ጀርመን፡ ግለሰቡ የራሱን ስድስት የቤተሰብ አባላት ተኩሶ ገደለ

በሮት አም ዚ የሚገኘው ሕንፃ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ግድያው የተፈፀመው በሮት አም ዚ የባቡር ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኝ ሕንፃ ውስጥ ነው

በደቡብ ምዕራብ ጀርመን በምትገኘው ሮት አም ዚ ከተማ አንድ ግለሰብ ወላጆቹን ጨምሮ ስድስት የራሱን የቤተሰብ አባላት ተኩሶ መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የ26 ዓመቱ ተጠርጣሪ በምሳ ሰዓት ለፖሊስ ስልክ በመደወል በርካታ ሰዎችን መግደሉን ተናግሯል።

የጦር መሳሪያ የመያዝ ፈቃድ ያለው ግለሰቡ፤ ከሕንፃው ውጭ ቆሞ ፖሊስ እየተጠባበቀ ሳለ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የሦስት ወንዶችና ሦስት ሴቶች አስክሬንም በቤቱ ውስጥ ተገኝቷል። ሌሎች ሁለት ዘመዶቹም ጉዳት ያጋጠማቸው ሲሆን አንደኛቸው በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

ከ27 ዓመታት በኋላ ከ'ኮማ' የነቃችው ሴት

በሥራ ባልደረባው የተመረዘው ከዓመታት ጣር በኋላ ሕይወቱ አለፈ

ተጎጅዎቹ ዕድሜያቸው ከ36 እስከ 69 መሆኑንም የባደን ቪተንበርግ ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ እንዳለው ተጠርጣሪው ሁለት በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የቤተሰቡን አባላትም ሲያስፈራራ ነበር፤ ይሁን እንጅ ታዳጊዎቹ ጉዳት አልደረሰባቸውም።

ግድያው በቤተሰብ መካከል ከተፈጠረ አለመግባባት ጋር ሳይገናኝ እንደማይቀር ታምኗል።

ፖሊስ የግድያውን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ነው።

እስካሁን በግድያው የሌላ ሰው እጅ እንዳለበት የሚያሳይ ምንም የተገኘ ማስረጃ እንደሌለ ፖሊስ ገልጿል።

ግድያው የተፈፀመው ትናንት አመሻሹ ላይ ሲሆን በባህንሆፍስትራሴ በሚገኝ ሕንፃ ውስጥ የደቾች ምግብ ቤት ውስጥ ነው።

ቦታው ዝግ የተደረገ ሲሆን የወንጀል መርማሪዎች በቦታው ምርመራ እያካሄዱ ነው።

ሮት አም ዚ 5 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች የሚኖሩባት ትንሽ ከተማ ስትሆን በሰሜን ምስራቅ ስቱትጋርት ሽቬቢሽ ሃል ግዛት ትገኛለች።

'መንፈስ ቅዱስ' ከቅጣት የጋረደው አሽከርካሪ

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ