ኤርትራዊው ተማሪ እንግሊዝ ውስጥ በተፈጸመበት ጥቃት ተገደለ

አማኑኤል ገብርኤል Image copyright GMP
አጭር የምስል መግለጫ አማኑኤል ገብርኤል

እንግሊዝ ውስጥ ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቃት ተፈጽሞበት የነበረው ኤርትራዊው የህክምና ተማሪ የግድያ ወንጀል እንደተፈጸመበት ፖሊስ አስታወቀ።

በጥር ወር መጨረሻ ላይ ከአንድ ካፌ ውጪ ተከስቶ በነበረ ክፍ ያለ አምባ ጓሮ መካከል ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ተወስዶ የነበረው የ33 ዓመቱ አማኑኤል ገብርኤል ስምኦን ማክሰኞ ዕለት ህይወቱ አልፏል።

ሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ ያለፈው ኤርትራዊው ተማሪ በእረፍት ላይ የነበረ ሲሆን ትምህርቱን ሊድስ ውስጥ ሊቀጥል እንደነበረ ጠግሬተር ማንችስተር ፖሊስ ገልጿል።

የሟቹ ኤርትራዊ ቤተሰቦች እነዳሉት አማኑኤል "ትልቅ ህልምና ፍላጎት የነበረው ብልህ ወጣት ነበር" ሲሉ ምስክርነት ሰጥተዋል።

አማኑኤል ለሞት ከዳረገው ጥቃት ጋር ተያያዘ ምርመራውን የያዙት መርማሪ ካርል ጆንስ ስለ ድርጊቱ የሚያውቁ ሰዎች ምስክርነት እንዲሰጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ክስተቱን "አሳዛኝ ድርጊት" ብለውታል።

በተፈጸመበት ጥቃት ህይወቱ ያለፈው አማኑኤል ገብርኤል ወደ ብሪታኒያ የሄደው ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር።