የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ ጭምር የዘገበው የቢቢሲ አርታኢ በሥነ-ልቦና ጭንቀት ኃላፊነቱን ለቀቀ

ፈርጋል ኬን በተለያዩ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይም ዘገባዎች ሰርቷል።
አጭር የምስል መግለጫ ፈርጋል ኬን በተለያዩ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይም ዘገባዎች ሰርቷል።

የቢቢሲ አፍሪካ አርታኢ በመሆኑ ለረዥም ዓመታት ያገለገለው ፈርጋል ኪን ከሥራው የመነጨ የሥነ-ልቦና ጭንቀት ምክንያት ከኃላፊነቱ ተነሳ።

ፈርጋል ኪን የሩንዳን የዘር ጭፍጨፋ ጨምሮ በርካታ ጦርነቶችን ዘግቧል። ይህም በሥራው ያያቸው እና ያጋጠሙት ልማዶች ለሥነ-ልቦና ጭንቀት (post-traumatic stress disorder-PTSD) ዳርገውታል።

የቢቢሲ ዜና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ጆናታን ሙንሮ፤ ጋዜጠኛውን ለዚህ ተጋላጭ ያደረገው "በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተዘዋውሮ ለበርካታ አስርተ ዓመታት የዘገባቸው የግጭት ሥራዎች ናቸው" ብለዋል።

ኃላፊው ጨምረውም ፈርጋል ኪን "ለብዙ ዓመታት ፒ ቲ ኤስ ዲ [PTSD] ያስከተለበትን ጫና ለመቋቋም ጥሯል" ብለዋል።

ኬን እ.አ.አ. 1996 ላይ በላቀ የጋዜጠኝነት ሥራው የእግሊዝ አገር ከፍተኛ ሽልማትን (ኦቢኢ) መሸለም ችሏል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ፈርጋል ኪን እአአ 2016 ላይ

የዜና ክፍሉ ኃላፊ ሙንሮ፤ ባልደረቦቹ ኬንን ሲረዱት መቆየታቸውን እና ድርጅቱም ሙያዊ ድጋፍ ሲያደርግለት እንደነበረ አስታውቀዋል። "በፍጥነት እንዲያገግም ካለበት የሥራ ኃላፊነት መነሳት እንዳለበት አምኗል" ሲሉም አክለዋል።

ኪን "ስለ PTSD በግልጽ መናገሩ ጠንካራ መሆኑን ያሳያል፤ እኛም አድንቀነዋል" ብለዋል።

ኪን እአአ 1989 ላይ የኮርፖሬሽኑን ሰሜን አየርላንድ ቢሮ ዘጋቢ ሆኖ የተቀላቀለ ሲሆን ከዚያም ደቡብ አፍሪካ እና ኢሲያ ሃገራት ጉዳዮች ላይ ዘገባዎችን ሰርቷል።

1994 ላይ በሠራው የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ የአምነስቲ ቴሌቪዥን ሽልማትን ወስዷል።


'ቅሽለት' ስለሚባለው የአእምሮ ጤና ችግር ያውቃሉ?

የትራምፕ ''የማመዛዘን አቅም ጤነኛ ነው''

ታዋቂው ፀሀፊ የአዕምሮ ህመሙን ለመደበቅ ካንሰር ታምሜያለሁ ብሎ መዋሸቱን አመነ

ፒ ቲ ኤስ ዲ ምንድነው?

  • በጣም አስጨናቂ፣ አስፈሪ እና ለሕወይት አስጊ የሆነ ቦታ ላይ ራስን ማግኘት ወደ ፒ ቲ ኤስ ዲ ሊያመራ ይችላል።
  • ከክስተቱ በኋላ ከፍተኛ የሃዘን ስሜት፣ ጭንቀት፣ የተጠያቂነት ስሜት እና ብስጭት ሊኖሩ ይችላሉ።
  • የፒ ቲ ኤስ ዲ ምልክቶች ወዲያው መታየት ሊጀምሩ ወይም በጣም ዘግይተው ሊስተዋሉ ይችላሉ።
  • አንዳንድ ሰዎች ክስተቱ ዳግም ሊከሰት ይችላል በማለት በየትኛውም ሥፍራ ላይ ነቅተው የመቆየት ዝንባሌ አላቸው።
  • የማያቋርጥ አካላዊ ህመም፣ ተቅማጥ፣ ወጥነት የሌለው የልብ ምት፣ ራስ ምታት የመሳሰሉ አካላዊ ምልክቶችም ሊኖሩ ይችላሉ።
  • የህመሙ ተጠቂዎች አልኮል እና እጾችን በብዛት መውሰድ ሊጀምሩ ይችላሉ።

ምንጭ፡ ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ሳይካትሪስትስ

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ