በሊል ዋይን ናይጄሪያዊ የዘር መሰረት ናይጄሪያውያን ደስታቸውን እየገለፁ ነው

የፎቶው ባለመብት, Jeff Schear
ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር ሊል ዋይን የዘር መሰረቱን ለማወቅ ባደረገው ምርመራ ናይጄሪያዊ መሆኑን ተከትሎ ናይጄሪያውያን ደስታቸውን እየገለፁ ነው፤ ባለስልጣናቱም ዜናውን በደስታ ተቀብለውታል።
ውጤቱ ከተገለፀው በኋላ የናይጄሪያ ዲያስፖራ ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቢኬ ዳቢሬ ሊል ዋይንን "ናይጄሪያዊ ወንድማችን" ብለውታል።
ኮሚሽነሯም አክለው ሊል ዋይንን ወደ ናይጄሪያ ሲመጣ አቀባበል እንዲሚያደርጉለት ገልፀዋል።
የዘር መሰረቱን ለማወቅ ምርመራ ያደረገው ሊል ዋይን ሪቮልት ለተባለ ቴሌቪዥን ጣቢያ 53 በመቶ ናይጄሪያዊ መሆኑንና አገሪቱን የመጎብኘት እቅድ እንዳለው ተናግሯል።
ናይጄሪያውያንም ደስታቸውን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችም እየገለፁ ነው።
"ሊል ዋይን 53 በመቶ ናይጄሪያዊ ነው? ወንድሜ እንደሆነ ሁልጊዜም ይሰማኝ ነበር። ስኑፕ ዶግና ፊፊቲ ሴንትም ናይጄሪያዊ ሳይሆኑ አይቀሩም" በማለት ኢሆማ የተባለ ግለሰብ በትዊተር ገፁ አስፍሯል።
"የውጭ አገር ታዋቂ ሰዎች ናይጄሪያዊ ነን የሚሉበት ሁኔታ ይገርማል፤ እኛ የማናየው ነገር ይታያቸዋል መሰለኝ" በማለት ሪድባብሎ አስተያየቱን ገልጿል።
"ሊል ዋይን 53 በመቶ ናይጄሪያዊ ነው፤ ከመጀመሪያው ታውቆኛል እንዲያውም የኢቦ ብሔር ነው" በማለት ሌላኛዋ በትዊተር ገጿ ጽፋለች።