"የተመረጠው ኢህአዴግ እንጂ ብልጽግና አይደለም" ዶ/ር ሰለሞን ኪዳነ

ፒፒ/ህውሃት Image copyright PP/TPLF

ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሚኒስትሮች ሹም ሽር ማድረጋቸው ተሰምቷል።

የህወሃት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሄር በጠቅላይ ሚንስትሩ ሹም ሽር ከስልጣናቸው ከተነሱት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በተመሳሳይ የህወሃት ከፍተኛ አመራር የሆኑት በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር) ከስልጣን እንደሚነሱ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ይህን ተከትሎ ህወሃት ባወጣው መግለጫ አባላቱን ከፌደራል ከፍተኛ የሃላፊነት ደረጃዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማንሳት እርምጃ ህግን የጣሰና ችግርም የሚያስከትል ነው ብሏል።

ብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ የተደረገው የተለመደ ሹም ሽር ስለሆነ ከብሄር እና ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት አይገባም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚገኙ የህወሓት ካድሬዎችና የስራ ኃላፊዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እየተነሱ በሌሎች አባል ባልሆኑ እየተተኩ ነው ብለዋል።

"አዲስ አባባ ላይ እንደ ኢህአዴግ ነው የተወዳደርነው። ኢህአዴግ እስካሸነፈ ድረስ ህወሓት 25 በመቶ ቦታ፤ እኩል የማስተዳደር ስልጣን አለው። ይህንን አሰራር ማፍረስ ማለት የከተማውን መንግሥታዊ አስተዳደር መዋቅር ማፍረስ ማለት ነው" በማለትም እርምጃው ህግና ስርዓትን የተላለፈ ነው ይላሉ።

ላለፉት 28 ዓመታት ስልጣን ላይ የቆየው ኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሲሸጋገር ስሙን ብቻ ሳይሆን ርእዮተ ዓለሙን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ን በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ቀይሯል።

ህወሃት ይህ ሂደት ህገ-ወጥ ነው በማለት ብልፅግናን የማይቀላቀል መሆኑንን ማሳወቁ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ይበልጥ እንዳካረረው እየተስተዋለ ነው።

የህወሃት አባላትን ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሃላፊነት የማንሳት እርምጃም የዚህ መካረር ውጤት እንደሆነ ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ። መንግሥት እርምጃውን ከመውሰዱ በፊት ህወሃትን ማማከር ነበረበት ብለው ያምናሉ።

"ይሄ የፖለቲካ ስልጣን ነው። ህዝቡ ህወሃትን እና ፕሮግራሙን ነው የመረጠው። ህወሃትን ሊወክሉ የሚችሉ ሰዎችን ህወሃት ራሱ ብቻ ነው ሊያቀርብ የሚችለው። በስመ የትግራይ ተወላጆች መተካት አይቻልም። ይሄ አካሄድ ሕገ-ወጥ ነው። የብሄር ተዋጸኦ ነው ያስመሰሉት" ይላሉ።

"ህወሃት በህዝብ ተመርጦ እንጂ ለምኖ የመጣ ድርጅት አይደለም" የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን፤ ህወሃት ከብልጽግና ጋር አልዋሃድም ስላለ ብቻ በትግራይ ህዝብ የተመረጡ ግለሰቦችን እየለዩ ከሃላፊነታቸው ማንሳት የህዝብ ድምጽ እንደመቀማነት ይታያል ሲሉ ይከራከራሉ።

"የተመረጠው ኢህአዴግ እንጂ ብልጽግና አይደለም" በማለትም መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።

በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል መካረር ተፈጥሮ እያለ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች እንዴት በፌደራል ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ሊቀጥሉ ይችላሉ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ሰለሞን ሲመልሱ "ገና ወደ መድብለ ፓርቲ እንሄዳለን እያልን አይደል እንዴ? ህወሃት አብሮ ሲሰራ የነበረው ህጋዊ ስልጣን ስላለው ነው። የመንግሥት ሥራን በጋራ መስራት ይቻላል እየተሰራም ነበር ብዬ ነው የማምነው። ልዩነቱ የፖለቲካ እንጂ አብሮ የማያሰራ አልነበረም" ይላሉ።

በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የምታምኑ እና አዲሱን የመደመር ፍልስፍና የማትቀበሉ ከሆነ እንዴት አብራችሁ ልትቀጥሉ ትችላላችሁ? ለዶ/ር ሰለሞን ያነሳነው ተከታይ ጥያቄ ነበር።

"አዲሱን ፕሮግራም ህዝቡ አያውቀውም አልመረጠውምም። ህዝቡ የመረጠው የቀደመውን ነው። ስለዚህ ጥያቄው መሆን ያለበት ህዝቡ በብልፅግና ፕሮግራም ሊተዳደር ይችላል ወይ? የሚለው ነው"

እሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳ ለውጡን ተከትሎ የኢህአዴግ ፕሮግራምና አቅጣጫ ተትቶ ሌላ አቅጣጫ የተመረጠ ቢሆንም በፌደራል ደረጃ እንዲሁም በአዲስ አበባ ደረጃ ያሉ የህወሃት ባለስልጣናት በህዝብ ህጋዊ ስልጣን የተሰጣቸው በመሆናቸው ህዝብ በድምፁ እስኪያነሳቸው በሃላፊነት መቀጠል አለባቸው፤ ፖለቲካውም የትግል ሜዳ መሆን አለበት።

ሹም ሽሩ ከህግ አንፃር?

የህግ ባለሙያና የህገ መንግስት ምሁር አቶ ምስጋነው ሙሉጌታ ስልጣን ላይ ያለው መንግስትን የመሰረተው ግንባር ሊፈርስ እንደሚችልና አብላጫ ድምጽ ያለው ፓርቲ በስልጣን ሊቀጥል እንደሚችል ተደንግጎ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በሌሎች አገራትም ይሄ የተለመደ እንደሆነ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ከሌሎች አገራት ልምድ በሚለይ መልኩ በኢትዮጵያ የሆነው፤ ጥምረቱ ብቻ ሳይሆን የፈረሰው ጥምረቱን የፈጠሩት አባል ድርጅቶቹ ራሳቸውን ማክሰማቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።

"የሆነ ህገ-መንግሥታዊ ሂደት መኖር አለበት። የፓርላማ አባላት የአዲሱ ብልጽግና ፓርቲ አባል ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚፈልጉ መጠየቅ አለባቸው። ቁጥራቸው የበዛና የበላይነቱን የሚይዙ ከሆነ ችግር የለውም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ህገ-መንግስታዊ ሂደቱን ያሟላ ነው ይባላል" ብለዋል።

"በእርግጥ ይሄንንም ሃሳብ ቢሆን የፖለቲካ ምሁራን ይተቹታል። አዲስ ፓርቲ ሆኖ በአዲስ ፕሮግራም እቀጥላለሁ ቢል የቅቡልነት ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል። ይሁን እንጂ ቢያንስ ህጋዊ ሂደቱን አሟልቷል ይባላል"።

አዲሱን የምረጫ ህግ በመጥቀስ ይህንን ያልተቀበሉ የፓርላማ አባላት በግል አልያም በተቀዋሚነት መቀጠል እንደሚችሉም አቶ ምስጋናው ያስረዳሉ። በዚህ መሰረት ከ547 የፓርላማ አባላት ምን ያህሎቹ ብልፅግናን ተቀብለው መቀጠል እንደሚፍልጉና መቀጠል እንደማይፈልጉ ፓርላማው፤ ግልጽ ማድረግ ነበረበት ይላሉ። ብልፅግና ሆነው የሚቀጥሉት አብላጫ ድምፅ እንደሚይዙ ምንም ጥርጥር የለውም።

ይህ ሆኖ እያለ የህግ አግባብን ተከትሎ ነገሮችን ማድረግ ያልፈለጉት ለምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም ይላሉ አቶ ምስጋናው።

"የፖለቲካ ሹመቶቹ ብዙም አያሰደንቅም" የሚሉት የህግ ምሁሩ፤ አንድን ሚኒስትር መሻር የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ስለሆነ ያን ላለማድረግ አይገደድማ ባይ ናቸው።

ይሁን እንጂ አዲስ ሚኒስትር ሲሾም ለፓርላማው ቀርቦ መጽደቅ እንዳለበትና ይህ እየተረደገ እንዳልሆነ ያስረደሉ። ብልጽግና ፓርቲ ቢያንስ የህግ የበላይነት ለማክበር ይህንን ሂደት መከተል እንደነበረበት ያስቀምጣሉ።

"ይሄ ተራ የሂደት ነገር ሊመስል ይችላል። ከህግ የበላይነበት አንጻር ግን መሰረታዊ ነገር ነው። ምክንያቱም የህግ የበላይነት መሸርሸር የሚጀምረው እንደዚህ ዓይነት አካሄድን መጣስ ስትጀምር ነው" ይላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ