"እናቴ 'አንቺ ለሽያጭ የምትቀርቢ አይደለሽም፤ ማንም ሊገዛሽ አይችልም' ትለኝ ነበር''

የጆፍሪና የአንጄላ ሰርግ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, ኤሪስቱዲዮስ

''ለሙሽሪት ቤተሰቦች የሚከፈል ገንዘብ እኔን ከፍሎ ለመውሰድ እንደሚደረግ ነገር አልቆጥረውም፤ እንደውም ጄፍሪ በገንዘብ ልግዛሽ ቢል በጣም ውድ እሆንበታለው'' ትላለች እንግሊዝ ውስጥ የተወለደችውና ትውልዷ ከጋና የሚመዘዘው አንጄላ።

ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ለሙሽሪት ቤተሰቦች ገንዘብ አልያም ስጦታ መስጠት፤ በእኛም ሀገር ጥሎሽ እንደሚባለው ማለት ነው የተለመደ ነገር ቢሆንም አይነቱ እና መጠኑ ግን እንደየባህሉ ይለያያል።

አንጄላ ደግሞ ''እጮኛዬ እና ቤተሰቦቹ በገንዘብ እንደገዙኝ ሳይሆን ወደቤተሰባቸው የገባሁ ትልቅ ሀብት አድርገው እንዲቆጥሩኝ ነው የምፈልገው'' ትላለች።

በጋናውያን ባህል መሰረት የሙሽራው ቤተሰቦች ገንዘብ፣ ስጦታ ወይም የሁለቱን ቅልቅል በአንድ ጊዜ አልያም ቀስ እያሉ ይከፍላሉ። ይህ ባህል በታይላንድ፣ ቻይና እና ፓፓው ኒው ጊኒም ይስተዋላል።

አንጄላ ምንም እንኳን እንግሊዝ ውስጥ ተወልዳ ብታድግም ጉዳዩ ባህሏን የመቀበልና የማስቀጠል እንደሆነ ታስባለች።

''አፍሪካዊ መሆን በራሱ ትልቅ ጫና የሚያስከትልባቸው በርካታ ዘመናት አልፈዋል፤ አሁን ግን ነገሮች እየተቀየሩ ነው። አፍሪካዊ ባህሎቻችንን መግለጸዕና መተግበር ችለናል።''

የአንጄላ ባለቤት ጄፍሪ ከጋናውያን ቤተሰቦች የተገኘ ሲሆን እሱም እንግሊዝ ውስጥ ነው የተወለደው። ለሙሽሪት ቤተሰቦች የሚከፈለው ገንዘብም ሆነ ስጦታ 'ልጃችሁን ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን' እንደማለት እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም ይላል።

''መሆን ከሚገባው በላይ የተጋነነ ገንዘብ ከሆን ግን ትርጉሙን ያጣል። ሴቲቱን በገንዘብ ገዝቶ እንደ መውሰድ ነው የሚቆጠረው።''

ከዋናው ሠርግ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ጄፍሪና አንጄላ በጋና ባህላዊ ሥነ ሥርዓት መሰረት ተሞሽረዋል። በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም ለሙሽሪት ቤተሰቦች ገንዘብና የተለያዩ ስጦታዎች ተበርክተዋል።

ነገር ግን ባህሉን ትንሽ በማሻሻል ከጄፍሪ ቤተሰቦች የተገኘውን ገንዘብና ሌሎች ስጦታዎች መልሰው፤ ከቤተሰቦቿ ለመውሰድና ኑሯቸውን ለማቋቋም ተስማሙ።

''እናቴ ሁሌም ቢሆን ስለብዙ ነገሮች ታወራኝ ነበር። አስታውሳለው ወጣት እያለሁ 'አንቺ ለሽያጭ የምትቀርቢ አይደለሽም፤ ማንም ሊገዛሽ አይችልም' ትለኝ ነበር'' ብላለች አንጄላ።

እንግሊዝ ውስጥ የሚኖሩት ሌላኞቹ ጥንዶች ብለሲንግና ቼልሲ ደግሞ ነገሮችን በተለየ መልኩ ነበር የተቀበሉት።

የፎቶው ባለመብት, BBC

ብለሲንግ ትውልዱ ከዚምባብዌ ሲሆን ለሙሽሪት ቤተሰቦች የሚከፈለውን ጥሎሽ ለማሟላት በማሰብ ሁለት ሥራዎችን በአንድ ጊዜ ይሰራ እንደነበር ያስታውሳል። ምንም እንኳን ኑሮ ከባድ ቢሆንም ባህሌ ስለሆነ ማድረግ ነበረብኝ ብሏል።

''ቼልሲ በባህላቸው መሰረት ገንዘብና ስጦታዎችን ለእሷ ቤተሰቦች በመስጠቱ ሀሳብ ብዙም አልተስማማችም ነበር። ምክንያቱም አባቷ በሕይወት ስለሌሉ ነው። እኔ ግን አሳምኛት ለቤተሰቦቿ ጥሎሹን ለመስጠት ተስማማን።''

ብለሲንግ ይህን ማድረጉ የባለቤቱን ቤተሰቦች በኩራት ለመጋፈጥ እንደሚያስችለው ያምናል።

''የጥሎሽ ገንዘቡን ለቤተሰቦቿ ባልከፍል ኖሮ ልንጠይቃቸው ስንሄድ ወይም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንገናኝ አንገቴን ሊያስደፋኝ የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ ጥሎሹን በመክፈሌ ደስተኛ ነኝ።''

ኤቨሊን ሺለር ኡጋንዳ ውስጥ ለሙሽሮች የሚከፈል ገንዘብን የሚቃወም እንቅስቃሴ ትመራለች። እሷ እንደምትለው የማህበረሰቡ ትኩረት ከባህላዊ እሴቱ ወደ ጥሬ ገንዘብ ምንጭነት ዞሯል።

''አሁን አሁን የሚደረጉትን ስንለመከት አብዛኛዎቹ ጥሬ ገንዘብ ላይ ነው ትኩረታቸው። ስለዚህ ከጥሎሽነት አልፎ ሙሽሪትን ወደመግዛት ይጠጋል። ይሄ ባህላችንም አይደለም፤ ተቀባይነትም ሊኖረው አይገባም'' ትላለች።

በኡጋንዳ ለሙሽሪት ቤተሰቦች የሚሰጥ ገንዘብ ወይም ሌላ አይነት ስጦታ ግዴታ እንዳልሆነ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰነ ሲሆን የጥንዶቹ ትዳር የሚፈርስ ከሆነ ግን የጥሎሹን ገንዘብ ይመለስልኝ ማለት አይቻልም።