ህንድ፡ አልኮል በቧንቸው የመጣላቸው ነዋሪዎች በድንጋጤ ላይ ናቸው

በመጠጥ የተሞላው ቧንቧ Image copyright Joshy Maliyekkal

በህንዷ ግዛት ኬራላ ሰሞኑን አንድ አስደናቂ ጉዳይ ተከስቷል።

በአንድ የጋራ መኖሪያ ህንፃ የሚኖሩ ነዋሪዎች የቤታቸውን ቧንቧ በሚከፍቱበት ወቅት ቢራ፣ ብራንዲና ሌሎች መጠጦች ጋር የተቀላቀለ የአልኮል መጠጥ መፍሰስ ጀመረ።

የሚሰነፍጥ ሽታ ያለው ቅልቅሉ ቡናማ ቀለም ያለው ሲሆን በህንፃው ማዕድ ቤቶች ባለው ቧንቧ በኩልም ነው የመጣው ተብሏል።

በዚህ ሁኔታ የተደናገጡት ነዋሪዎች የአካባቢውን ባለስልጣናት ስለ ሁኔታው ያሳወቁ ሲሆን፤ ውሃቸውም በድንገት ከአልኮል ጋር መቀላቀሉን ተረድተዋል።

በህንድ ግማሽ ብርጭቆ ውሃ እየተሸጠ ነው

የውሃ እጥረት ዋነኛው የዓለማችን ስጋት

እንዴት ሊቀላቀል ቻለ? ነገሩ እንዲህ ነው

ስድስት ሺ ሊትር የሚሆን ህገ ወጥ የአልኮል መጠጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በጋራ መኖሪያ ቤቱ አካባቢ በሚገኝ ጉድጓድ ተቀምጦ ነበር።

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት በቁጥጥር ስር የዋለው መጠጥ በመሬትም ስር ፈሶ ለትሪሱር ግዛት የመጠጥ ውሃ የሚያቀርበው የውሃ ጉድጓድ ላይ መቀላቀሉ ታውቋል።

በዚህም የውሃ መጠጥ ጉድጓድም አስራ ስምንት የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ይጠቀሙበታል ተብሏል።

"በጣም ነው የደነገጥነው" በማለት ጆሺ ማልይካል የተባለ ነዋሪ ለቢቢሲ ሂንዲ ተናግሯል።

ኢትዮጵያውያን፡ የአስወጡን ድምጽ በጎሉባት የቻይናዋ ዉሃን

መፀዳጃ ቤት ማግኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሆነባት አፍሪካዊት ሃገር

እንደ እድል ሆኖ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰነፍጠው የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት ቢያግዳቸውም፤ ለመጠጥም ሆነ ለመታጠቢያ የሚሆን ውሃ ተቸግረዋል።

"በውሃ ችግር ምክንያት ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም፤ ከስራም ቀርተናል" ብሏል ጆሺ ማልይካል

Image copyright Joshy Maliyekkal

ነዋሪዎቹ ሁኔታውን ካስረዱ በኋላ ባለስልጣናቱ ስህተታቸውን ለማስተካከል ሞክረዋል።

ነገር ግን የውሃ ጉድጓዱን በደንብ ለማፅዳት አንድ ወር እንደሚወስድ ነዋሪዎቹም ገልፀዋል፤ ይህም ሁኔታ ነዋሪውን ባለስልጣናቱ እየቀዱ በሚያመጡት ውሃ እንዲወሰኑ አስገድዷቸዋል።

"በየቀኑ አምስት ሺ ሊትር የሚሆን ውሃ እየቀዱ ቢያመጡም በህንፃዎቹ ለሚኖሩ ቤተሰቦች በሙሉ በቂ ሆኖ አላገኘነውም" ብለዋል ጆሺ ማልይካል

የአካባቢው ባለስልጣናት ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምንም አይነት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የኬራላ ግዛት በአገሪቱ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ አልኮልን በሚወስዱ ነዋሪዎቿ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።