‘በአስራ አራት አመቴ የተደፈርኩበት ቪዲዮ 'በፖርን' ድረገፅ ላይ ነበር'

ሮዝ ካሌምባ Image copyright Rose Kalemba

ሮዝ ካሌምባ በአስራ አራት አመቷ የተደፈረች ሲሆን ይህ ቪዲዮ ታዋቂ የወሲብ ፊልም ድረገፅ ላይ ይኖራል ብላ በህልሟም አላለመችም። ያላሰበችው ሆነና በታዋቂ የወሲብ ፊልም ድረ ገፅ ላይ የመደፈሯን ስቃይ የሚያሳይ ቪዲዮ ለተመልካቹ ይፋ ሆነ።

ይህ ቪዲዮ ከድረ ገፁ እንዲጠፋ ብዙ ትግል አድርጋለች፤ ይህንንም ተስፋ አስቆራጭ ትግል በፅሁፏ አስፍራለች።

ፅሁፏ ከወጣም በኋላ ብዙዎች በተመሰሳይ መንገድ የተደፈሩበት ተንቀሳቃሽ ምስል በወሲብ ፊልም ድረገፅ ላይ እንደተቀመጠና እንዲወርድ ለማድረግ እንዳልቻሉ አጋርተዋታል።

የአስገድዶ መደፈር ክሷን ለመከታተል የሄደችው ወጣት በእሳት ተቃጠለች

የተነጠቀ ልጅነት

ማስጠንቀቂያ፦ ታሪኩ ጭካኔ የተሞላበት ወሲባዊ ጥቃት አለበት

ሮዝ በተኛችበት ሆስፒታል ውስጥ የምታስታምማት ነርስ ቀና ብላ አይታት "ስለደረሰብሽ ነገር በሙሉ በጣም አዝኛለሁ"አለቻት በሚንቀጠቀጥ ድምፅ "ልጄም ተደፍራለች" ነርሷ አከለች

ሮዝ ነርሷን ቀና ብላ አየቻት፤ ዕድሜዋ ከአርባ አይበልጥም። ልጇም እንደኔ ትንሽ ልትሆን ትችላለች ብላ አሰበች።

በተደፈረች በነገታው ስሜት ካልሰጠው ወንድ ፖሊስና ዶክተር ጋር ያደረገችውን ውይይት አስታወሰች።

ሙሉ ሌሊት ጭካኔ በተሞላበት መልኩ የተደፈረችውን "ተጠርጣሪዎቹ" እያሉ ነበር የሰሟት፤ ታሪኳን ስትናገር።

የባዳዎቹን ይቅርና ከአባቷና ከአያቷ በስተቀር ዘመዶቿም አላመኗትም።

የነርሷ ግን የተለየ ነበር። "አመነችኝ" አለች ሮዝ

የደረሰባትንም ጥቃት ያለምንም ጥርጣሬ ስላመነቻት ተስፋ ፈነጠቀላት፤ መጪው መጥፎ ላይሆን ይችላል በሚል።

ነገር ግን የወደፊቱ መጥፎ ቅዥት ነበር፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተደፈረችበትን ቪዲዮ ራሳቸው አዩት፤ ምንም ሃዘኔታ አልነበራቸውም።

በህንድ በቡድን ተደፍራ የተገደለችው ዶክተር ጉዳይ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ

ከአስር አመት በኋላ ሮዝ ካሌምባ በመስታወት እያየች ፀጉሯን ታስተካክላለች፤ ከተደፈረችበት ከጥቂት ወራት በኋላ መስታወት መመልከት የሚታሰብ አልነበረም።

ቤት ውስጥ ያሉ መስታወቶች በሙሉ በብርድ ልብስ መሸፈን ነበረባቸው። የራሷን ምስል ለማየት አቅሙ አጥሯት ነበር።

የሃያ አምስት አመቷ ሮዝ ራሷን ከደረሰባት የማይረሳ ህመም ለማዳን የየቀኑ ጉዳይ ላይ ማተኮር አለባት።

ፀጉሯን ማበጠርና መንከባከብ አንዱ ነው። ፀጉሯ ላይ ብቻ እንድታተኩር ያደርጋታል። የሚያምር ፀጉር አላት ብዙዎችም አስተያየት ሰጥተዋታል።

በጥዋት ተነስታም ካካዎ ከቸኮሌት ታፈላለች፤ የፈውስ ንጥረ ነገር እንዳለው ታምናለች።

ከዚያም እቅዶቿን በዲያሪያዋ ላይ ታሰፍራለች፤ ወደፊት የማሳካቸው በሚል ሳይሆን አሁን እያከናወንኩት በሚል።

"በጣም ጎበዝ አሽከርካሪ ነኝ" አንደኛው እቅድ፣ " ከሮበርት ጋር ተጋብተን በሰላምና በደስታ እየኖርን ነው" ሌላኛው እቅድ "መልካም እናት ነኝ"

ሮዝ ያደገችው በትንሿ ከተማ ኦሃዮ ውስጥ ነው። ማታ ማታም ከቤት ወጥታ ብቻዋን በእግሯ መራመድ የተለመደ ተግባሯ ነበር፤ ፀጥታውና ንፁህ አየሩ ያስደስተኛል ትላለች።

እናም ከአስራ አንድ አመታት በፊትም አንድ ምሽት የአስራ አራት አመቷ ሮዝ በአካባቢዋ ቀስ ብላ እየተራመደች ነበር።

የአንዱ እርግማን ለአንዱ ምርቃን፡ ኢትዮጵያን መጠጊያ ያደረጉ የስደተኞች ታሪክ

Image copyright Rose Kalemba
አጭር የምስል መግለጫ ሮዝ ህፃን እያለች

በድንገት አንድ ግለሰብ ከጨለማው ወጣ ብሎ ወደሷ መጣ። ቢላውን አሳያትና መኪናው ውስጥ እንድትገባ አስገደዳት።

ጋቢና ወንበር ላይ 19 እድሜ የሚገመት ሌላ ወንድ ተቀምጧል። ሰውየውን መንገድ ላይ አይታው ታቃለች።

ራቅ ብሎ ወደሚገኝ ሰፈርም ወሰዷት፤ የሆነ ቤት ውስጥ አስገቧት ለአስራ ሁለት ሰዓታት ያህል ደፈሯት። ይህንንም የሚሰቀጥጥ መደፈር የሚቀርፅ አንድ ወንድ ነበር።

በከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የነበረችው ሮዝ ለመተንፈስ ስትታገል ነበር፤ ክፉኛ ተደብድባለች፣ ግራ እግሯም በጩቤ ተወግቷል፤ ልብሷም በደም ተጨመላልቋል።

ራሷንም ብዙ ጊዜ ስትስትና ስትነቃም ነበር። የሆነ ሰዓት ላይ አንደኛው ግለሰብ ሌሎች የተደፈሩ ሴቶች ቪዲዮ አሳያት።

"ደፋሪዎቹ በሙሉ ነጮች ሲሆኑ የተደፈሩት ደግሞ ነጭ ያልሆኑ ሴቶች ናቸው እናም ነጭ የበላይ ነው አለኝ" ትላለች።

አንደኛው ሰውየ ነቅታ የማታዋራቸው ከሆነ እንደሚገላት አስፈራራት። እሷም በትግል ነቃ ብላ ከለቀቋት ለማንም እንደማትናገር በመለመን ጠየቀቻቸው።

እነሱም እንደዛ ካሰቃይዋት በኋላ መኪና ውስጥ አስገቧትና፤ ሰፈሯ አካባቢ ሲደርሱ ጎዳና ላይ ጣሏት።

እንደምንም እየታገለች ቤቷ ደረሰች፤ በመስታወት ራሷን ስታየው ከጭንቅላቷ በሚፈስ ደም ፊቷ በከፊል ተሸፍኗል።

አባቷ ሮንና አንዳንድ ዘመዶች ሳሎን ተቀምጠው እየተመገቡ ነበር፤ እንደዛ ቆሳስላና በደም ተጨማልቃ ቤት ስትደርስ።

የመደፈሬን ታሪክ ከስልሳ ሰባት ዓመታት በኋላ የተናገርኩበት ምክንያት

የታዳጊዋ ሬስቶራንት ውስጥ መደፈር ደቡብ አፍሪቃውያንን አስቆጥቷል

ምን እንደተፈጠረ ነገረቻቸው

"አባቴ በፍጥነት ፖሊስ ጠራ ፤ አቀፈኝ። ሌሎች ዘመዶቻችን ግን ለምንድነው በማታ ብቻሽን በጨለማ የወጣሽው የሚል ጥያቄ ነው የጠየቁኝ" ትላለች ሮዝ

ሆስፒታል ስትደርሰ ወንድ ዶክተርና ፖሊስ ተቀበሏት።

"ሁለቱም ቢሆን እውነቱን ለማውጣት በሚል ጥያቄዎች ጠየቁኝ፤ ምንም አይነት ደግነትም ሆነ ሃዘኔታ አይታይባቸውም ነበር"

በተለይም ወንዱ ፖሊስ በፈቃደኝነት ላይ የተጀመረ ሆኖ ምናልባት ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ይሆን አላት።

ሮዝ ደነገጠች፤ አላመነችም።

"ክፉኛ ተደብድቤ፣ በጩቤ ተወግቼና በደም ተጨማልቄ እኮ ነው የመጣሁት"

ሮዝ እንደምንም ታግላ በፈቃደኝነት እንዳልሆነና የደፋሪዎቹንም ማንነት እንደማታውቅ ተናገረች። ፖሊሶቹ ምንም ፍንጭ የለንም አሉ።

ሮዝ በነገታው ከሆስፒታልም ስትወጣ ራሷን ልትገድል ሞከረች፤ ወንድሟ በጊዜው ባይደርስ ህይወቷ አልፎ ነበር።

ከተደፈረች ከጥቂት ወራት በኋላ በወቅቱ ዝነኛ የነበረው ማይ ስፔስ ማህበራዊ ድረገፅ ላይ ብዙዎች የተጋሩትን የድረገፅ ማስፈንጠሪያ አገኘች፤ ስሟም ተጠቅሶ ነበር።

ማስፈንጠሪያውን ስትጫን 'ፖርን ሃብ' ወደሚል የፖርን ድረገፅ ወሰዳት።

ራሷን ስትደበደብ፣ ጥቃት ሲደርስባትና ስትደፈር የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ስታይ ወደላይ አላት።

አንደኛው ቪዲዮ 'ታዳጊ በጥፊ ስትመታ፣ ስታለቅስና ስትደፈር' የሚል ርእስ 'ሌላኛው ቪዲዮ 'ታዳጊዋ በመደፈር ከጥቅም ውጭ ስትሆን'፣ እንዲሁም 'ራሷን የሳተች ታዳጊ ስትደፈር' የሚሉ ሁሉም የሷን መደፈር የሚያሳዩ ሲሆኑ አንደኛው ቪዲዮን አርባ ሺ ሰዎች ተመልክተውታል።

"ከዚህ ሁሉ የሰቀጠጠኝ ራሴን ስቼ የምደፈርበትን ሳይ ነው፤ ራሴን እኮ አላውቅም"

ቪዲዮዎቹን አይታ ለቤተሰቦቿ ላለመንገር ወሰነች፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ የቤተሰቦቿ አባላት እየደገፏት ስላልነበር፤ መንገር እርባና አልነበረውም።

በጥቂት ቀናትም የትምህርት ቤቷ ልጆች አዩት። "ይሰድቡኝ ጀመር፣ ፈልጌ እንደሆነና ሸርሙጣ ነሽ ይሉኝ ጀመር"

አንዳንድ ወንዶች በቤተሰቦቻቸው እንዳላሳስታቸው ከኔ እንዲርቁ ተነገራቸው። "ለብዙዎች ተጠቂን ወንጀለኛ ማድረግ ቀላል ነው" ትላለች።

የፖርን ሃብ ድረገፅን ለስድስት ወራት ያህል ቪዲዮውን እንዲያወርዱት ለመነቻቸው።

"ለመንኳቸው፣ ተማፀንኳቸው። ገና ታዳጊ ነኝ፤ ተደፍሬ ነው! እባካችሁ ከድረገፁ አውርዱት ብላቸውም ምላሽ አልሰጡኝም"

"በሚቀጥለው አመት ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼ ዝም አልኩ፤ ለምንም ነገር ስሜት አልነበረኝም"

ቢሆንም ግን አንዳንድ ሰዎች ሲያይዋት ቪዲዮውን አይተውት ይሆን በማለት ራሷን ትጠይቃለች።

"የመደፈሬ ቪዲዮ አስደስቷቸው ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ"

ራሷን በመስታወት ማየት ከበዳት ለዛም ነው ቤት ውስጥ ያሉ መስታወቶች በብርድ ልብስ የተሸፈኑት።

ጥርሷን በቡርሽም ስታፀዳ በጨለማ ማን ቪዲዮውን ተመልክቶት ይሆን እያለች ትጠይቃለች።

ከዚያም ድንገት አንድ ሃሳብ መጣላት ራሷን ጠበቃ በማስመሰል ለፖርን ድረገፁ ኢሜይል ፃፈች።

ቪዲዮውን ካላወረዱት ህጋዊ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀቻቸው፤ በአርባ ስምንት ሰአታትም ውስጥ ቪዲዮው ከድረገፁ ላይ ተነሳ።

ከወራት በኋላም የስነልቦና እርዳታ ሲደረግላት እነማን እንደሆኑ ደፋሪዎቿ ይፋ አደረገች። ለቤተሰቦቿም ሆነ ለፖሊስ ስለ ቪዲዮውም ሆነ ስለ ደፋሪዎቿ ትንፍሽ አላለችም።

የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጋቸውን ተከትሎ ደፋሪዎቿ ፍርድ ቤት ቀረቡ። የደፋሪዎቿ ጠበቃ በፍቃዷ ነው የሚል ክርክር አቅርቦ አሸነፈ።

ደፋሪዎቿ በመድፈር ሳይሆን "ከእድሜ በታች ያለችን ህፃን በማባለግ" በሚል ወንጀል ቀለል ያለ እስር ቢፈረድባቸውም፤ የእስሩ ቅጣት ተፈፃሚ አልሆነም።

ሮዝም ሆኑ ቤተሰቦቿ የደፋሪዎቿ ቅጣት ከፍ እንዲል ይግባኝ የማለት የገንዘቡ አቅምም ሆነ ፍላጎቱ አልነበራቸውም።

ሮን ካሌምባ ልጁ ላይ የነበረውንም ዝርዝር ሁኔታ ቪዲዮም እንደነበር የደረሰበት በቅርቡ ነው። በወቅቱ ቢያውቅ ምን ያደርግ ነበር ራሱን ሁልጊዜም የሚጠይቀው ጥያቄ ነው።

ከመደፈሯ በፊት ጎበዝ ተማሪ የነበረች ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን ውጤቷ አሽቆለቆለ።

ሮንና ልጁ አንዳንድ ጊዜ ፓርክ ውስጥ ሄደው ቢዝናኑም ስላለፈው ነገር ትንፍሽ አይሉም።

"መላው አለም ግድ አልሰጠውም፤ የደረሰባት ጥቃትና መደፈር ቀልድ ነበር። ሙሉ ህይወቷ ተቀይሯል" ይላል አባቷ

አጭር የምስል መግለጫ የሮዝ አባት ሮን ካሌምባ

ሮን ስለ ቪዲዮው ያወቀው ባለፈው አመት ነው፤ ሮዝ በፃፈችው ፅሁፍ ምክንያት። ፅሁፉን ብዙዎች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጋርተውታል።

የመደፈሯ ቪዲዮ ይህን ያህል ሰው እንዳየውም ሆነ ትምህርቤት እንደተቀለደባት አያውቅም።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቪዲዮዋን አይተውት ተሳልቀዋል፤ ሌላም ነገር አድርገዋል ።

Image copyright Rose Kalemba
አጭር የምስል መግለጫ ሮዝ ካሌምባና አባቷ

ሮዝ እያደገች ከመጣች በኋላ መፃፍ ላይ አተኮረች፤ በተለያዩ ድረገፆችም ላይ አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ ስሟን በመጠቀም የምትፅፍ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ በብዕር ስም፤

ሆነም ቀረ ስምጥ ብላ ወደ መፃፉ አለም ገባች።

በአንድ ወቅትም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ፖርን ሃብን የሚያወድሱ አስተያየቶች ተመለከተች፤ ለንብ ጥበቃ ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ለሚረዳ ድርጅትና ወደ ቴክኖሎጂው መግባት ለሚፈልጉ ሴቶች 25 ሺ ዶላር እርዳታ ማድረጉን አነበበች።

በፖርን ሃብ መረጃ ከሆነ በባለፈው አመት ብቻ አርባ ሁለት ቢሊዮን ጊዜ ድረገፁ ተጎብኝቷል፤ በቀን 115 ሚሊዮን ጊዜ ይጎበኛል፤ 1200 ጊዜ በሰከንዶች ድረገፁ ይታያል።

ፖርን ሃብ ታዋቂ ድረገፅ ነው፤ ራሳቸውንም እንደ ተራማጅ አድርገው ማስተዋወቋ ገረማት፤ ምክንያቱም የሷ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሴቶች የተደፈሩበት ቪዲዮዎች በድረገፁ ስላሉ።

ብዙዎች ባጋሩት ፅሁፏም ላይ የመደፈሯን ዝርዝር ሁኔታ፣ቪዲዮውን ከፖርን ሃብ ላይ ለማስወረድ የገጠማትን ፈተና ፃፈች።

ብዙዎችም ለፅሁፏ እኛም ጥቃት ደርሶብን እንዲሁ ድረገፁ አላወርድም ብሏል የሚል ምላሽ መስጠት ጀመሩ።

ፖርን ሃብ በበኩሉ ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ ይህ የተፈጠረው ከአስራ አንድ አመት በፊት እንደሆነና የድረገፁ ባለቤትም ሌሎች ግለሰቦች እንደነበሩ ነው፤ እናም በወቅቱ የነበሩት ባለቤቶች ምን አይነት ምላሽ እንደሰጡ እንደማያውቁ አስፍረዋል።

በአሁኑ ሰዓት ግን እንዲህ አይነት ህገወጥና የህፃናትንም ጥቃት ለመታደግ ፖሊሲ ከማርቀቅ በተጨማሪ የተለያዩ ሶፍትዌሮች እንዳሏቸውም አስረድተዋል።

ነገር ግን እንደ ሮዝ የመደፈር ቪዲዮ አይነት "ታዳጊ ተኝታ ባለችበት ሰዓት ጥቃት ሲደርስባት"፣ "የሰከረች ታዳጊ ስትደፈር"፣ "በጭካኔ የተሞላ የታዳጊ መደፈር" በሚሉ ርእሶች ለምን ቪዲዮዎች እንዳሉ በተጠየቁበትም ሰዓት "የትኛውንም አይነት ወሲባዊ ራስን በነፃነት የመግለፅ መብት እንደማይቃወሙና፤ እነዚህ ቪዲዮዎች ለአንዳንዶች አግባብ ባይመስሉም የሚፈልጓቸው አሉ። ይህም ነፃነትን የሚፃረር አይደለም" ብለዋል።

ምንም እንኳን ድረገፁ ህገ ወጥ ቪዲዮዎች ሲመጡ ማሳወቂያ መንገድ ከሶስት አመታት በፊት ቢያስተዋውቅም አሁንም ጥቃትንና መደፈርን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ብዙ ናቸው።

ባለፈው አመት ክርስቶፎር ጆንሰን የተባለ የ30 አመት ግለሰብ አንዲት የ15 አመት ታዳጊን ወሲባዊ ጥቃት ሲያደርስ የሚያሳይ ቪዲዮ በፖርን ሃብ ወጥቶ ግለሰቡ ለእስር ተዳርጓል።

ይህንንም ሁኔታ አስመልክቶ ፖርን ሃብ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ "ህገ ወጥ መሆኑን ስናውቅ ወዲያው አስወግደነዋል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው አመት እንዲሁ ሃያ ሁለት ሴቶች በወሲብ ባርያነት የተገደዱበትን ቪዲዮዎች በማሳየት ተከሶ የነበረ ሲሆን ቪዲዮውን አስወግደውታል፤ ቪዲዮውን የሰሩት ሰዎችም በህገወጥ የወሲብ ንግድ ተከሰዋል።

"ምንም እንኳን ብዙ ሰዎች በኔ ላይ ከአስር አመት በፊት የደረሰው የማይደርስ ቢመስላቸውም ተሳስተዋል፤ አሁንም ይደርሳል" ትላለች ሮዝ

"በከፍተኛ ሁኔታ ፖርን በሚታይባቸው በመካከለኛው ምስራቅና በእስያ ሃገራት የተደፈሩ ሴቶች ቪዲዮዋቸው እንደሚታይ ላያቁ ይችላሉ"

ሌላ እንዲሁ በካሊፎርኒያ ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት ስትደፈር የሚያሳይ ቪዲዮ በሌላ የፖርን ድረገፅ እንዳለና አውርዱት ብላ ብትጠይቃቸውም አሻፈረኝ ማለታቸውን ለሮዝ ነግራታለች።

ቢቢሲም የድረገፁን ጠበቆች ባናገረበት ወቅት ስለጉዳዩ ምንም አናውቅም ቢሉም ቢቢሲ በምላሹ የቪዲዮውን ማስፈንጠሪያ በላከላቸው በቀናት ውስጥ ቪዲዮውን አውርደውታል።

በሮዝ ላይ የተፈፀመው በሌሎች ሴቶችም ላይ እንደሚፈፀም መረጃ እንዳላቸው ኬት አይዛክ የተባለች ተመራማሪ ገልፃለች።

"ፖርን ሃብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ድረገፆች ይህንኑ ያደርጋሉ። በግለሰቦች የተቋቋሙ ትንንሽ ድረገፆች ምንም ማድረግ አንችልም። ፖርን ሃብ ግን ተጠያቂ ሊሆን ይገባል፤ ይህን የሚያስፈፅም ህግ የለም" ትላለች።

ምንም እንኳን በእንግሊዝ ለግለሰቦች ግላዊ የሆነ፣ እርቃንን የሚያሳዩ፣ ወሲባዊ ግንኙነትን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ያለ ፈቃድ ማጋራት እስከ ሁለት አመት እስራት ቢያስቀጣም፤ ድረ ገፆች ግን ተጠያቂ አይደሉም።

"የፖርን ድረገፆች የሚረብሹና ፍቃድ የሌላቸው ቪዲዮዎች እንዳሉ ያውቃሉ፤ ፊልምና ትክክለኛውን ነገርስ እንዴት እንለየዋለን ተመሳሳይ ናቸው" ትላለች።

ፖርን ሃብ ቪዲዮዎቹን ወደ ግል ኮምፒውተር መጫን (ዳውንሎድ) ማድረግ የሚቻል ሲሆን ይህ ማለት ከድረገፅ ላይ እንኳን ቢጠፉ በሰዎች ንብረትነት ይቆያሉ።

ሮዝ መደፈሯን ሙሉ በሙሉ ባትዘነጋውም ከጓደኛዋ ሮበርት ጋር ተወያይተውበታል። ተጋብተውም ሴት ልጅ እንደሚወልዱ ተስፋን ሰንቃለች።፥

Image copyright Rose Kalemba

" በብዙ መንገድ የዘላለም ፍርደኛ ነኝ፤ አንዳንድ ጊዜ እቃ ልገዛም ወጥቼ ቪዲዮውን አይተውት ይሆን እላለሁ" ትላለች።

ነገር ግን አሁን ዝምታዋን ሰብራለች። "ለደፋሪዎች መሳሪያቸው ዝምታችን ነው"

ሮዝ ብቻ አይደለችም፣በሰሜናዊ ባንግላዴሽ በአስራ ሶስት አመቷ በቡድን የተደፈረችው ፑርኒማ ሺል መደፈሯን የሚያስታውሳት ጉዳይ አሁንም አለ።

ከአስራ ሁለት አመታት በኋላ አንድ ግለሰብ ስሟንና ስልክ ቁጥሯን የያዘ የፌስቡክ ገፅ ከፍቷል።