የሕዝብ እንደራሴዎችን ጎራ አስለይቶ ያሟገተው የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃ ሕግ

የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አርማዎች Image copyright NurPhoto

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ ባደረገበት ሐሙስ ዕለት ከወትሮው በርከት የሚሉ ሪፖርቶችን እና የውሳኔ ሃሳቦችን መርምሮ አፅቋል።

ይሁንና በሕዝብ እንደራሴዎች ዘንድ ሞቅ ያለ ሙግትን ያስተናገደው የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ነው።

ረቂቁ የኋላ ኋላ በዕለቱ በምክር ቤቱ ከተገኙ 320 አባላቱ የሃያ ሦስቱን ተቃውሞ አስተናገዶ፤ ሁለቱ ደግሞ ድምጻቸውን አቅበው በአብላጫ ድምፅ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ሆኖ ቢፀድቅም ከአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ዘንድ የሰላ ትችት ሲቀርብበት በሌሎች ደግሞ በብርቱው ተደግፏል።

ሥጋት ያጫረው የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሕግ ጸደቀ

ቴክቫህ ኢትዮጵያ፡ የፀረ ጥላቻ ንግግር የወጣቶች እንቅስቃሴ

በምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን በመወከል አቶ አበበ ጌዴቦ በረቂቁ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብን በንባብ ካቀረቡ በኋላ የተደረገው ክርክር አባላቱ መካከል አሽሙር መወራወርን ያካተተ ነበር።

በተለይም ከአምስት ዓመታት በፊት ሁሉንም የምክር ቤቱን ወንበሮች በአባል እና አጋር ፓርቲዎቹ ከተቆጣጠረው ኢህአዴግ መፍረስ በኋላ መንገዳቸው ለየቅል በሆነው በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ አባል የሕዝብ እንደራሴዎች እና በብልፅግና ፓርቲ የምክር ቤት አባላት መካከል ያለው ፍትጊያ ጎልቶ መውጣቱን ሙግቱን የታደመው የቢቢሲ ዘጋቢ ልብ ብሏል።

በቅድሚያ በረቂቅ አዋጁ ዙርያ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ካሳ አዋጁ ሊያስፈፅማቸው የሚሞክራቸው ተግባራት በሌሎች የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግጋት ሊፈፀሙ የሚችሉ ናቸው አንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ የመናገር ነፃነትን ይሸራርፋል የሚሉ ሙግቶችን አቅርበዋል።

አሁን ሥራ ያሉ የተለያዩ ሕግጋት ግጭት ማነሳሳት፣ ሐይማኖቶችና ብሔር ብሔረሰቦችን ማጥላላትን የሚከለክሉ መሆናቸውን ጠቅሰው የሕጉን አስፈላጊት አጣጥለዋል።

በመቀጠል ዕድሉን ያገኙት አድሓና ኃይለም (ዶ/ር) እንዲሁ የዜጎችን የመናገር መብት መገደብ አሳሳቢ ነገር ነው ሲሉ ተሟግተዋል። ሕዝብን የሚያናቁሩ ንግግሮች በአብዛኛው የሚደመጡት ከባልስልጣናት፣ ከፖለቲካ መሪዎችና ከአንዳንድ የብዙሃን መገናኛዎች መሆኑን ጠቅሰው ተራውን ዜጋ በሰበቡ ለመቀፍደድ ከመሞከር ይልቅ እነዚህ አካላት ላይ ያነጣጠረ ሕግ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተከራክረው ሕጉን ምክር ቤቱ እንዳያፀድቀው ጠይቀዋል።

ረቂቅ አዋጁ የተቹ የምክር ቤት አባላት የአገርን እና የሕዝብን ደህንነትን ለመጠበቅ ሲባል ነው አዋጁ መረቀቅ ያስፈለገው የሚለውን የሕግ፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሐሳብን "አዛኝ ቅቤ አንጓች" እና "አፉ ቅቤ ልቡ ጩቤ" የተሰኙ ተረቶችን ተጠቅመው ነቅፈዋል።

Image copyright House of Peoples Representative

ይሁንና የአዋጁ ደጋፊዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየታዩ ካሉና በተለይ በማኅበራዊ የብዙሃን መገናኛዎች ከሚሰነዘሩ ጥላቻ የታጨቀባቸው ወይንም ሐሰተኛ ከሆኑ መረጃዎች ጋር ትስስር ካላቸው ግጭቶች ጋር በተያያዘ በረቂቅ አዋጁ ዙርያ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ "ለምን እስካሁን ዘገየ?" የሚል ሊሆን እንደሚገባ ተሟግተዋል።

ከመካከላቸው አቶ ተስፋዬ ዳባ በሕገ መንግሥቱ እንዲሁም በሌሎች የሕግ መርሆዎች መሰረት የመናገር ነፃነት ፍፁማዊ ከሚባሉት መካከል እንደማይመደብ ጠቅሰው ሕጉን ያለማጽደቅ አደጋን ይጋብዛል ብለዋል።

“ኢትዮጵያ አዲስ የጥላቻ ንግግር ህግ አያስፈልጋትም” አቶ አብዱ አሊ ሂጂራ

አቶ ተስፋዬ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም "ጥፍርን ለመንቀል፣ ለማኮላሸት" ምክንያት ሆኗል ያሉትን የፀረ ሽብር ሕግ እንዲሁም የቀድሞውን ፕሬዚደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን መብት ለመከልከል "ለአንድ ሰው ሲባል" ሕግጋትን ማፅደቁን ማስታወስ ይገባል "ለዚህም ይቅርታ ጠይቀናል" ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁንና አዲሱ ሕግ ዜጎች እና አገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመጋፈጥ ዕድል ይሰጣል እንደርሳቸው ሙግት።

ከዚያ ይልቅ ረቂቅ ሕጉ ለጥፋተኞች ይሁን ብሎ ያቀረበው ቅጣት መቅለል የክርክር መንስዔ ሊሆን ይገባው ነበር ብለዋል።

"ያቀረብኩት ሐሳብ ተገቢ ባልሆነ መልኩ ተተርጉሞ ምላሽ እየተሰጠበት ነው" ያሉት አድሃና (ዶ/ር) ሁለተኛ ዕድል እንዲሰጣቸው ከጠየቁ በኋላ፤ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ጫላ ለሚ የአካሄድ ተቃውሞ ቀርቦበት ሳይሳካ ቀርቷል።

በመቀጠልም በረቂቅ አዋጁ ዙርያ የሚነሰዘሩ ሐሳቦችን መበራከት ያስተዋሉት ምክትል አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ወደ ድምፅ መስጠት መሄድ ሳይሻል እንደማይቀር ሐሳብ አቅርበው ከሕዝብ እንደራሴዎቹ "አዎ" የሚል ጎላ ያለ የወል ድመፅ በመሰማቱ የምክር ቤት አባላቱ ወደ ድምፅ መስጠቱ አምርተው በ295 ድምፅ ረቂቁን አዋጅ አድርገው አፅድቀውታል።

ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ምን አሉ?

ቢቢሲ በሕጉ መውጣት ላይ ያለውን አስተያየት የጠየቀው አዲስ አበባ ውስጥ በእንግሊዝኛ እየታተመ ለረጅም ዓመታት የቆው የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ "የጥላቻ ንግግርና አደገኛ ንግግር ተምታቷል" ሲል የሕጉን መውጣት ይቃወማል።

የጥላቻ ንግግርን የሚቀጣ ሕግ ማውጣት ልክ አይደለም ያለው አቶ ታምራት ሐሳቡን በሦስት አንኳር ነጥቦች ለይቶ ይሞግታል።

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ አለው በማለትም "ባይወጣ ይሻል ነበር" ሲል አንደኛውን ምክንያቱን ያቀርባል።

ሁለተኛው ምክንያቱን ሲያስረዳም ሕግ አውጪው "እንዲህ አይነት ሕግ የማውጣት ሕገ መንግሥታዊ ስልጣን የለውም" በማለት ነው።

"ረቂቅ ሕጉ የመናገር ነጻነትን አደጋ ላይ ይጥላል" ሂይውመን ራይትስ ዎች

ይህንን ሐሳቡን በዝርዝር ሲያስረዳም ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የሚገደብባቸውን ምክንያቶች ሕገ መንግሥቱ በጠባቡ ማብራራቱን በማስታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ተነጻጻሪ መብቶችን ለመጠበቅ ሲባል ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ሊታገድ ወይም ገደብ ሊጣልበት ይችላል እንደሚል ገልጾ፣ "...እርሱ ግን የሚሆነው ጦርነትን ለመቀስቀስ የሚሞክሩ ሰዎችን አደብ ለማስገዛት፣ የሰውን ሰብዓዊ ክብር ለመጠበቅ ሲባል ከዚያ ደግሞ የሕጻናትን ወይም የወጣቶችን ደህንንት ለመጠበቅ ሲባል ሊጣልበት ይችላል ይላል። ከዚህ ውጪ ግን በምንም መስፈርት ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን ሊገድብ የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም ማለት ነው" ሲል አስተያየቱን ያጠናክራል።

አቶ ታምራት አክሎም በሕገ መንግሥቱ ላይ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን መገደብ ቢፈቀድ ኖሮ በጣም የተብራራ ዝርዝር ሊኖር ይችል ነበር ይላል።

"የጥላቻ ንግግርን ለማስቀረት ወይንም ለመከላከል ሲባል ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ ገደብ ይጣላል አልተባለም። እና ሕገመንግሥታዊ መሰረት የለውም ብዬ የምከራከረውም በዚያ ምክንያት ነው።"

አቶ ታምራት ሦስተኛው ሐሳቡን ሲያስረዳም ሕጉን ያረቀቁት ሰዎች መቆጣጠር የፈለጉት አደገኛ ንግግርን ነው በማለት ነው። "አደገኛ ንግግርን ለመቆጣጠር ደግሞ በሥራ ላይ ያሉ ወይም እስካሁን የወጡ በቂ ሕጎች አሉ" ሲል ያክላል።

"የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ውስጥ በቂ ነገር አለ። ከዚህ በፊት የነበረው የሚዲያ ሕግ፣ የማስታወቂያ ሕግ፣ የኮምፒውተር ወንጀል ሕግ ምናምን የሚባሉ በርካታ ሕጎች አሉ።"

ለአቶ ታምራት እነዚህ የጠቀሳቸው ሕጎች አደገኛ ንግግርን ለመቆጣጠርና ለመቅጣት የሚበቁ የሕግ መሳሪያዎች ናቸው። እነርሱን ሳይጠቀሙ ቀርቶ አዲስ ሕግ ማውጣም አስፈላጊ አይደለም ብሎ ያምናል።

"በጽንሰ ሃሳብ አደገኛ ንግግርና የጥላቻ ንግግር የተደበላለቀ ይመስለኛል" የሚለው ታምራት የጥላቻ ንግግርን መታገስ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል።

ሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ቅሬታዎች፣ ሙግቶች፣ መከፋቶችና አቤቱታዎች ይፋ አይውጡ እንጂ አይቀሩም የሚለው አቶ ታምራት የጥላቻው መንስዔና ምክንያት እስካልተነካ ድረስ መናገር የሚችሉት ሰዎች ፈርተው ለጥቃት አንጋለጥም ብለው በሚያስቡበት ቦታ ላይ ያደርጉታል እንጂ ሊያስቆመው አይችልም ይላል።

"የጥላቻ ንግግር ባለበት አካባቢ ላይ ብዙ ተፎካካሪና ተቃራኒ ተሟጋች ንግግሮች እንዲሰሙ፣ እንዲሰራጩ ማድረግ የሰዎች አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች በአደባባይ እንዲፋጩ፣ እንዲፈተሹ እድል ያገኛሉ" ይላል አቶ ታምራት።

"ይህ ካልሆነ ግን ግጭት የመጨረሻው እውነት ይሆናል" በማለት "ለዚያ ትልቅ ጥቅም ሲባል የጥላቻ ንግግርን መታገስ መቻል ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ" ይላል።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዚህ ሕግ ረቂቅ ላይ ማሻሻያ መደረግ አለበት በማለት ሲወተውቱ ከነበሩት አካላት መካከል አንዱ ነው። የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር ) ያሳስባቸው የነበረውን ጉዳይ በማንሳት ለምክር ቤቱ አስተያየት መስጠታቸው ያስታውሳሉ።

በወቅቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መሻሻል አለባቸው ብለው ካነሷቸው ሐሳቦች መካከል የጥላቻ ንግግርን በሚመለከት ያነሱት ነጥብ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ በጸደቀው ሕግ ላይ መሻሻሉን ይናገራሉ።

በዚህ ሕግ አወጣጥ ሂደት ውስጥ የተወሰነ ውጤት አግኝተንበታል የሚሉት ኮሚሽነሩ ከእንግዲህ በኋላ ደግሞ ወሳኙ ነገር የሕጉን ሥራ ላይ አዋዋል መከታተል መሆኑን በማንሳት ይህንንም እንደሚያደርጉ ለቢቢሲ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ሕጉ ከፀደቀ በኋላ መግለጫ ያወጣው ሂይውመን ራይትስ ዎች በበኩሉ "የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ ሕጉ የመናገር ነጻነትን አደጋ ላይ ይጥላል" በማለት መጪውን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ሠላማዊ ውይይት የሚደረግበትን መንገድ መፈለግ አለበት ሲል አሳስቧል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ