በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1ሺህ ደረሰ

የቻይና ፖሊሶች አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሸፍነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የቻይና ባለስልጣናት የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝን የያዙበት መንገድ በተደጋጋሚ ሲያስተቻቸው ነበር

ቻይና ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በአግባቡ አልያዙም ያለቻቸውን ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሥልጣን ያነሳች ሲሆን በበሽታው ተይዘው የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 1 ሺህ መድረሱ ተሰምቷል።

የሁቤይ ጤና ኮሚሽን የፓርቲው ጸሐፊ እንዲሁም የኮሚሽኑ የበላይ ኃላፊ ከሥራቸው ከተነሱት ባለስልጣናት መካከል ናቸው።

እነዚህ ከፍተኛ ሹማምንት በቻይና ከበሽታው ጋር በተያያዘ ከስልጣናቸው የተነሱ የመጀመሪያዎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው።

የአካባቢው የቀይ መስቀል ምክትል ኃላፊም የመጣውን እርዳታ በአግባቡ ካለማድረስ ጋር በተያያዘ "ኃላፊነትን በተገቢው ሁኔታ አለመወጣት" በሚል ከሥራቸው ተሰናብተዋል።

ሰኞ እለት በሁቤይ አውራጃ ብቻ 103 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ደግሞ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1,016 ደርሷል።

ነገር ግን በቻይና በበሽታው አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ የተነገረ ሲሆን የሁቤይ አውራጃ የጤና ኮሚሽን በግዛቱ 2,097 ሰዎች መያዛቸውን ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

እንደ ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘገባ ከሆነ በሁቤይና በሌሎች ግዛቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኮረናቫይረስ ወረርሽን ጋር በተገናኘ ከሥራቸው የተሰናበቱ ሲሆን ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉና ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው የተደረጉም መኖራቸው ተገልጿል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቻይና ባለስልጣናት ወረርሽኙን የያዙበት መንገድ እያስተቻቸው ይገኛል።

የኮረናቫይረስን አስቀድሞ በመለየት ያስጠነቀቀው ዶክተር መሞቱን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።

በአሁኑ ሰዓት በቻይና 42,200 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የታወቀ ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የሳርስ ወረርሽን ቀጥሎ ከፍተኛ የጤና ቀውስ መሆኑ ተገልጿል።

የሁቤይ ጤና ኮሚሽን እንዳለው ከሆነ በአውራጃዋ ብቻ 31,728 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 974 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

አብዛኛው ሞት በሁቤይ ግዛት ዋና ከተማ ዉሃን ውስጥ የተከሰተ ነው። ይህች 11 ሚሊየን ነዋሪዎች ያሉባት ከተማ አሁን ድረስ እንቅስቃሴ ተገድቦባት ትገኛለች።

ከቻይና ውጪ በዩናይትድ ኪንግደም ስምንት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን መንግሥትም ይህንን የጤና ስጋት በሚመለከት ማስጠንቀቂያ ለዜጎቹ አስተላልፏል።

የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን ሞትን ሊያስከትል የሚችል ህመም ነው።

ወረርሽኙ በሽታው ያለበት ሰው ሲያስነጥስ፣ ባልበሰሉ ምግቦች፣ ከታማሚው ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ ይተላለፋሉ።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል። በሽታው የጠናባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ እንደ ሳምባ ምች እና ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመም ይስተዋላል።