ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር "አፍሪካ ትራምፕን ትወዳቸዋለች" ማለታቸው እያነጋገረ ነው

Patrice Motsepe ፓትሪስ ሞትሴፔ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ፓትሪስ ሞትሴፔ አፍሪካ ጥሩ ነገር ለመሥራት እርሳቸውን እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ፓትሪስ ሞትሴፔ ለአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካዊያን እንደሚወዷቸው ከተናገሩ በኋላ መነጋገሪያ ሆነዋል።

ባለሃብቱ ይህንን የተናገሩት በስዊትዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ሲሆን "አፍሪካ አሜሪካን ትወዳለች፤ አፍሪካ እርስዎን ትወዳለች፤ ጥሩ ነገር ለመስራት አሜሪካ ታስፈልገናለች" ሲሉ ነበር ለትራምፕ የነገሯቸው።

የ57 ዓመቱ ጎልማሳ ፓትሪስ ሞትሴፔ፤ በ2017 በወጣው ፎርብስ መፅሔት ላይ ምርጥ የንግድ ሰዎች ተብለው አብረው ከወጡት ትራምፕ ጋር ስለተገናኙ ክብር እንደሚሰማቸው ገልፀዋል።

ትራምፕም "ጥሩ ሥራ ነው የሠራኸው" ሲሉ ለባለሃብቱ ንግግር ምላሽ ሰጥተዋል። ይህንኑ የሚያሳው ቪዲዮም በትዊተር ተጋርቷል።

ንግግራቸውን ተከትሎም የተለያዩ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩ ነው። "ባለሃብቱ ፓትሪስ ሞትሴፔ ለራሳቸው የአፍሪካ ቃል አቀባይነትን ሚና ሰጥተው ነበር" ሲሉ በርካቶች ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

አንዳንዶቹ ደግሞ የባለሃብቱ አስተያየት የግላቸውና የራሳቸው ብቻ እንጅ አፍሪካዊያንን እንደማይወክል በመግለፅ ንግግራቸውን አጣጥለዋል።

ሌሎችም በበኩላቸው ባለሃብቱ ፕሬዚደንቱን ለማስደሰት በመፈለጋቸው ብቻ እዚያ በመገኘታቸው ብስጭት አዘል አስተያየት ሰጥተዋል። ንግግራቸው ለአሜሪካ ያላቸውን ክብር ለማሳየት የተጠቀሙት የንግድ እና የባህል አገላለፅ ነው ሲሉ የተከራከሩም አልታጡም።

በቅርቡ የተሠራ የሕዝብ አስተያየት መስፈሪያ (Opinion Poll) ፕሬዚደንት ትራምፕ በናይጀሪያና በኬንያ በሕዝብ የሚወደዱ እንደነበሩ ያመለክታል።

ፒው የተሰኘው የጥናት ማዕከል አብዛኞቹ የዓለም አገራት በትራምፕ ላይ ዝቅተኛ መተማመን እንዳላቸው ሲያሳዩ፤ ከኬንያ 65 በመቶ ከናይጀሪያ ደግሞ 58 በመቶ በጎ አስተያየት አግኝተዋል።

በትራምፕ የክስ ሂደት የተሰላቹ ሴናተሮች ሲጫወቱ እና ሲያንቀላፉ ታዩ

በዚሁ የሕዝብ አስተያየት ጥናት የተካተተችው ደቡብ አፍሪካ ደግሞ፤ በትራምፕ ላይ 42 በመቶ መተማመን እንዳላት አሳይታለች።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ምንም እንኳን አፍሪካን ጎብኝተው ባያውቁም፤ ልክ ውለታ እንደዋሉ ሰው አህጉሯን ወክለው አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ።

በአውሮፓዊያኑ 2018 አፍሪካዊያንን ለመግለፅ "ቆሻሻ" የሚል ቃል መጠቀማቸውን ተከትሎ ቁጣ ከተነሳ በኋላ በሰጡት መልስ "ዘረኛ" መባላቸውን ተቃውመዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አፍሪካውያንን፣ ሄይቲ እና ኤልሳልቫዶርን ለመግለፅ "ቆሻሻ" የሚለውን ቃል ከተጠቀሙና በኋላ ተቃውሞ ደርሶባቸው "ዘረኛ አይደለሁም" ሲሉ አስተባብለው ነበር።

የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዚደንት ትራምፕ ለዚህ ግልፅ ለሆነ ዘረኛ ንግግራቸው ይቅርታ እንዲጠይቁ ጠይቆ ነበር።

ይሁን እንጅ ትራምፕ ይህን ከተናገሩ በኋላ የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በንግግራቸው "ትራምፕን እወዳቸዋለሁ፤ ለአፍሪካዊያን እቅጩን ነው የነገሯቸው፤ በመሆኑም አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር መፍታት አለባቸው" ብለዋል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ በቅርቡም የ2019 የኖቤል ሰላም ሽልማት መውሰድ የነበረባቸው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆኑ እርሳቸው እንደነበሩ መናገራቸው ይታወሳል።

ባለፈው ዓመትም አራት የኮንግረንስ አባላትን "ወደ መጣችሁበትና የወንጀል መናሃሪያ ወደ ሆነችው አህጉራችሁ ተመለሱ" ብለው ነበር።

የኮንግረስ አባላቱ በሶማሊያ ከተወለደችው ኢልሃን ኦማር በስተቀር የተወለዱት በአሜሪካ ሲሆን ኢልሃን ህፃን ሳለች ነበር ወደ አሜሪካ ያቀናችው።