ቶምና ጄሪ፡ ከኢትዮጵያ እስከ ኢራን ታዋቂነትን ያተረፈው ፊልም እንዴት ተሰራ?

ቶምና ጄሪ Image copyright Alamy

አንድ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ የተገደዱት አይጧ ጄሪና ድመቱ ቶም ተስማምተው አያውቁም። ከባለቤቶታቸው በሚሰጣቸው አይብ [ቺዝ] ሁሌም እንደተፋለሙ ነው። አይጥ ብልሃ ናት። ብዘዉን ጊዜ በአሸናፊነት ሆዷን ሞልታ ነው የምትሄደው።

መቸም መጨረሻውን መገመት አያዳግትዎትም። ድመቱ ጄሪ በብስጭት ፊቱ ቀልቶ አይኑ በርቶ ሳለ ነው የሚጠናቀቀው። አብዛኛው ክፍል ተመሳሳይ ይዘት አለው።

ምንም እንኳ ጄሪ አሸናፊ ቶም ተሸናፊ እንደሆኑ መገመት ባያዳግትም ይህ የካርቱን ፊልም እጅግ ተወዳጅ ነው። በርካታ ሽልማቶችንም አፍሷል። ቶምና ጄሪ አሁን የ80 ዓመት አዛውንት ናቸው።

ፊልሙን መጀመሪያ ያለሙት ቢል ሃና እና ጆ ባርቤራ ነበሩ። ሌሎች የፊልም አምራቾች በካርቱን ፊልም ስኬት ሲንበሻበሹ እነርሱ የሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ግን መሰል ስኬት አላገኘም። ድብርት ተጫጭኗቸው ቁጭ ብለው እያወጉ ሳለ ነው ሃሳቡ የተገለጠላቸው።

ሁሉቱም በወቅቱ ዕድሜያቸው 30 ዓመት ገደማ ነበር። ባርቤራ ስለ ድመትና አይጥ ፍጥጫ ሲያስብ እንደው ድንቅ እንደሚለው ይናገራል። ይሄኔ ነው ለምን ይህን ሃሳብ ፊልም አናደርገውም የሚለው የተገለጠላቸው።

የመጀመሪያ ክፍል በግሪጎሪ አቆጣጠር 1940 ላይ ለአየር በቃ። ከዚያማ ፊልሙ ተወዳጅነት አተረፈ። ሁሉም ስለ ቶምና ጄሪ ማውራት ያዘ፤ አልፎም ለኦስካር ሽልማት ታጨ።

ቶምና እና ጄሪ የመጀመሪያ ስማቸው ጃስፐር እና ጂንክስ ነበር። የቶምና ጄሪ አንድ ክፍል ለማምረት ሳምንታት ይወስዳል፤ እስከ 50 ሺህ ዶላርም ሊያስወጣ ይችላል። ለዚያም ነበር በዓመት ጥቂት ክፍሎች ብቻ የሚመረቱት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፈው ቶምና ጄሪ በእጅ በተሳሉ ካርቱኖች ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ ነው። ለእያንዳንዱ ክፍልም የተለያየ ሙዚቃ ይሠራላታል።

በ1950ዎቹ ቴሌቪዥን እንደጉድ ሲፈላ የቶምና ጄሪ ፊልም ሠሪዎች አዳዲስ ክፍሎችን ከምናመርት ለምን ቀድሞ የተሠሩትን አናድሳቸውም የሚል ሃሳብ መጣላቸው። ያንንም ማድረግ ጀመሩ።

Image copyright BETTMANN VIA GETTY
አጭር የምስል መግለጫ ፊልሙን መጀመሪያ ያለሙት ቢል ሃና [ግራ] እና ጆ ባርቤራ [ቀኝ]

ቶምና ጄሪ ፊልም ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል። በርካታ የፊልም ሰዎችም ተሳትፈውበታል። በ1970ዎቹ ለሕፃናት አይሆንም፤ ምክንያቱም ብዙ አመፅ ይስተዋልበታል ተብሎ በቴሌቪዥን እንዳይታይ ተከልክሎም ነበር። ይሄኔ ቶምና ጄሪ የሚስማሙባቸው ክፍሎች መመረት ጀመሩ። ተወዳጅነታቸው ግን ያን ያህል አልነበረም።

ፊልሙ ሌላው የሚወቅስበት የነበረው ጉዳይ ከቆዳ ቀለም ጋር የተገናኘ ነበር። ፊልሙ ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ሰዎች የቆዳ ቀለም መጥቆርና የገፀ-ባሕርያቱ አሳሳል ትችት አስተናግዷል።

በቴሌቪዥን በሚተላለፉ ክፍሎች ላይ ግን መሰል ገፀ-ባሕርያት ተቆርጠው እንዲወጡ ተደርጓል።

የድመትና አይጥ ግብግብ የሚያሳየው ቶምና ጄሪ ዘንድሮም ተወዳጁ የካርቱን ፊልም እንደሆነ ቀጥሏል። ከጃፓን እስከ ካናዳ፤ ከኢትዮጵያ እስካ ኢራን የሕፃናት ቴሌቪዥን ጣብያዎች ይህንን ፊልም ያስኮመኩማሉ። ቻይና ውስጥ ደግሞ ይህንን ፊልም መሠረት አድርጎ የተሠራ 'ጌም' 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ማፍራት ችሏል።

2016 ላይ አንድ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣን በመካከለኛው ምሥራቅ ለተነሳው አለመረጋጋት ተጠያቂው ቶምና ጄሪ የተሰኘው ፊልም ነው ማለታቸው አነጋጋሪ ነበር። የኢራኑ ጠቅላይ መሪ የሃገራቸውና የአሜሪካ ግንኙነት እንደ ቶምና ጄሪ ነው ሲሉ ከአንድም ሁለት ጊዜ ተደምጠዋል።

በሕፃናትም ሆነ በአዋቂዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅነት ያተረፈው ቶምና ጄሪ 80 ዓመት ደፍኗል። የፊልሙን ባለቤትነት የያዘው ዋርነር ብራዘርስ የተሰኘው ግዙፍ ተቋም ፊልሙን ለየት ባለ መልክ ሠርቶ ለዕይታ እንደሚያበቃ አስታውቋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ