ቻይና ኮሮናቫይረስ፡ በመቶ ሚሊዮኖች በሚደረጉ ጉዞዎች ሥርጭቱ ሊስፋፋ እንደሚችል ተሰግቷል

በውሃን የፅዳት ሠራተኛ Image copyright Getty Images

ቻይና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በሚያከብሩት ሉናር አዲስ ዓመት ተከትሎ በሁቤ ግዛት የተከሰተውን ገዳይ ቫይረስ ሥርጭት ለመቆጣጠር ግብ ግብ ገጥማለች።

ሉናር የቻይናውያን አዲስ ዓመት ሲሆን በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። ይህ በዓል በዓለማችን በርካታ ሰዎች ጉዞ የሚያደርጉበት ወቅት ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓሉን ለማክበር ወደ አገራቸው ይገባሉ።

ባለሥልጣናት በቤጂንግ እና ሆንግ ኮንግ የሚደረጉ ትላልቅ ዝግጅቶች እንዳይካሄዱ ሰርዘዋል።

ሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ 'ካርኒቫሎችን' እና ዓመታዊ የሆነውን የእግር ኳስ ውድድር እንዳይደረግ ከልክላለች።

ቻይና የተከሰተው ገዳይ ቫይረስ በርካቶችን ሳይበክል አልቀረም

ቻይና ውስጥ የተከሰተው ቫይረስ አሜሪካ ደረሰ

ቫይረሱ ከተከሰተበት ውሃን ግዛት አውሮፕላን ወይም ባቡር እንዳይገባም እንዳይወጣም ተከልክሏል፤ መንገዶች መዘጋታቸው ተነግሯል።

በዉሃን ግዛት ሰዎች የፊት ጭምብል አድርገው መንቀሳቀሳቸው ግድ ሆኗል።

ዉሃንን ጨምሮ በሁቤ ግዛት የሚገኙ ሌሎች ከተሞች የሕዝብ የመጓጓዣ አገልግሎቶችን ከልክለዋል።

የቻይና ባለሥልጣናት እንዳሉት በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 25 ከፍ ያለ ሲሆን 830 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

በቫይረሱ እንደተያዙ ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል 177ቱ በአስጊ ሁኔታ የሚገኙ ሲሆን፤ 34 ከበሽታው ድነው ከህክምና ተቋም መውጣታቸውን የአገሪቷ የጤና ኮሚሽን አስታውቋል።

ከዚህም ባሻገር 1,072 በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩ የተጠረጠሩ ሰዎች መኖራቸውንም ኮሚሽኑ አክሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከቻይና ውጭ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 13 መሆናቸውና ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ ቫይረሱ 'ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ' ነው ሲል አልፈረጀውም።

ይሁን እንጅ "ምን አልባት አስቸኳይ ትኩረት ከሚያስፈልጋቸው አንዱ ሊሆን ይችላል" ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ማክሰኞ አሜሪካ ሁለተኛውንና በቫይረሱ ሳይያዝ እንዳልቀረ የተጠረጠረ ሰው ምርመራ እያደረገች እንደሆነ ገልጻለች።

ሌሎች የዓለም አገራትስ ?

ታይላንድ፣ አሜሪካ፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቬየትናምና ሲንጋፖር ባሳለፍነው ማክሰኞ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ በቫይረሱ የተያዘ ሁለተኛ ሰው ማግኘታቸውን አረጋግጠዋል።

እስካሁን ከቻይና ውጭ 13 በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ከቻይና ቀጥሎ ታይላንድ በብዛት በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተገኙባት አገር ሆናለች።

ዩናይትድ ኪንግደምና ካናዳን ጨምሮ በበሽታው ሳይያዙ እንዳልቀሩ የተጠረጠሩ ሰዎችን እየመረመሩ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በቴክሳስ ግዛት ሁለተኛውን በቫይረሱ የተጠረጠረ ሰው ላይ ምርመራ እያደረገች እንደሆነ ያሳወቀችው ባለሰፈው ማክሰኞ ነበር።

ታማሚው ከቻይናዋ ዉሃን ወደ ቴክሳስ ያቀናና የቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆኑ ታውቋል።

የኢቢሲ ጋዜጠኞች ለምን ይጠፋሉ?

በአሜሪካ እስካሁን በቫይረሱ እንደተያዘ የተረጋገጠው በዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ሲሆን ግለሰቡ አገግሞ ከሆስፒታል መውጣቱ ተገልጿል።

በርካታ ባለሥልጣናት ዱባይና አቡዳቢ አየር መንገዶችን ጨምሮ ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች የጤና ምርመራ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ታይዋን ከውሃን የሚመጡ መንገደኞች እንዳይገቡ እገዳ ጥላለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ቻይና የሚያቀኑ አሜሪካዊያን ተጓዦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ