የዶስ ሳንቶስ ኢሳቤላ የሒሳብ ባለሙያ ሞቶ ተገኘ

ኢሳቤላ ዶስ ሳንቶስ Image copyright Getty Images

አገሯን በሙስና አራቁታለች ተብላ ክስ የተመሰረተባት የአፍሪካ ሃብታሟ ሴት የሒሳብ ባለሙያ በፖርቹጋል ሞቶ ተገኘ።

ይህ የሂሳብ ባለሙያ በኢሳቤላ ዶስ ሳንቶስ የክስ መዝገብ ላይ ተጠርጣሪ ተብሎ ስሙ ተጠቅሶ ነበር።

የ45 ዓመቱ ኑኖ ሪቤኢሮ ዳ ኩሃን የተባለው የሒሳብ ባለሙያ በኢሳቤላ ዶስ ሳንቶስ ሊቀመንበርነት ይመራ የነበረው ሶናንጎል የተባለው በአንጎላ የነዳጅ ዘይት አምራች ኩባንያ ገቢ ወጪዎችን ይቆጣጠር ነበር።

የአፍሪካ ባለጸጋዋ ሴት አገሯን በሙስና እንዴት እንዳራቆተቻት የሚያመላክቱ መረጃዎች ሲወጡ ነበር። ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ልጅ ስትሆነ የአንጎላ መንግሥት የሙስና እና ማጭበርበር ክሶች መስርቶባታል።

የሒሳብ ባሙያው ሞት የተሰማውም የአንጎላ ጠቅላይ አቃቤ ሕጎች ሁለቱን ግለሰቦች በወንጀሎቹ ተጠርጣሪ መሆናቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

የፖርቹጋል ፖሊስ እንዳለው የሂሳብ ባለሙያው ሞቶ የተገኘው በመዲናዋ ሊስበን ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በአንዱ ሲሆን፤ "ሁሉም ነገር የሚጠቁመው ሕይወቱን በራሱ እጅ ስለማጥፋቱ ነው" ብለዋል።

የፖርቹጋል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ የሂሳብ ባለሙያው ከአንድ ወር በፊትም እራሱን ለማጥፋት መሞከሩን ዘግበዋል።

ኢሳቤላ ዶስ ሳንቶስ የቀረቡባትን ክስ "ፈጽሞ አሳሳች እና ሃሰተኛ" ስትል ታጣጥላለች።

ኢዛቤል ዶስ ሳንቶስ በመሬት፣ በአልማዝ፣ በነዳጅ ዘይት ዘርፍ በመሰማራት የመንግሥትን እጅ በመጠምዘዝ ከድሃ አንጎላዊያን ጉሮሮ እየነጠቀች ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንዳካበተች ይነገራል።

በተለይ አባቷ በመንግሥት ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የኢንቨስትመንት አማራጮች ለእርሷ ብቻ ተብለው የሚከፈቱና የሚዘጉ ነበሩ።

ከነዳጅ ጋር በተያያዘ

አንድ የለንደን የነዳጅ አውጭ ኩባንያ በአገሯ እንዲሰራ በተጭበረበረ መንገድ ሲገባ ወይዘሮ ዶስ ሳንቶስ የትወናው አካል ነበረች። በኋላ አባቷ ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ ኩባንያው ሲታገድ 58 ሚሊዮን ዶላር የከፈለችበት ደረሰኝ ተገኝቷል። ይህ ለምን እንደተፈጸመና ድርሻዋስ ምን ነበር የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።

የወይዘሮ ኢሳቤላ ዶስ ሳንቶስ ጉዳይ በዚህ አያበቃም። አንድ ዱባይ ከሚገኝ ኩባንያ ጋርም በተመሳሳይ ተመሳጥራ ሁለት የክፍያ ሰነዶች እንደተላኩላት ማግኘት ተችሏል። ይህ ሕጋዊነት ይጎድለዋል የተባለው የክፍያ ሰነድም ለምን ክፍያው እንደሚፈጸም የሚያትተው ነገር የለም።

በዚህ የሂሳብ መጠየቂያም በአንደኛው 472,196 ዩሮ ሁለተኛው ደግሞ 928,517 የአሜሪካን ዶላር ተጠይቆበታል።

ይህም ሰነድ ሕጋዊነቱ ያልተረጋገጠ ቢሆንም ወይዘሮዋ ግን ሕጋዊ መንገድን ተከትየ የፈጸምኩት ነው ብላለች።

አጭር የምስል መግለጫ ለኢሳቤላ የተላከ ሰነድ

ሌላኛው ከነዳጅና ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለኢሳቤላ የቀረበው ክስ በ2006 የአንጎላ የኃይል አቅርቦት ለመሥራት ስትስማማ በወቅቱ 15% ብቻ ከፍላ ቀሪው ዝቅተኛ ወለድ ተደርጎላት በተራዘመ ጊዜ እንድትከፍል ነበር። ላለፉት 11 ዓመታት ግን መክፈል የነበረባትን 70 ሚሊዮን ዶላር አልከፈለችም። አሁን ኢሳቤላ በባለድርሻነት የምትመራው ኩባንያ አጠቃላይ ዋጋው 750 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።

ተቋሟ እዳውን በ2017 ለመክፈል ተስማምቶ ነበር፤ ነገር ግን ቢያንስ ወለድ ተብሎ የታሰበውን 9 በመቶ ማካተት ስላልቻለ ክፍያው እንዳይፈጸም ተደርጓል።

ከአልማዝ ጋር በተያያዘ

በሙስና ሥራው ኢዛቤል ብቻዋን አትሳተፍም። ባሏም አጋሯ ነው። በ2012 ባለቤቷ ሲንዲካ ዶኮሎ መንግሥት ከሚቆጣጠረው ሶዳየም ከሚባለው የአልማዝ ኩባንያ ጋር የአንድ ወገን ፊርማ ፈርሟል።

በፊርማው መሰረት ሁለቱ ፈራሚዎች የፕሮጀክቱን ወጪ ግማሽ ግማሽ መቻል ነበረባቸው።

ነገር ግን ሙሉ ወጭው የተሸፈነው በመንግሥት ነው። ሰሞኑን የሚዲያዎች እጅ ላይ የገባው መረጃ እንደሚያሳየው ከ18 ወራት በኋላ ዶኮሎ 79 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ሲገባው የከፈለው የገንዘብ መጠን ግን 4 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

ይባስ ብሎ ደግሞ ጉዳዩን ስለደለልኩ ሽልማት ይገባኛል ብሎ ከዚሁ ፕሮጀክት ውስጥ የኢሳቤል ባለቤት ዶኮሎ ተጨማሪ 5 ሚሊዮን ዶላር ራሱን ሸልሟል።

ከዚህ ስምምነት የአንጎላ ሕዝብ የሚያገኘው ጥቅም ምንም ሲሆን በአንጻሩ ለኩባንያው መሥሪያ ተብሎ ከግል ባንክ ለተበደሩት 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይከፍላሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአንጎላ መንግሥት አልማዝ በዝቅተኛ ዋጋ መሽጡን ቢያምንም ምንጮች እንደሚሉት ግን እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ከስሯል። ከዚህ ጀርባ ማን ሊኖር ይችላል ሲባል ደግሞ የብዙዎቹ ግምት ኢሳቤላ ዶስ ሳንቶስና ባለቤቷ መሆናቸውን አብዛኛው የአገሬው ሰው ይረዳዋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኢሳቤላ እና ባለቤቷ

ከመሬት ጋር በተያያዘ

ወይዘሮ ዶስ ሳንቶስ መሬት ላይም ሁነኛ ተሳታፊ ናቸው። መረጃው እንደሚያሳየው ወይዘሮ ዶስ ሳንቶስ በ2017 በዝቅተኛ ዋጋ መሬት እንድትገዛ መንግሥት አመቻችቶላታል። ይህንን በመዲናዋ ሉዋንዳ የባህር ዳርቻ የሚገኘውን ጋሻ መሬት የገዛችውም በአባቷ ረጅም እጅ በመታገዝ ነበር።

ኮንትራቱ የሚለው መሬቱ 96 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ነው። ወይዘሮ ዶስ ሳንቶስ ያወጣችው ግን 5 በመቶ ብቻ ነው። ምስኪን ቦታው ላይ የነበሩ አንጎላዊያን ግን ይዞታቸው ለወይዘሮ ዶስ ሳንቶስ በመሰጠቱ ከነበሩበት ዋና ከተማዋ ሉዋንዳ 50 ኪሎ ሜትር ርቀው ተጥለዋል። ከመሬት ጋር በተያያዘ በሌላ የኢሳቤላ ዶስ ሳንቶስ ፕሮጀክት ከ500 በላይ ቤተሰብ በእርሷ ምክንያት ተፈናቅሏል።

ከቴሌኮም ዘርፍ ጋር በተያያዘ

ቢሊየነሯ ከቴሌኮም ዘርፍም አንጎላ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ አግበስብሳለች። በአገሪቱ ከፍተኛው የሞባይል ስልክ አቅራቢ ኩባንያ ውስጥ 25 በመቶ ድርሻ አላት።

ዩኒቴል የተባለው ይህ ኩባንያ በቅርቡ ለኢሳቤላ 1 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ የሰጣት ሲሆን ቀሪ ሀብቷም ሌላ 1 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሏል። ይሁንና ሴትዮዋ ከዘርፉ ገንዘብ የምታገኝበት ይህ ብቸኛ መንገድ አይደለም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ