የዓለማችን ግዙፉ ባለሁለት ሞተር ቦይንግ አውሮፕላን የሙከራ በረራውን አደረገ

ቦይንግ 777 Image copyright AFP

ቦይንግ 777ኤክስ የተሰኘው የዓለማችን ግዙፉ ባለሁለት ሞተር አውሮፕላን የሙከራ በራራውን በድል አጠናቋል።

ቦይንግ የተሰኘው አውሮፕላን ፈብራኪ ድርጅት 737 ማክስ በተሰኙ አውሮፕላኖቹ ላይ በደረሰ እክል ምክንያት የሰው ሕይወት ከጠፋ በኋላ ገበያ ለማግኘት ሲዳክር ከርሟል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢንዶኔዢያ አቻው ንብረት የሆኑ ሁለት አውሮፕላኖች በወራት ልዩነት ተከስክሰው በድምሩ 346 ሰዎች ሞተዋል። ከአደጋዎቹ በኋላ የተቀሩትን 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ያገደው ቦይንግ እነሆ ግዙፍ አውሮፕላን ይዞ ብቅ ብሏል።

ለአራት ሰዓትታ የዘለቀው የሙከራ በረራ ሲያትል የተሰኘችው የአሜሪካ ከተማ አቅራቢያ ነው የተከወነው። የተሳካው በረራ ከመካሄዱ በፊት ሁለት ጊዜ በአየር ፀባይ ምክንያት በረራዎች እንዲቋረጡ ተደርገዋል።

252 ጫማ [76 ሜትር] የሚረዝመው አውሮፕላን የዓለማችን ግዙፉ ባለሁለት ሞተር የንግድ አውሮፕላን ነው ተብሎለታል።

ቦይንግ እስካሁን 309 777ኤክስ አውሮፕላኖች ሸጫለሁ የአንዱ ዋጋ ደግሞ 442 ሚሊዮን ዶላር ነው ብሏል። የድርጅቱ ግብይት ባለሙያ ዌንዲ ሶወርስ "ድርጅታችን ትልቅ ነገር ማድረግ እንደሚችል ያሳየ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

አውሮፕላኑ 360 ሰዎች የመጫን አቅም ካለው ኤርባስ ኤ350-1000 ጋር ተመሳሳይ ባሕሪ አለው ተብሏል።

ቦይንግ አደጋ የጠናባቸውን 737 ማክስ አውሮፕላኖች ሲያመርት ለደህንነት የሰጠው ዋጋ ዝቅ ያለ ነው ተብሎ ብዙ ወቀሳ ደርሶባታል። እንዳይበሩ የታገዱት አውሮፕላኖች እንደገና ተፈትሸው ወደ ሰማይ ይወጣሉ ሲል ድርጅቱ ማሳወቁ አይዘነጋም።

ማክስ 737 የቦይንግ እጅግ በብዛት የተሸጡ አውሮፕላኖች ሲሆን አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ በመተጋዳቸው ምክንያት ቦይንግ 9 ቢሊዮን ዶላር እንደከሰረ ይገመታል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ