''ባልሽን በጥንቆላ አሳብደሸል አሉኝ፤ እኔ ግን እስካሁን ከጎኑ አልተለየሁም''

ኤስተር

ኤስተር ኪያማ በኬንያዋ 'ንዬሪ' ከተማ በመምህርነት በመስራት ላይ ሳለች ነበር ያልጠበቀችውን ዜና በስልክ የሰማችው።

ባለቤቷ ዴቪድ መታመሙን ደዋዩ ከነገራት በኋላ የአእምሮ ህመም እንደሆነ አስረዳት።

በጎርጎሳውያኑ 2005 ኤስተር ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ባለቤቷን አልተመለከተችውም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ አንድ የንግድ ስራ ለማከናወን በሚል ወደሌላ ከተማ በመሄዱ ነው።

እሷ ልታገኘው በሄደችባቸው ጊዜያት በሙሉ ምንም አይነት ህመም አላስተዋለችም ። ነገር ግን አንዴ መታመሙን በሰማች ጊዜ ሳታቅማማ ወዳለበት ቦታ መሄዷን ታስታውሳለች።

''ቤት ውስጥ ብቻውን ያወራ ነበር፤ እጆቹን እያወናጨፈ በተመስጦ ሃሳቡን ያብራራል። ምንም እንኳን ብቻውን ቢሆንም የሚያወራው፤ አጠገቡ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው እንደሚያዳምጡት ነበር የሚያስበው።''

'ቅሽለት' ስለሚባለው የአእምሮ ጤና ችግር ያውቃሉ?

የአልኮል ችግር ያለባቸው ወንዶች ጥቃት የመፈጸም እድላቸው ከፍ ያለ ነው

የኤስተር ባለቤት ወደ ህክምና ቦታ ከተወሰደ በኋላ 'ባይፖላር ዲስኦርደር' የሚባል የአእምሮ እክል እንደዳጋጠመው ተደረሰበት።

'' ወደቤት ሲመለስ እንደውም ጭራሽ ባሰበት። እቤት ውስጥ ትቼው ከሄድኩኝ በጣም ነው የምሳቀቀው። አንድ ቀን ትቼው ሄጄ ስመለስ የቤቱን ጣራ አቃጥሎት ደረስኩኝ።''

ኤስተር ለረጅም ዓመታት የምታውቀው ባለቤቷ የማታውቀው ሰው ሲሆንባት ምን እንደምታደርግ ግራ ገባት። እየሆነ ያለውን ነገር ለመረዳትም እጅግ አስቸጋሪ ሆኖባት ነበር።

በቃ የፈጀውን ይፍጅ ብላ ወደህክምና ቦታ ለመውሰድ ስትሞክር ግን የባለቤቷ ቤተሰቦች ይከለክሏታል። እንደውም ልጃችንን 'በመተት' ያሳበድሽው አንቺ ነሽ ብለው ይወነጅሏት ጀመሩ።

''አባቱ መጥተው ሊወስዱት እንደሆነ ነገሩኝ። 'ልጄን በጥንቆላ ያሳበድሽው አንቺ ነሽ፤' ሲሉኝ በጣም ደነገጥኩ።

ለ 15 ዓመታት በትዳር አብሯት ከቆየው ግለሰብ በእንደዚህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታ መለየት ቢከብዳትም ከእሷ በበለጠ እጅግ አስቸጋሪ የነበረው በትዳራቸው ያፈሯቸው ልጆች ነበሩ።

ዴቪድ ወደቤተሰቦቹ ቤት ከሄደ በኋላ የጤናው ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየባሰበት መምጣት ጀመረ። ነገር ግን ቤተሰቦቹ ጤናው የታወከው 'በጥንቆላ' ምክንያት ነው ብለው ስላመኑ ወደ ህክምና ቦታ ለመውሰድ አልፈቀዱም።

በኬንያ በርካታ የጤና እክሎች ከጥንቆላ እና ከእርግማን ጋር የተገናኙ እንደሆነ ማህበረሰቡ ያምናል። ምንም እንኳን እነዚህ የጤና እክሎች በቀላል ህክምና መዳን የሚችሉ ቢሆኑም ታማሚዎች ከሰው ተደብቀው በቤት ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋሉ።

የኬንያ ጤና ሚኒስትር እንደሚለው በርካታ ኬንያውያን የጤና እክል ሲያጋጥማቸው ባለሙያዎች ጋር ሄዶ ከመታከም ይልቅ ባህላዊ ህክምናዎችን ይመርጣሉ።

Image copyright Esther Kiama

የኤስተር ባለቤት ለሶስት ዓመታት ከቤተሰቦቹ ጋር የቆየ ሲሆን በተለይ ደግሞ በእድሜ ለገፉት እናቱ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር።

ልጃቸው አቅሉን ስቶ መመልከት የከበዳቸው እናት እሳቸውም ታመው ነበር።

አንዳንድ ጊዜ የቤተሰቦቹ ጎረቤቶች ወደ ኤስተር በመደወል ስለባለቤቷ ሁኔታ ይነግሯታል።

'' አንዳንድ ጊዜ ደውለው በመንገድ ላይ እየጮኸ እንደሆነ ይነገሩኛል፤ ወዲያው ሄጄ መኪና እከራይና ወደ ቤተሰቦቹ ቤት እመልሰዋለው። አንዳንድ ጊዜም ጥሩ ምግብ ሰርቼ አበላዋለው።''

ምንም እንኳን ባለቤቷ ጤናው እንዲመለስ የቻለችውን ሁሉ ብታደርግም ተወቃሽ ከመሆን ግን አላመለጠችም። እንደውም ባለቤቷም ጭምር ጥፋተኛ አድርጎ ቆጠራት።

ማልቀስ ጠቃሚ ነው ወይስ ጎጂ?

''አንድ ቀን ቆንጨራ ይዞ 'አንቺ ነሽ በጥንቆላ ያሳበድሽኝ' እያለ አባረረኝ። እንደምንም ብዬ አረጋጋሁትና እኔን ከገደልከኝ ማን ምግብህን ያበስልልሀል? ስለው ቆንጨራውን ወርውሮት ሄደ።''

ምንም እንኳን ዘመዶቿና ጓደኞቿ ባለቤቷን እንድተረሳው ቢነግሯትም፤ እሷ ግን አሻፈረን ብላ ቆይታለች።

'' ስንጋባ የገባነው ቃል አለ፤ መቼም ቢሆን ከአንዱ ጎን ላለመለየት። ገና ወጣቶች እያለን ነበር ትዳር የመሰርተነው። እውነቱን ለመናገር በጣም ነበር የምንዋደደው። አራት ልጆችንም አፍርተናል።''

ከሶስት ዓመታት በኋላ ኤስተርና ልጆቿ ከአእምሮ ጤና ባለሙያ ጋር በመሆን ዴቪድን ከቤተሰቦቹ ለመውሰድ ወሰኑ። ሰርቀው ለማምጣትም ተስማሙ።

'' ቤተሰቦቹ ሳይሰሙ ወደ እኛ ቤት ስናመጣው የእጅና የእግር ጥፍሮቹ በጣም አድገውና ቆሽሸው ነበር። እሱን ለማጽዳት ቀናት ነበር የፈጀብን። ጺሙም ቢሆን በጣም አድጎ ስለነበር አስፈሪ ገጽቶ ሰጥቶታል።''

በአሁኑ ሰአት ዴቪድ በሆስፒታል ህክምናውን እየተከታተለ ሲሆን ሁለተኛ ወሩን አስቆጥሯል። ቤተሰቡም በመጨረሻ አንድ ላይ ለመሆን በቅቷል።