በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አቃቤ ሕግ አስታወቀ.

ጠቅላይ አቃቤ ህግ Image copyright Attoreny General

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተበራከቱ በመጡ የወንጀል ተግባራት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር በማዋል ክስ መመስረት መጀመሩን አስታወቀ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 350 አባላቱ እንደታሰሩበት ገልጿል።

አቃቤ ሕጉ ትናንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ በብሔር ወይም በክልሎች መካካል እንዲሁም በግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጠር ግጭት መነሻነት ወንጀል በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በማድረግ የተደራጀ የምርመራና ክስ የመመስረት ሂደት ተጀምሯል ሲል ገልጿል።

በመግለጫው ላይ በግጭቶቹ ላይ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ከሚገኙባቸው ስፍራዎች መካከልም ምዕራብ ጉጂ፣ አዳማ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ አርሲ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ እና አዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የተጠቀሱ ሲሆን ከደቡብ ክልል ደግሞ ጌዲኦ ዞን፣ ሐዋሳ፣ የቴፒና ሸካ ዞን ተጠቅሰዋልወ።

በመግለጫው ላይ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ የተጀመረባቸው ሌሎች አካባቢዎችም የተጠቀሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከልም በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በጅግጅጋና ሌሎች ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ካማሽ ዞን፣ መተከል ዞን የተጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን በጃዊ ወረዳ፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በአንዳንድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተፈጸመውን ወንጀል ድርጊቶችን መነሻ በማድረግ ተጠሪጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ መጀመሩ ተጠቅሷል።

አቃቤ ሕግ በመግለጫው ላይ አክሎም የመንግሥት ከፍተኛ አመራር ባደረገዉ ግምገማ በየቦታው የሚፈጠሩ የወንጀል ድርጊቶች ዋነኛ ችግር የፖለቲካ አመራሮች እጅ ያለበት መሆኑን በሚገባ መረዳቱን ገልጿል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አክሎም ይህን የማይገባ ተግባር ሲያስፈጽም እና ሲፈፅም በዝምታ ሲያልፍ የነበረው አመራር ከድርጊቱ እንዲታረም አሳስቧል።

"በአገሪቱ በሚፈለገው መጠን የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የነበረውን ፈተና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የምንሻገረው እንደሚሆን እሙን ነው" ያለው መግለጫው ተጠርጣሪዎች በሕግ ፊት እንዲቀርቡ የሚደረገውን ጥረት በሚያደናቅፉ አካላት ላይ ያለምንም ምህረት በማያዳግም ሁኔታ ተጠያቂ እንደሚደረግ ገልጿል።

"የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ለድርድር አይቀርብም" ያለው መግለጫው ለአገሪቱ ደህንነትና ለሕዝቦች ህልውና ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን እንደማይታገስ ጽኑ አቋም መያዙን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ቢቢሲ ከቀናት በፊት በጅማ ሊደረግ ታስቦ በነበረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሕዝባዊ መድረክ መከልከል ጋር በተያያዘ ያነጋገራቸው የድርጅቱ የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ አባላቶቻቸው እየታሰሩባቸው መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችም ወጣቶች እየታሰሩ መሆኑን ቢቢሲ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሚኖሩ ግለሰቦች መረጃ ደርሶታል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ዛሬ በሰጠው መግለጫው ላይ " በኦሮሚያ የተቃዋሚ ድርጅት አባላትና ንፁኀን ዜጎች በጅምላ መታሰራቸው እጅጉን ያሳስበናል" ያለ ሲሆን፤ የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ከሳምንታት በፊት ባወጣው መግለጫ ይህንኑ ጠቅሶ ነበር።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ