አፍሪካ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል አቅሙ አላት?

አፍሪካዊት እናት Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አፍሪካዊት እናት

ቻይና ሁቤይ ግዛት የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም ጭንቀትን ፈጥሯል። ቫይረሱ በርካታ የዓለማችን አካባቢዎችን በአጭር ጊዜ ማዳረሱና ለጊዜው ፈዋሽ መድሃኒት ያልተገኘለት መሆኑ ደግሞ አሳሳቢነቱን ከፍ አድርጎታል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ ቫይረሱ ካልተገኘባቸው ሁለት አህጉራት መካከል አፍሪካ አንዷ ብትሆንም ባለሞያዎች ግን ይህ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም እያሉ ነው።

ቫይረሱ በዉሃን ከተማ ከተከሰተ ጀምሮ ቢያንስ 600 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በበሽታው መጠቃታቸው ታውቋል። ከሟቾቹም ሆነ በበሽታው ከተያዙት ውስጥ ላቅ ያለውን ድርሻ የሚይዙት ቻይናዊያን ናቸው።

ባለፈው ሳምንት የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስን የዓለም ከፍተኛ ስጋት ነው ብሎታል። ይህ ዓይነቱ ውሳኔ በድርጅቱ የሚወሰነው በጣም ኣሳሳቢ ጉዳይ ሲከሰት ሲሆን ይህም በታሪክ ለስድስተኛ ጊዜ የሆነ ነው።

እስካሁን አፍሪካ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው አገራት ባይኖሩም ዋናው ጥያቄ ግን አፍሪካዊያን አሁን በአህጉሩ ያሉትን ህሙማን በአግባቡ ማከም በማይችሉበት ደረጃ ላይ እያሉ ኮሮናቫይረስ ቢጨመር ምን ይሆናሉ የሚለው ነው።

አሁን በሽታው አፍሪካ ውስጥ ቢከሰት ህክምናውን ለማድረግ ምን የተሟላ ነገር አለ?

እስከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ድረስ በአፍሪካ ቫይረሱን ለመለየት የነበሩት ቤተ ሙከራዎች ሁለት ብቻ ናቸው። አንዱ ደቡብ አፍሪካ፤ ሌላኛው ደግሞ ሴኔጋል የሚገኙ ናቸው። ሌሎች የአህጉሪቱ አገራትም ናሙናዎቻቸውን ወደ እነዚህ አገራት በመላክ ነው የቫይረሱን ውጤት ሲያረጋግጡ የነበሩት።

በዚህ ሳምንት ደግሞ ጋና፣ ማዳጋስከር፣ ናይጄሪያና ሴራሊዮን ይህንን የቤተ ሙከራ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ለኮሮና ቫይረስ የአፍሪካ ዝግጅት

የዓለም ጤና ድርጅትም በአህጉሩ ያሉ 29 ቤተ ሙከራዎች ቫይረሱን መለየት እንዲችሉ ድጋፍ ለማድረግ አጋዥ ቁሳቁስ የላከ ሲሆን አስፈላጊም ከሆነ ከሌሎች አገራት ተጨማሪ የድጋፍ ቁሳቁሶችን ለማምጣትም ዝግጁ ነኝ ብሏል።

በመቀጠልም በዚህ ወር መጨረሻ ቢያንስ 36 የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስን ለመለየት የሚያስችል ቤተ ሙከራ ይኖራቸዋል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

አገራት የወሰዱት ርምጃ

የናይጄሪያ የቀይ መስቀል ማኅበር 1 ሚሊዮን የበጎ አድራጎት ሠራተኞችን በተጠንቀቅ አዘጋጅቻለሁ ብሏል። ይህም በማንኛውም ወቅት የኮሮናቫይረስ በናይጄሪያ ምድር ተከሰተ ቢባል ተረባርበን ለመቆጣጠር ያስችለናል ብሏል።

የታንዛኒያ የጤና ሚንስቴር የለይቶ ማቆያ አካባቢዎችን በምሥራቅ፣ በሰሜንና ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች አዘጋጅቷል። የሙቀት መጠን መለኪያ በበቂ ሁኔታ ያሟላ ሲሆን ቫይረሱን መከላከል አመቺ በሆነ መልኩ የሰለጠኑ 2 ሺህ የጤና ባለሞያዎችም ዝግጁ ተደርገዋል።

የኡጋንዳ የጤና ሚንስቴር ከቻይና የመጡ ከ100 በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው እስኪረጋጥ ድረስ ለብቻቸው እንዲቆዩ አድርጓል። ከፊሎቹ በሁለት ሆስፒታሎች እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ ከማንም ጋር ሳይገናኙ በቤታቸው እንዲያሳልፉ ተርጓል።

ከኢቦላ የተወሰደ ተሞክሮ ይኖር ይሆን?

ዶክተር ሚካኤል ያኦ በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ድንገተኛ ህክምና ክፍል ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የኢቦላ ቫይረስ ከ2014 እ.አ.አ ጀምሮ በምዕራብ አፍሪካና አሁን በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተ ቢሆንም ያስገኘው ተሞክሮ እምብዛም ነው።

"ኮሮና ቫይረስ አፍሪካ ውስጥ ቢገባ ጉዳቱ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል" በማለትም ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

"አገራትን የምንመክረው ቢያንስ ቫይረሱ ከመሰራጨቱ በፊት ከፍተኛ የሆነ የመለየት ሥራ ላይ እንዲረባረቡ ነው" ብለዋል ኃላፊው።

በርካታ የአፍሪካ አገራት አየር ማረፊያቸው ላይ ተጓዦች እንደደረሱ የኢቦላ ምርመራ ያደርጋሉ። የኢቦላ ቫይረስ የተከሰተባቸው አገራትም እስካሁን የለይቶ ማቆያ ቦታዎች አሏቸው። በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከምም የሕክምና አሰጣጥ ብቃታቸውን አሳድገዋል።

ነገር ግን አስቸጋሪው ነገር ኢቦላ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው የበሽታው ምልክት ከታየ በኋላ ሲሆን በሌላ በኩል ኮሮናቫይረስ ምንም ምልክት ሳያሳይ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል። ይህም ከአፍሪካ ደካማ የጤና ሥርዓት ጋር ተዳምሮ የስርጭቱንና የቁጥጥር ሂደቱን ፈታኝ ያደርገዋል።

በአፍሪካና በቻይና መካከል የሚደረገው ጉዞስ ለቫይረሱ ስርጭት ምን አስተዋጽዖ አለው?

የአፍሪካና የቻይና የተጠናከረ የንግድ ልውውጥ ቫይረሱን ያሰራጨዋል ተብሎ ከሚፈራባቸው መንገዶች ቀዳሚው ነው።

ቻይና የአፍሪካ ትልቅ የንግድ ሸሪኳ ስትሆን ከ10 ሺህ በላይ የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪካ በተለያዩ ዘርፎች እየሰሩ ይገኛሉ። ከ1 ሚሊዮን በላይ ቻይናዊያንም አፍሪካ ውስጥ በተለያዩ አገራት ይኖራሉ።

ይህም የቻይናንና የአፍሪካን የገዘፈ ቁርኝት ያሳያል። ነገር ግን በእንደዚህ አይነቱ አስቸጋሪ ወቅት ሌላ ጣጣ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

ጋርዲያን ባወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ ከ80 ሺህ በላይ የአፍሪካ ተማሪዎች በቻይና የተለያዩ ግዛቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። በተመሳሳይ የቻይና ተማሪዎችም ወደ አፍሪካ ይመጣሉ።

የ21 ዓመቱ ካሜሩናዊ ተማሪ በቻይና በነበረው ቆይታ በቫይረሱ ተይዟል ተብሎ በመጠርጠሩ በሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት ይገኛል።

በእስያ ያለው ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴና በአየር ትራንስፖርት ምክንያት የተከሰተ ነው የሚሉት የዘርፉ ሙያተኞች ለአፍሪካም ይህ ተጨማሪ ስጋት እንደሚደቅን ያስረዳሉ።

በ2002 እ.አ.አ በቻይና የተከሰተው የሳርስ ቫይረስ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተገኘ አንድ የቫይረሱ ተጠቂ ግለሰብ ምክንያት፤ ቫይረሱ በአህጉሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። በዚያን ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ደግሞ አሁን በቻይናና በአፍሪካ መካከል ያለው የአየር ትራንስፖርት በ600 በመቶ ጨምሯል።

Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ የሙቀት መጠን አየር መንገድ ላይ ሲለካ

በርካታ የዓለም አገራት አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን ጉዞ አቋርጠዋል። በአፍሪካም ተመሳሳይ ሥራ እርምጃ እንዲወሰድ ሕዝቡ ጫና እያደረገ ነው።

ሩዋንዳና ኬንያ የአየር ጉዟቸውን ያቋረጡ የአፍሪካ አገራት ናቸው። ነገር ግን የአህጉሪቱ ግዙፍ አየር መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ያላቋረጠ በመሆኑ የአፍሪካዊያን ስጋት ብዙም አልተቀነሰም።

የዓለም ጤና ድርጅት በተለይ ከቻይና ጋር ሰፊ ግንኙነት አላቸው ያለቸውን 13 አገራት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል በማለት ለይቷል። እነዚህ አገራት ኮሮናቫይረስን የማስተናገድ እድላቸው ሰፊ ነው በመባል ነው የተለዩት። ለእነዚህ አገራትም የተለየ እገዛ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያላቸው አገራት የሚከተሉት ናቸው።

 • አልጄሪያ
 • አንጎላ
 • ዴሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኦፈ ኮንጎ
 • ኢትዮጵያ
 • ጋና
 • አይቮሪ ኮስት
 • ኬንያ
 • ሞሪሽየስ
 • ናይጄሪያ
 • ደቡብ አፍሪካ
 • ታንዛኒያ
 • ኡጋንዳ
 • ዛምቢያ

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ