በሽታውን ለመደበቅ ባለስልጣናት ዶክተሮችን ያስፈራሩ ነበር

ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ Image copyright WEIBO
አጭር የምስል መግለጫ ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ

በጥር ወር መጀመሪያ ላይ የኮሮናቫይረስ በዋናነት የተቀሰቀሰባት የዉሃን ከተማ ባለስልጣናት ስለበሽታው መከሰት የሚያመለክቱ መረጃዎችን ለመሸፋፈን ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

የበሽታውን መከሰት በተመለከተ ለሰዎች በመንገር እንዲጠነቀቁ ሲመክር የነበረ አንድ ዶክትርን ፖሊሶች ቤቱ ድረስ መጥተው ከድርጊቱ እንዲቆጠብ አስጠንቅቀውት ነበር።

ነገር ግን ከአንድ ወር በኋላ በሽታው በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ዓለምን ማስጨነቅ ሲጀምርና ሐኪሙ ምን ተብሎ እንደነበረ ሃኪም ቤት ተኝቶ ታሪኩን ይፋ ሲያደርግ ጀግና ተብሎ እየተወደሰ ነው።

ስለአዲሱ ኮሮና ቫይረስ ማወቅ የሚገባዎ ነጥቦች

የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች ኮሮና ቫይረስን 'ሊያመርቱ' ነው

"ጤና ይስጥልኝ፤ ሊ ዌንሊያንግ እባላለሁ፣ በዉሃን ማዕከላዊ ሆስፒታል የዓይን ሃኪም ነኝ" በማላት ይጀምራል የዶክተሩ መልዕክት።

ዶክተሩ ይፋ ያደረገው መልዕክት የኮሮናቫይረስ በተከሰተባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ዉሃን ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት በሽታውን ለመሸፋፈን ያደረጉትን ጥረት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ተብሏል።

ታህሳስ ወር ላይ ወረርሽኙ በተከሰተበት ማዕከል ውስጥ ይሰራ የነበረው ዶክተር ሊ በአንድ እንግዳ ቫይረስ ተጠቅተው የመጡ ሰባት ሰዎችን አግኝቶ ነበር፤ እሱም በሽታው ከ15 ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ የነበረው 'ሳርስ' ነው ብሎ ገምቶ ነር።

እነዚህ የበሽታው ክስተቶች ሁናን ተብሎ ከሚጠራው የባሕር ውስጥ ምግቦች መሸጫ ገበያ የተከሰተ እንደሆነ ስለታሰበ ህሙማኑ ከሌሎች ተለይተው በሆስፒታሉ ክትትልና ህክምና እንዲያገኙ ውስጥ ተደረገ።

ኮሮናቫይረስ በመላዋ ቻይና መዛመቱ ተነገረ፤ የሟቾችም ቁጥር እየጨመረ ነው

ቻይና አሜሪካን ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ ፍራቻ እየነዛች ነው ስትል ወነጀለች

እንደ አውሮፓዊያኑ ታህሳስ 30 ላይ ዶክተሩ በአንድ የቡድን መልዕክት መለዋወጫ መድረክ ላይ ለሙያ አጋሮቹ ዶክተሮች ስለወረርሽኙ መከሰትና እራሳቸውን ለመጠበቅ የመከላከያ አልባሳትን እንዲጠቀሙ የሚመክር መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

በዚያ ወቅት ዶክትር ሊ ያላወቀው ነገር ቢኖር የወረርሽኙ ምክንያት የሆነው ተህዋስ በኋላ ላይ እንደተደረሰበት ፍጹም አዲስ አይነት የኮሮናቫይረስ እንደሆነ ነበር።

ከአራት ቀናት በኋላ ከሕዝብ ደህንንት ቢሮ ባለስልጣናት መጥተው አንድ ደብዳቤ ላይ እንዲፈርም ነገሩት። ወረቀቱም ዶክተሩን "ሐሰተኛ አስተያየቶችን በመስጠት" ይህም "በከፍተኛ ሁኔታ ማኅበራዊ ሥርዓትን የሚያናጋ" መሆኑን በመግለጽ ጥፋተኛ አድርጎ የሚከስ ነበር።

Image copyright LI WENLIANG
አጭር የምስል መግለጫ ለዶክተሩ የተጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ

"በጥብቅ የምናሳስብህ ነገር ቢኖር፡ በዚህ ድርጊትህ በግትርነት የምትገፋ ከሆነና ሕግን ባለማክበር በሕገወጥ ተግባርህ የምትቀጥል ከሆነ ለፍርድ ትቀርባለህ። ገብቶሃል?" ይላል የቀረበለት ወረቀት። ከስርም ዶክተር ሊ በእጅ ጽሑፉ "አዎ፤ ተረድቻለሁ" የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል።

"ሐሰተኛ አሉቧልታዎችን በማሰራጨት" በሚል ተጠርጥረው ምርመራ ከተደረገባቸው ስምንት ሰዎች ዶክተሩ አንዱ ነው።

በጥር ወር ማብቂያ ላይም ዶክተር ሊ ከባለስልጣናት የተሰጠውን የዚህን ደብዳቤ ቅጂ 'ዌቦ' በተባለው የቻይናዊያን ማህበራዊ የትስስር መድረክ ላይ በማውጣት ምን አጋጥሞት እንደነበረ ይፋ አደረገ።

ይህንን ተከትሎም የአካባቢው ባለስልጣናት የበሽታው ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ በኋላ ዶክተሩን ይቅርታ ቢጠይቁትም፤ ይቀርታው የዘገየ ነበር።

በጥር ወር መጀመሪያ ሳምንታት ላይ ዉሃን ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች በሽታው ካለባቸው እንስሳት ጋር የቀረበ ንክኪ ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ በመግለጻቸው፤ ሐኪሞችን ለመከላከል ምንም መመሪያ አልተሰጠም ነበር።

ቻይና ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን በስምንት ቀናት ሆስፒታል ገነባች

ቻይና በ 6 ቀናት ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል ልትገነባ ነው

ፖሊሶች ዶክትር ሊን ካናገሩት ከሳምንት በኋላ አንዲት የግላኮማ ችግር ያለባትን ሴት እያከመ ነበር። ታካሚዋም አዲሱ የኮሮናቫይረስ እንዳለባት አላወቀም።

ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ ዶክትር ሊ በጥር ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ ሳል እንደጀመረው፣ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ትኩሳት እንዳጋጠመውና ከሁለት ቀናት በኋላም ብሶበት ሆስፒታል እንደገባ ገልጿል። ቤተሰቦቹም መታመማቸውንና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውንም አመልክቷል።

ዶክትር ሊ ላይ የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት ከታየ ከ10 ቀናት በኋላ ቻይና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን አወጀች።

ዶክትር ሊ እንዳለው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በተደጋጋሚ ቢደረግለትም የተገኘው ውጤት ግን ነጻ እንደሆነ ነበር። ነገር ግን በጥር ወር መጨረሻ ላይ የተደረገለት ምርመራ በበሽታው መያዙን አመለከተ።

ይህንንም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ በማድረጉ አድናቆትና ድጋፍን ከበርካታ ሰዎች አግኝቷል።

"ዶክተር ሊ ጀግና ነው" ያለው አንድ ግለሰብ አገሩ ስላለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ጠቅሶ "በዚህ ሁኔታ ወደፊት የወረርሽኝ ምልክቶችን ያዩ ሐኪሞች ቀድመው ለማሳወቅ ፍርሃት ሊያድርባቸው እንደሚችል" አስተያየቱን ሰጥቷል።

አክሎም "ለሕዝብ ጤና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን ለመፍጠርም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሊ አይነት ሐኪሞች ያስፈልጋሉ" ሲል የዶክተሩን ድርጊት አወድሷል።