በትራምፕ የክስ ሂደት የተሰላቹ ሴናተሮች ሲጫወቱ እና ሲያንቀላፉ ታዩ

ዋይት ሃውስ Image copyright THE WASHINGTON POST/GETTY IMAGES

በትራምፕ የክስ ሂደት ላይ ሴናተሮች ተሰላችተው ሲጫወቱ፣ ሲያንቀላፉ እና ከመቀመጫቸው በተደጋጋሚ ሲነሱ ተስተውለዋል።

በሴናተሮቹ ተግባር አሜሪካውያን ብስጭታቸውን እየገለጹ ነው።

ለረዥም ሰዓታት በሚዘልቀው የክስ ሂደት የተሰላቹት ዲሞክራት እና ሪፓብሊካን ሴናተሮች በተደጋጋሚ ከመቀመጫ ወንበሮቻቸው እየተነሱ ሲወጡ ሲገቡ፣ መጽሄቶችን ሲያነቡ፣ ሲያንቀላፉ እና መጽሄት ጀርባ ላይ ያሉ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ታይተዋል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሴናተሮቹን በወሳኝ ጉዳይ ላይ "ልክ እንደ ህጻን ስልቹ" ሆነው ታይተዋል ሲሉ አብጠልጥለዋቸዋል።

ሮይተርስ ቢያንስ 9 ዲሞክራቶች እና 22 ሪፓብሊካን ሴናተሮች በተለያዩ አጋጣሚዎች ወንበሮቻቸውን ጥለው ተነስተዋል ሲል ዘግቧል።

ስልቹ ሆነው ከመቀመጫቸው ከተነሱት መካከል የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዕጩ የሆኑት ዲሞክራቱ በርኒ ሳንድረስ ይገኙበታል።

ማርክ ዎርነር የተባሉት የቨርጂኒያ ግዛት ዲሞክራት ለ20 ደቂቃዎች ያክል ዐይናቸውን በእጃቸው ሸፍነው ተኝተው ነበር ተብሏል።

ከኬንታኪ ግዛት የመጡት ሪፓብሊካኑ ራንድ ፖል ደግሞ የክስ ሂደቱ እየተሰማ እርሳቸው ከወረቀት የአውሮፕላን ቅርጽ ሲሰሩ ነበር።

መነጋገር በማይፈቀድበት የክስ ሂደት ላይ ሴናተሮች በብጣሽ ወረቀት እየተጻጻፉ መልዕክት ሲለዋወጡም ተስተውሏል።

በዚህ የትራምፕ ክስ ሂደት ላይ ሴናተሮች ስልክ ወይም ላፕቶፕ ይዘው እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎ ሴናተሮቹን እረፍት አልባ አድርጓቸዋል ተብሏል።

ሴኔቱ የትራምፕን የክስ ሂደት መስማት የጀመረው ማክሰኞ ዕለት ሲሆን፤ የክስ ሂደቱ ሳይቋረጥ ለበርካታ ሰዓታት የሚዘልቅበት አጋጣሚዎች አሉ።

ሴኔቱ ጉዳዩን ተመልክቶ ድምጽ መቼ እንደሚሰጥ በትክክል ባይታወቅም፤ ለሳምንታት ሊቀጥል ይችላል ተብሏል።

ትራምፕ ጥፋተኛ ናቸው ለማለት እና ከሥልጣን ለማስነሳት የሴኔቱ 2/3 ድምጽ ያስፈልጋል። ይህ ማለት ከ100 የሴኔት መቀመጫ 67ቱ ትራምፕ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል።

የትራምፕ አጋር የሆኑት ሪፓብሊካኖች በሴኔቱ አብላጫ የሆነ 53 መቀመጫ አላቸው።

የትራምፕ ተቀናቃኝ የሆኑት ዲሞክራቶች በሴኔቱ ያላቸው መቀመጫ 47 ብቻ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ትራምፕ ላይ የተነሳው ክስ ውድቅ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ገምተዋል።

ከተገመተው ውጪ ሆኖ ትራምፕ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ፤ ከሥልጣን ይባረራሉ፤ ከዚያም ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ መንበረ ሥልጣኑን ይረከባሉ።

በዚህ ብቻ ሳይወሰን፤ የትራምፕ ጉዳይ በወንጀል ሕግ ታይቶ ከሥልጣን በኋላ ዘብጥያ ሊወርዱም ይችላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች