አጥፍቶ ጠፊዎች በናይጄሪያ መስጂድ ላይ ጥቃት ፈጸሙ

ናይጄሪያ

በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ በሚገኝ አንድ መስጂድ ላይ የጠዋት ጸሎት (ሱብሂ ሰላት) በሚደረግበት ጊዜ አጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ጥቃት መፈጸማቸው ተዘገበ።

ጥቃቱ የተፈጸመው ትናንት እሑድ ሲሆን በሰሜናዊ ምሥራቅ ቦርኖ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ግዎዛ በተባለችው ከተማ ውስጥ በሚገኝ መስጂድ ላይ ነው።

ከጥቃቱ በኋላ የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት በጠዋቱ የጸሎት ሰዓት ወቅት በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች እንደሞቱ ቢገለጽም ሌሎች ግን ጥቃቱን ለመፈጸመ የሞከረው ግለሰብ ብቻ ሕይወቱ እንዳለፈ አመልክተዋል።

በኋላ ላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እንዳረጋገጡት በጥቃቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር አምስት ደርሷል።

ስለክስተቱና ስለደረሰው ጉዳት ባለሥልጣናት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

በጥቃቱ አካባቢ የነበሩ ምንጪች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አጥፍቶ ጠፊዎቹ በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወንድና ሴት መሆናቸውንንና መስጂዱንም ኢላማ ያደረጉት በጠዋቱ የጸሎት ሰዓት እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን ሁለቱም የጥቃቱ ፈጻሚዎች ሴቶች እንደሆኑ ተነግሯል።

አክለውም በጥቃቱ ከአጥፍቶ ጠፊዎቹ በተጨማሪ አንድ ታዳጊ ሲገደል በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውንም መስክረዋል። የእርዳታ ሰራተኞች እንዳረጋገጡት ዘጠኝ ሰዎች በጥቃቱ ቆስለው ህክምና እያገኙ ነው።

የአጥፍቶ ጠፊዎቹ ቦንብ የፈነዳው የጸሎት ሥነ ሥርዓት በሚካሄድበት በመስጂዱ ውስጥ እንደሆነ አንዳንድ ዘገባዎች ቢያመለክቱም ሌሎች ግን ፍንዳታው የተከሰተው ምዕመናኑ ጸሎታቸውን ጨርሰው ሲወጡ ከመስጂዱ ውጪ ነው ብለዋል።

እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ቡድን ባይኖርም ቦኮ ሐራም የተባለውና የአይኤስ ቡድን የምዕራብ አፍሪካ ክንፍ እንደሆኑ የሚናገሩ ቡድኖች በአካባቢው ጉልህ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ይታወቃል።

ባለፈው ወርም በአካባቢው አንድ ፓስተርን ጨምሮ ከ12 የሚበልጡ ክርስቲያኖች መገደላቸው ተዘግቧል።

እነዚህ ቡድኖች ቀደም ባሉ ጊዜታት በአብያተ ክርስቲያናትና በመስጂዶች ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችችን ገድለዋል።