ባለ ጦር አፍ አሳ አንገቱ ላይ ተቀርቅሮ ሕይወቱ በአስደናቂ ሁኔታ የተረፈችው ታዳጊ

የ16 ዓመቱ ኢንዶኔዥያዊ ሙሃሙድ ኢዱል።
አጭር የምስል መግለጫ የ16 ዓመቱ ኢንዶኔዥያዊ ሙሃሙድ ኢዱል።

ባለ ጦሩ አፍ አሳ አንገቱ ላይ ከተቀረቀረ በኋላ ሕይወቱ በአስደናቂ ሁኔታ የተረፈችው የ16 ዓመቱ ኢንዶኔዥያዊው ታዳጊ ያጋጠመውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ማሳሰቢ፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ስሜት ሊረብሽ የሚችል ፎቶ ተካቷል

ሙሃሙድ ኢዱል የ16 ዓመት ታዳጊ ሲሆን ከትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር በመሆን የቀኑን የመጨረሻ ዙር አሳ ለማስገር ጀልባ ላይ ሆነው ወደ ሐይቅ ይገባሉ።

ሙሃሙድ "ጓደኛዬ ሳርዲ ከእኔ ቀደም ብሎ ተነሳ። ከዛ እኔ ከእሱ ቀጥዬ ጀልባዬ ላይ ወጥቼ መቅዘፍ ጀመርኩ" ይላል ከስድስት ቀናት በፊት ያጋጠመውን ክስተት ማስረዳት ሲጀምር።

የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ መፃኢ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

"500 ሜትር ያክል ከቀዘፍኩ በኋላ ጓደኛዬ ሳርዲ በእጁ ይዞ የነበረውን የእጅ ባትሪ ሲያበራ፤ ባለ ጦር አፍ አሳ [Needlefish] ድንገት ከሐይቁ ውስጥ ዘሎ ወጥቶ አንገቴን ወጋኝ" ይላል።

Image copyright Andrew Eio
አጭር የምስል መግለጫ ኒድልፊሽ ተብሎ የሚጠራው አሳ አፉ እንደ ጦር የረዘመና ጥርስ ያለው ነው።

የአሳው ፍጥነት ከፍተኛ ስለነበረ የሙሃመድ አንገትን በስቶ ከገባ በኋላ በተቃራኒ በኩል ጫፉ ወጥቶ የታዳጊው አንገት ላይ ተቀርቅሮ ቀርቷል።

ሙሃሙድ ሁኔታውን ሲያስታውስ፤ "ድንገት አሳው ሲወጋኝ ወደ ሐይቁ ወደኩ። ምሽት ስለነበር ውሃው በጣም ጨልሞ ነበር። አንገቴ ላይ ተቀርቅሮ የገባው አሳው ለማምለጥ ሲሞክር በኃይል ይንቀሳቀስ ነበር" ይላል።

ሙሃሙድ ሐይቁ ውስጥ እንዳለ በአሳው ንቅናቄ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስበት አሳውን ከአንገቱ ጋር አጥብቆ እንደያዘ ይናገራል።

"ሳርዲ እንዲረዳኝ ጠየኩት። አሳውን ከአንገቴ ላይ ልነቅል ስል ደግሞ 'ደም ይፈስሃል አትንቀል አለኝ'" ይላል ሙሃሙድ።

Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ አሳው የሙሃሙድ አንገት ላይ ተቀርቅሮ የሚያሳየውን ምስል በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተቀባብለውታል።

75 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመውን የአሳ አፍ አንገቱ ላይ ተቀርቅሮ እንዳለ በጓደኛው እርዳታ ሐይቁን ዋኝቶ ወጣ።

ከዚያም የሙሃሙድ አባት ልጃቸውን በ30 ደቂቃ ርቀት በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ባኡ-ባኡ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ።

በባኡ-ባኡ ሆስፒታል የሚገኙ ዶክተሮች ከአንገቱ ውጪ ያለውን የአሳውን ክፍል ቆርጠው ቢያሶግዱም አንገቱ ውስጥ ተቀርቅሮ ያለውን የአሳ አካል ለማውጣት የሚያስችል የመሳሪያም ሆነ የሰው ኃይል ስላልነበራቸው ወደ ሌላ ሆስፒታል ይልኳቸዋል።

ከዚያም አባት ልጃቸውን ይዘው ወደተባሉበት ሆስፒታል ያመራሉ።

እናት አልባዎቹ መንደሮች

ዌል የተባለው የባህር እንስሳ 6 ኪሎ ያህል ኩባያ ውጦ ተገኘ

በተባለው ትልቅ ሆስፒታል ቢደርሱም፤ ይህም ሆስፒታል የህክምና እርዳታውን ከማድረጉ በፊት ሃኪሞች በጉዳዩ ላይ እንዲመክሩ ማድረግ ግድ ሆኖበት ነበር።

የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ካሊድ ሳሌህ፤ መሰል አደጋ ከዚህ በፊት አጋጥሟቸው እንደማያውቅ እና የታዳጊውን ሕይወት ለመታደግ እና የቀዶ ህክምና ለማድረግ አምስት ሰፔሻሊስቶች እንዳስፈለጉ ተናግረዋል።

ከአምስት ቀናት በኋላ ግን ሙሃሙድ ተሽሎታል። አሁን ላይ አንገቱን ወደ ግራ እና ቀኝ ማዟዟር ባይችልም "በጣም ደህና ነኝ። የህመም ስሜት የለኝም" ይላል።

ሙሃሙድ ወደ መኖሪያ ቀዬው ለመመለስ ቢቸኩልም፤ ሃኪሞች ተጨማሪ ቀናቶችን በሆስፒታል ማሳለፍ እንዳለበት ነግረውታል።

"በቅርበት እየተከታተልነው ነው። በጥቂት ቀናት ውስጥ ከሆስፒታል ሊወጣ ይችላል። አሁን ላይ ግን ተጨማሪ ምርመራዎች እና ክትትሎች መደረግ አለባቸው" ይላሉ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ካሊድ።

ሙሃሙድ ያጋጠመው አደጋ የሚወደውን አሳ ማስገር እንደማያስቆመው ይናገራል።

"ወደፊት መጠንቀቅ ነው ያለብኝ። ኒድልፊሽ (ባለ ጦር አፍ አሳ) ብርሃን እንደማይወድ አውቃለሁ-ለዛም ነው ከውሃው ውስጥ በድንገት ወጥቶ የወጋኝ" ብሏል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ