የኮሮናቫይረስ ስጋትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ Image copyright Luke Dray

የኮሮናቫይረስ ስርጭት አሁንም የዓለም ስጋት ሆኖ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቫይረሱ ሊዛመትባቸው ይችላሉ ተብለው ከፍተኛ ስጋት ካለባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ለቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ያደረጋት ከቻይና ጋር ያላት ቀጥተኛ እና ከፍተኛ መጠን ያለው የተጓዥ ቁጥር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በረራ ባደረገ ቁጥር ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰራጭበትን አጋጣሚን ከፍ ያደርጋል የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች እንደቀጠሉ ናቸው።

ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በቻይና

በኮሮናቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩት ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ተነገረ

አየር መንገዱ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ መሰረዝ አለበት ብለው ከሚከራከሩት መካከል አንዱ የጤና ባለሙያው ዶ/ር የሺዋስ መኳንንት ይገኙበታል።

ዶ/ር የሺዋስ የበሽታውን ባህሪ እና የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በሽታው ወደ አገር ቢገባ የሚያስከትለው ኪሳራ በቀላሉ የሚተመን አይሆንም ይላሉ።

"ባለን የጤና ሥርዓት አይደለም ኮሮናቫይረስ፤ ቀላል የሚባሉ ወረርሽኞችን መቆጣጠር አቅቶናል" የሚሉት ዶ/ር የሺዋስ እንደማሳያነት ከዚህ ቀደም ድሬዳዋ አካባቢ ቺኩንጉኒያ የሚባል ወረርሺኝ ተነስቶ መሠረታዊ የሆኑ መድሃኒቶች እጥረት አጋጥሞ እንደነበረ ያስታውሳሉ።

"እኔ ድሬዳዋ ነው የምሰራው። ባለፈው ክረምት ላይ ቺኩንጉንያ የሚባል ቫይረስ ተከስቶ ፓራሲታሞል ጠፍቶ ታማሚዎችን ሆስፒታል አስተኝተን የሰውነት ሙቀት ስናወርድ የነበረው በውሃ በተነከረ ጨርቅ ነበር። ይህ የጤና ሥርዓት ኮሮናቫይረስን ይከላከላል ማለት ከባድ ነው" ይላሉ።

በቻይና የተከሰተው አዲስ ቫይረስ ምን ያህል አስጊ ነው?

ኮሮናቫይረስ፡ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

"የሙቀት መጠንን በመለካት በሽተኛን በትክክል መለየት አይቻልም። አንድ ሰው የበሽታውን ምልክት ሳያሳይ 14 ቀናት ሊቆይ ይችላል። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ሰዎች ከማንም ጋር ሳይገናኙ መቆየት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ግን ከማህብረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ነው የሚገኙት።

"አንድ ምልክቱን ያሳየ ሰው አክሱም ላይ አለ ሲባል በጣም ነው ያዘንኩት። ቫይረሱ እኮ በ 6 ጫማ [2 ሜትር ገደማ] ርቀት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል። ይህ ሰው አክሱም እስኪደርስ ከስንት ሰዎች ጋር ተገናኝቶ ይሆን?" ሲሉ ይጠይቃሉ ዶክትሩ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እስከ ጥር 24/2012 ድረስ 47,162 ተጓዦች በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሙቀት መለያ ምርመራ እንደተደረገላቸው እና ከእነዚህም ውስጥ 1,695ቱ የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አገራት መሆኑን አስታውቋል።

ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በሃገር ውሰጥ በሚቆዩበት ወቅት አድራሻቸው ተመዝግቦ ለአስራ አራት ቀናት ክትትል ይደረግባቸዋልም ተብሏል።

ክትትል ይደረግባቸዋል የተባሉት ከ1600 በላይ ሰዎች ወደ ማህብረሰቡ ተቀላቅለዋል።

ኮሮናቫይረስና የነዳጅ ዘይት ምን አገናኛቸው?

ኮሮናቫይረስ፡ የወቅቱ አሳሳቢው የዓለማችን የጤና ስጋት

ከእነዚህ መካከል በጣት የሚቆጠሩት ሰዎች እንኳ ቫይረሱ ቢኖርባቸው እስካሁን ባላቸው ቆይታ የሚገናኟቸው ሰዎችን እንዲሁም የተገናኟቸው ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊፈጥሩት የሚችሉትን ግነኙነት በማስላት ቫይረሱ በቀላሉ ሊሰራጭ እንደሚችል ስጋታቸውን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።

በቅርቡ አውስትራሊያ ከቻይና ዜጎቿን ማስወጣቷ ይታወሳል። አውስትራሊያ የሰውንት ሙቀት ለክታ ወደ አገር ከማስገባት ይልቅ፤ ከቻይና ተመላሽ ዜጎቿን ለ14 ቀናት ርቃ በምትገኝ ደሴት ላይ ለማቆየት ነው የወሰነችው።

የዩናትድ ኪንግደም መንግሥትም ከቻይና የተመለሱ እንግሊዛውያንን ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ስፍራ ለማቆየት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል።

ኢንስቲትዩቱ ግን ቫይረሱ ቢከሰት 4 ተርሸከርካሪዎች እና አራት የጤና ተቋማትን ጨምሮ በተጠንቀቅ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ቡድን መኖሩን አሳውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራተኞች ሰጋት

ወደ ቻይና የሚበሩ የኢትዮጵያ አየር መንግድ ሠራተኞች ለበሽታው ልንጋለጥ እንችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ ወደ ቻይና የበረሩ የበረራ አስተናጋጆች እና በሌላ የበረራ መስመር ላይ የበረሩ ካፒቴን፤ አየር መንገዱ ወደ ቻይና መብረሩ ለኮሮናቫይረስ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በቅርቡ ከአዲስ አበባ - ባንኮክ- ሆንግ ኮንግ - ባንኮክ - አዲስ አበባ የበረረች የበረራ አስተናጋጅ፤ እሷም ሆነች የሥራ ባልደረቦቿ በአሁኑ ወቅት ወደ ቻይና የመብረር ፍላጎት የለንም ትላለች።

"አሁን ባለው ሁኔታ ማንም ሰው ወደ ቻይና የመብረር ፍላጎት የለውም። ሥራችን ንክኪ የበዛበት ነው። ሰዎች የተጠቀሙትን ሶፍቶችን እና ማንኪያዎችን እንነካለን። ተቆጥበህ የምትርቀው ነገር አይደልም። ካለው ነገር አንጻር ማንም ሰው መሄድ አይፈልግም። ነገሩን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ወደ ቻይና ስንበር በተወሰኑ በረራዎች ላይ ጓንት እና የአፈ መተንፈሻ እንድናደርግ አይፈቀድም" ትላለች።

ካሜሮናዊው በኮሮናቫይረስ በመያዝ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ

አውስትራሊያ ከቻይና ተመላሾችን ራቅ ወዳለች ደሴት ማጓጓዝ ጀመረች

ቢቢሲ ያነጋገራት ሌላ የበረራ አስተናጋጅ እንደምትለው ከሆነ፤ ወደ ቻይና ከሚደረጉ በረራዎች መካከል ለቫይረሱ ስርጭት "አስጊ አይደለም" በሚባሉት ላይ ማስክ (አፍ መሸፈኛ) ማድረግ እንደማይፈቀድላቸው አስረድታለች።

እንደ የበረራ አስተናጋጆቹ ከሆነ፤ ምንም እንኳን የቫይረሱ ስጋት በሁሉም በረራዎች ላይ ያለ ቢሆንም የቫይረሱ ስርጭት "አስጊ አይደለም" ወደተባሉ ከተሞች ስንጓዝ ማስክ ማድረግ እንደማይፈቀድላቸው ይናገራሉ።

"እኔ የበረርኩበትን እንደምሳሌ ልንገርህ ከአዲስ-ባንኮክ ስንበር እንድናደርግ አልተፈቀደልንም። ከባንኮክ ወደ ሆንግ ኮንግ ስንበር ግን ማስክ እንድናደርግ ይፈቀዳል። ከሆንግ ኮንግ ወደ ባንኮክ ስንበር ማስክ አድርገን ነበር፤ መልሶ ደግሞ ከባንኮክ ወደ አዲስ አበባ ስንበር እንድናደርግ አልተፈቀደልንም" በማለት ታስረዳለች።

ከቻይና ውጪ የመጀመሪያው ግለሰብ በኮሮና ቫይረስ ሞተ

ቻይና አሜሪካን ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ ፍራቻ እየነዛች ነው ስትል ወነጀለች

የበረራ አስተናጋጆች በተመረጠ በረራ ላይ ብቻ ማስክ እንድናደርግ ተገደናል ከማለታቸው በተጨማሪ፤ አየር መንገዱ ለሠራተኞቹ በቂ የማስክ እቅርቦት እንደማያደርግ ይናገራሉ።

"ስለ ቫይረሱ አጠቃላይ መረጃ የያዘ ባለ ሦስት ገጽ ወረቀት ተሰጥቶናል። በቂ ማስክ ግን የለም" በማለት እርሷ እና ባልደረቦቿ አንድ ማስክ ሳይቀይሩ ለስድስት ተከታታይ በረራዎች ለመጠቀም መገደዳቸውን ትናገራለች።

በሌላ የበረራ መስመር ላይ የሚበር ካፒቴን እንደሚለው ከሆነ ደግሞ ቻይናን ከተቀረው አፍሪካ ጋር የሚያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። "እኔ ወደ ቻይና ባልበር እንኳ በርካታ ከቻይና የሚነሱ መንገደኞች በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና ወደ ተቀሩት መዳረሻዎች ይዘን እንበራለን። ይህ ስጋት አሳድሮብናል" ይላል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሠራተኞቹ ለተነሳውን ቅሬታ እና ስጋት ምላሽ እንዲሰጠ በተደጋጋሚ በስልክ እና በኢሜይል ጠይቀናል። አየር መንገዱ ለጥያቄያችን ምላሽ እንደሚሰጥ ቢናገርም እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

በበሽታው መስፋፋት ምክንያት በተፈጠረ ስጋት በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራዎች አቋርጠዋል። አብዛኞቹ አየር መንገዶች የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት ሲሆኑ አምስት የአፍሪካ አገራትም አየር መንገዶቻቸው ወደ ቻይና እንዳይጓዙ አድርገዋል።

ወረርሽኙ በፈጠረው ስጋትና ሌሎች አየር መንገዶች በወሰዱት እርማጃ ከበርካታ ኢትዮጵያዊያን ከአፍሪካ ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች እንዲያቆም ቢጠይቁም አየር መንገዱ አሁንም ሥራውን አላቋረጠም።

አምስት የአፍሪካ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ አቋረጡ

አየር መንገዱ ለቀረቡለት ጥሪዎች በሰጠው ምላሽ ላይ ምንም እንኳን በርካታ መንገደኞችን ከቻይና ቢያጓጉዝም አብዛኞቹ ወደ ተለያዩ አገራት ትራንዚት የሚያደርጉ መሆናቸውን አመልክቷል።

በተጨማሪም መንገደኞች ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ በሌሎች አየር መንገዶች አማካይነት እንደሚገቡ፣ አየር መንገዱ የስታር አልያንስ አባል በመሆኑ ከሌሎች አየር መንገዶች የቻይና መንገደኞችን እንደሚያጓጉዝ በመጥቀስ "አየር መንገዱ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ቢያቆምም ባያቆምም መንገደኞች መምጣታቸው ስለማይቀር ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ ስጋት መቀጠሉ አይቀርም" ብሏል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ