ።"

መንበረ በአሲድ የተጠቃችን ዜጋ ስታግዝ አጸደ የመጀመሪያዋ አይደለችም።

በፈረንጆቹ በ2017 ዓ.ም አንዲት መሠረት የምትባል በፍቅረኛዋ አሲድ የተደፋባት ሴት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ በመውሰድ ሕክምና እንድታገኝ አድርጋለች።

መሠረት አሁን በመልካም ጤንነትና በጥሩ መንፈስ አሜሪካ ራሷን ችላ እየኖረች ትገኛለች።

አጸደን ወደ አሜሪካ ለመውሰድም ለመንበረ መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም።

ሦስት ጊዜ ያህልም በአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳዩ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። በመጨረሻም ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ጽፋ፤ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትዕዛዝ ነበር የተሳካው ትላለች።

የአጸደ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ የምትናገረው መንበረ "አሁን አጸደ ዐይነ ስውር ናት። ሆኖም በቅርቡ ማየት እንደምትችል እርግጠኛ ነኝ" ስትል ሙሉ ተስፋዋን ትገልጸላች።

"ራሴን ስለምወደው ነው እሷን ለማገዝ የወሰንኩት። ምክንያቱም አንድ ሰው ባገዝክ ቁጥር ያንተ ቁስል እየሻረ ይሄዳል። ምናልባትም እኔ ያደረኩት ነገር አይተው ሌሎች ሰዎችም ሌሎችን ማገዝ ይጀምሩ ይሆናል።" ትላለች መንበረ።

አጸደ አሁን ከመንበረ ጋር እየኖረች ትገኛለች። መንበረ የአጸደን የሕክምና ሁኔታ እና በሕይወቷ ስላሳደረችባት አዎንታዊ ተጽእኖ በማህበራዊ ሚዲያ ጽፋ ነበር።

አጸደ በበኩሏ ስለሷ የምትናገርበት ቃላት እንደሌላት ትናገራለች። ስላደረገችላት ነገር መናገር ስትጀምር ከቃላት ቀድመው እምባዎቿ ዱብ ዱብ ይላሉ።

"ዓለም የሁላችንም ናት"

አጸደ በአሜሪካ ያካሄደችውን ሕክምና እንደወደደችው ትገልጸላች። በተደረገላት የመጀመሪያ ቀዶ ጥገና የዐይን ክዳን እንደተሰራላት ትገልጻለች።

አሁን ዐይኗን መክደንና መግለጥ ትችላለች፤ የአሲድ ጥቃቱ የዐይን ብርሃኗን ብቻም ሳይሆን የዕይን ሽፋኗን ሙሉ በሙሉ አጥፍቶት ነበር።

በቅርቡ ደግሞ እዚያው አሜሪካ ለመኖር የሚያስችላትን ፍቃድ አግኝታለች። ይህ ደግሞ ከእሷ ተለይቶ ኢትዮጵያ የሚገኘው ልጇን ወደ አሜሪካ ለመውሰድ የሚያስችላት ነው።

አጸደ ስለ ሕይወት ያላት ትርጉም የሚደንቅ ነው።

"መልኬን አይቼው አላውቅም። እኔ ከ2 ዓመት በፊት የነበረችው አጸደን እንጂ አሁን ያለችውን አጸደን አይቻት አላውቅም" ትላለች።

የደረሰባት አካላዊ ጥቃት ሕይወቷን እንድትጠላ እንዳላደረጋት ግን አስረግጣ ትናገራለች።

በተቃራኒው እንዲያውም ለሕይወት መልካም አተያይን አዳብራለች።

"ሕይወት የሁላችንም ናት፤ በዚህ ዓለም ብዙ ጨካኝ አለ፤ ብዙ መልካም ሰዎች ደግሞ አሉ። በተለይ አንዳንድ ጊዜ ፈጣሪ እንዲህ ዓይነት ፈተና የሚያመጣብን ዓለም መልካም ሰዎች እንዳሏት እንድናስተውል ይሆን?" ትላለች።

አጸደ ከሕክምናዋ ጎን ለጎን ትምህርት ትማራለች። ማየት የማይችሉ ሰዎች የሚጠቀሙበትን የብሬል ትምህርት ተምራ አጠናቃለች። አሁን ደግሞ ኮምፒውተር እየተማረች ነው።

"ተምሬ ትልቅ ደረጃ እንደምደርስ እርግጠኛ ነኝ። አላማዬም እሱ ነው። ወደ ኋላ ተመልሼ የምጸጸትበት ነገር አይኖርም።"

"እሷ እናቴ አይደለችም የኔ እናት ቆንጆ ናት"

የአጸደ ልጅ ሃኒ ነው ስሙ።

ትናንት የደረሰባትን በደል፤ ደም ግባቷንና ዕይታዋን አስረስቷታል። አሁን ብርሃኗ ልጇ ነው።

ሀኒ ዕድሜው ገና 7 ነው። እኔ በሕይወት የምኖርበት አንዱ ምክንያቴ እሱ ነው ትላለች።

ይህ አደጋ አጸደ ላይ ሲደርስ እሱ ገና 5 ዓመቱ ነበር። በአሲዱ ምክንያት የደረሰባትን የገጽታ ለውጥ ሲመለከት ታዲያ በልጅነት አዕምሮው እናቱን ሊለያት አልቻለም።

"መጀመርያ ላይ በጣም ፈርቶ ነበር። እናትህ አጸደ እኮ እሷ ናት ሲሉት፤ ኖ ኖ እሷ እናቴ አይደለችም፤ የኔ እናት ቆንጆ ናት" እንዳለ ታስታውሳለች።

"አሁን ግን ሁኔታዎችን ስለተረዳ አይዞሽ ይለኛል። እሱ ስላለልኝ ደግሞ እኔ ጠንክሬ በሁለት እግሬ ለመቆም ቻልኩ ትላለች።"

አሁን ልጇ በአባቱ ቂም ቋጥሮ ጥላቻ እንዲያሳድር እንደማትፈልግ ትናገራለች።

"ልጄ ይቅርታ አድራጊ ሰው እንዲሆን ነው የምፈልገው። እኔም ይቅርታ አድራጊ ሰው እንድሆን እንጂ እንዲህ አድርጎኝ የምል ሰው መሆን አልፈልግም።" ትላለች።

"እኔን ሳይሆን የገዛ ልጁን ነው የበደለው" በማለት ልጇ በለጋ እድሜው መሸከም ከሚችለው በላይ ጫና መሸከሙን ትናገራለች።

የዘገየ ፍትሕ

የአጸደ ጥቃት አድራሽ ዛሬም ድረስ በፍትሕ አደባባይ አልቆመም። በወቅቱ የሚመለከተውን ክፍል ያሳወቀች ቢሆንም ይገኝበታል የሚባልባቸው ቦታዎችን ፈልጎ ለሕግ ለማቅረብ የሚመለከታቸው አካላት ግዴታቸውን እንዳልተወጡ ትናገራለች።

በደል የሚፈጽሙ አካላት በወቅቱ ሊጠየቁና የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙ የሚያስችል ሕግ እንደሌለ ጨምራ ታስረዳለች።

መንበረ በበኩሏ ሕብረተሰብን ከማስተማር ጎን ለጎን በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ቅጣት መጣል እንዲህ አይነት ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ያግዛል ትላለች።

ምክንያቱም ትላለች መንበረ፤ ይህ የአሲድ ጥቃት አጸደን ብቻ አይደለም የጎዳት፤ ልጇን፣ እናቷን፣ እህቷን እንዲሁም መላ ቤተሰቧንም ጭምር ነው።

ይህንን በተመለከተ የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋን አነጋግረናቸው ነበር።

ይህንን ወንጀል የፈጸመው ሰው ጠፍቶ ከአገር መውጣቱን የገለጹት አቶ አማኑኤል፤ ፖሊስ ከመጀመሪያው ይህንን ጥቃት ስለፈጸመው ሰው የተሟላ መረጃ አለማግኘቱን፤ በኋላም ወደ መሀል አገር ሄዷል በተባለ ጊዜ ደግሞ በአገሪቱ በነበረው ፖለቲካ፤ መሀል አገር ላለው አካል አመልክተው ሊተባበሯቸው እንዳልቻሉ ይገልጻሉ።

በአቃቢ ሕግ በኩል ደግሞ መጀመሪያ ችግሩ የነበረው በሕይወት ትቆያለች ወይ የሚለውን ለመገመት አስቸጋሪ ስለነበረ አቃቢ ሕግ በምን አግባብ ይክሰስ የሚለው አልተወሰነም ነበር ይላሉ።

"በአካል ማጉደል ከስሶ፤ በኋላ ደግሞ አንድ ጊዜ ከተፈረደበት በኋላ መልሶ በሰው መግደል ልታስፈርድበት ስለማይቻል አስቸጋሪ ነበር" ብለዋል ኃላፊው።

በኋላ ግን ሁኔታዎች በሕክምና ከተረጋገጡ በኋላ ግለሰቡ በከባድ የመግደል ሙከራ ተከሷል። አሜሪካ ሆና በ'ስካይፕ' ቃሏን እንድትሰጥ ተደርጎ ምርመራ ተካሄዶ አሁን ተከሶ እድሜ ልክ እንደተወሰነበት አቶ አማኑኤል ይገልጻሉ።

ወንጀለኛው በኢንተርፖል ወይም በሌላ መልኩ ወደ አገሩ ሲገባ ይህ ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል።

"ምን በድዬህ ነው?"

ከዚያች መጥፎ ዕለት ጀምራ አጸደ ባለቤቷን አይታው አታውቅም፤ ስለሱ ሰምታም አታውቅም። በአካል ድጋሚ ብታገኘው ግን አንድ ጥያቄ ልትጠይቀው አንደምትፈልግ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ምንድን ነው የበደልኩህ?" የሚል

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ