ወንዶች ቆመው ወይስ ተቀምጠው ቢሸኑ ይሻላቸዋል?

ወንዶች የመሽኛ ሳጥን ላይ ቆመው ይታያሉ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በብዙ አገራት በተለይም በምዕራቡ ዓለም ወንዶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ቆመው እንዲሸኑ ነው የተማሩት

በብዙ አገራት ባህል ለወንዶች ቆሞ መሽናት ትክክል ሲሆን ሴቶች ደግሞ ተቀምጠው መሽናት ይኖርባቸዋል ተብሎ ይታሰባል።

ይህ በርካቶች የተስማሙበትን ልማድ ግን የጤና ባለሙያዎች እና የህብረተሰብ ጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት ጥያቄ እያነሱበት ይገኛል።

ለአብነትም በቅርቡ አንዲት ኬንያዊት፤ ንጽህናቸው ባልተጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ የሚጠቀሙ ሴቶች ከኢንፌክሽን ለማዳን በማሰብ ሴቶች ቆመው እንዲሸኑ የሚያስችል ቱቦ እንዲዘጋጅ ሽንጧን ገትራ ተሟግታ ነበር። መሟገት ብቻም ሳይሆን ቱቦውን ለገበያ ማቅረብ መጀመሯም ይታወሳል።

ለወንዶችም ቢሆን ቆመው ወይም ተቀምጠው ይሽኑ የሚለው ከንጽህና አልያም ደግሞ ከእኩልነት መብት ጋር የተያያዘ ነው። ሃይማኖታዊ መልክ የለውም ማለትም አይቻልም። ከጤና አንጻርስ?

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በትንሽ ቦታ በርካታ መሽኛዎች ሊገነቡ ማስቻሉ የቁም መሽኛ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል

ለወንዶች ቆሞ መሽናት ፈጣን እና ከሴቶች ሲነጻጸር በቀላሉ ሊተገበር የሚችል ነው። የታጠቁትን ሳይፈቱ በቀላሉ ጣጣቸውን መጨረስ ያስችላቸዋል።

በህዝብ መጸጻጃ ቤቶች አካባቢ ከሴቶች ክፍል ይልቅ በወንዶች መጸዳጃ ቤቶች ረዥም ሰልፎችን የማናስተውለውም ለዚያ ይሆን?

ተቋማትም ወንዶች ቆመው ለመሽናት የሚያስችላቸውን ሽንት መሽኛ ቦታዎችን በአነስተኛና ቦታ በብዛት ማዘጋጀት መቻላቸውም ቆሞ መሽናት ተመራጭ እንዲሆን ሳያደርገው አልቀረም።

በጉዳዩ ላይ ብዙ የተመራመሩ ባለሙያዎች ግን ቆሞ መሽናት በቀላሉ ሊተገበር የሚችል ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር ሽንት በሰውነት ውስጥ ተቋጥሮ ሲያዝ እና ሲሸና የሚኖረው የሰውነት አቀማመጥ ከሰውነት የሚወገደውን የሽንት መጠን ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ነው ይላሉ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የሰው ልጆች የሽንት መቋጠሪያ ፊኛቸው ሁለት እጁ (2/3) ሲሞላ ነው መሽናት እንዳለባቸው መልእክት የሚደርሳቸው

ይህን ሃሳብ በቀላሉ ለመረዳት ሽንት እንዴት እንደምንሸና በቅድሚያ እንረዳ።

ሽንት የሚመረተው በኩላሊታችን ውስጥ ነው። ኩላሊት በደም ውስጥ ያለውን ቆሻሻ ያጣራል።

የተጣራው ቆሻሻ ወደ ሽንት ፊኛ [bladder] ሄዶ ይጠራቀማል። ለዚያም ነው መንቀሳቀስና ወደ ሥራ ቦታ መሄድ የቻልነው። መተኛትስ ቢሆን? ብቻ በጥቅሉ ፊኛ ሳይኖር ሕይወትን ማሰብ ከባድ ነው።

ይሄ ታላቁ ፊኛችን የማይናቅ ተግባር ነው የሚከውንልን። ምንም እንኳ ፊኛ ከ300 እስከ 600 ሚሊ ሊትር ሽንት ማጠራቀም ቢችልም፤ እኛ ሁለት እጁ (2/3ኛው) ሲሞላ ወደ ሽንት ቤት ወደ ማዝገሙ እናዘነብላለን።

ፊኛችንን ሙሉ በሙሉ ባዶ ለማድረግ ታዲያ ጤናማ የነርቭ ሥርዓት ሊኖረን ግድ ይላል። የነርቭ ሥርዓታችን ሽንት ቤት የመሄጃው ሰዓታችንን ይነግረናል። ያለንበት ቦታ ለዚያ የማይመች ከሆነም እንድንቋጥረው መልእክት የሚተወው የነርቭ ሥርዓታችን ነው።

እፎይ ስንል ደግሞ መሽኛ አካባቢ ያለ ጡንቻ ሰውነታችንና ፊኛችን እንዲፍታታ ያደርገዋል።

ዋናው ፊኛችን ሲኮማተር ደግሞ ሽንትን መጀመርያ ወደ የሽንት መውጫ ትቦ (ዩሬትራ) ከዚያም ደግሞ ከሰውነታችን ሙሉ በሙሉ ያስወጣዋል።

እንቁም ወይስ ቁጭ እንበል?

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የፕሮስቴት ህመም ለሚሰማቸው ወንዶች ቁጭ ብሎ የመሽናት ነገር እጅግ የሚመከር ነው

ማንኛውም ጤናማ ሰው ሽንቱ ሳይመጣ በግድ ለማስወጣት መሞከር የለበትም።

ነገር ግን አልፎ አልፎ ወንዶች በጊዜያዊነት አንዳንዴም በቋሚነት የሽንት ፍሰታቸው ሊስተጓጎል ይችላል።

ፕሎስ ዋን የተባለ የሳይንሳዊ ምርምሮች ሰነድ እንደተቀመጠው ወንዶች በተለይም ፕሮስቴት መለብለብ ስሜት የሚሰማቸው ሽንት ፍሰታቸው እንዲሳለጥ ቁጭ ብለው ቢሸኑ እጅግ የተሻለ ነው።

ጥናቱ ያወዳደረው ጤናማ ወንዶችንና በፕሮስቴት ችግር ላይ ያሉትን በተለይም የሽንት ትቦ ኢንፌክሽን ኣለባቸውን ሲሆን ችግሩ ያለባቸው ወንዶች ቁጭ ብለው ሲሸኑ በቱቦው አካባቢ የተሻለ ፍሰትና ምቾት እንዳላቸው ተደርሶበታል።

ሽንታቸውን ሸንቶ ለመጨረስም የሚወስድባቸው ጊዜ አጠር ያለ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ጤናማ ወንዶች ላይ ግን ቆመውም ሆነ ተቀምጠው ቢሸኑ የሽንት ፍሰቱ ለውጥ አላሳየም።

ታዲያ የትኛው መንገድ ነው ጤናማ?

Image copyright Getty Images

በታላቋ ብሪታኒያ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት (NHS) ዜጎች ሽንት እምቢኝ ቢላቸው እጅግ ጸጥታ ወደሰፈነበት ሰላማዊ ቦታ ሄደው እንዲሞክሩ ይመክራል።

አንዳንድ ዜናዎችን ሰምታችሁ ይሆናል፤ ቁጭ ብሎ መሽናት የፕሮስቴት ካንሰርን ይከላከላል፤ ብሎም የወሲብ አቅምን ያጎለብታል የሚሉ።

ይህንን ምክር የሚያጠናክር ሳይንሳዊ ጥናት ግን የለም።

ሽንት ቤቶችን ማስዋብ ይረዳ ይሆን?

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ለወንዶች ቁጢጥ ብሎ መሽናት በብዙ ባሕል የሚበረታታ አልሆነም

በ2012 አንድ የስዊድን ፖለቲከኛ የአገሬው ወንዶች በሕዝብ ሽንት ቤቶች ጉዳይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መቀስቀስ ጀምሮ ነበር። ዓላማው ሽንት ቤቶች ፈጠራ ታክሎባቸው ወንድ ተጠቃሚዎች ንጹሕ ያልሆኑ ሽንት ቤቶች ውስጥ እግራቸውን እንዳያነሱ ማድረግ ነበር። የቁም ሽንት የሚሸናባቸው ቦታዎች በንጽሕና የሚታሙ ናቸው።

ይህ በስዊዳናዊው ፖለቲከኛ የተጀመረው እንቅስቃሴ በተለያዩ የአውሮፓ አገራትም ተስፋፍቶ አሁን አሁን አንዳንድ የሕዝብ ሽንት ቤቶች በተለይም በጀርመን አገር ቆሞ መሽናት ጭራሽ ክልክል የሆነባቸው ቦታዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ለወንዶች ቆሞ መሽናትን የሚከለክሉ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች አሉ

በአንዳንድ አገራት ይሄ ቆሞ መሽናት ክልክል መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ቁጢጥ ብለው የሚሸኑ ሰዎች የሚሰጣቸው ስም አለ፤ "Sitzpinkler" ይባላሉ። የጀርመን ቃል ሆኖ ቃሉ በደምሳሳው 'ሴታሴት' ማለት ሲሆን በአሉታዊ ትርጓሜም የሚወሰድ ነው።

ይሄ በአንዳንድ አገሮች ወንዶች ቆመው እንዲሸኑ የሚያደርገው ምልክት አንዳንድ የግል መኖርያ ቤቶችን ጭምር ተጽእኖ አሳድሮበታል። ብዙ ቤቶች ውስጥ ወንድ እንግዶች ቁጭ ብለው ውሃ ሽንት እንዲሸኑ ያስገድዳሉ።

በጀርመን አንዳንድ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ከአሸናን ጋር የተያያዙ መሆናቸው አስገራሚ ነው።

ለምሳሌ በፈረንጆች በ2015 አነጋጋሪ የነበረ የፍርድ ቤት ጉዳይ ነበር። አከራይ ተከራዩን ፍርድ ቤት የገተረው ቆሞ እየሸና የሚረጨው ሽንት ወለሉ እንዲመነችክ አድርጓል የሚል ነው።

አከራዩ ተከታዬ ቆሞ በመሽናቱ ላደረሰብኝ የንብረት ጉዳት ካሳ ይክፈለኝ ነው ያለው። ሆኖም ዳኛው በመጨረሻ ወንድ ቆሞ መሽናቱ ያለና የነበረ ነው ስለዚህ ተከራዩን አልቀጣም ብለው ውሳኔ አሳልፈዋል።