እስካሁን ስለፕላኔቶች አፈጣጠር የምናውቀውን ይቀይራል የተባለው አዲስ ግኝት

ፕላኔቶች

የፀሐይ ሥርዓትና በዙሪያዋ ያሉ ፕላኔቶች እንዴት እንደተፈጠሩ የሚተነትነውና ከዚህ በፊት የነበረውን ንድፈ ሐሳብ "በማያወላዳ ሁኔታ" የሚቀይር ግኝት ላይ መድረሳቸውን ተመራማሪዎች ተናገሩ።

እስካሁን በፀሐይና በፀሐይ ዙሪያ ያለው ዓለም እንዲፈጠር ምክንያት ነው ተብሎ የተያዘው አመለካከት የግዙፍ ቁስ አካላት በከፍተኛ ሁኔታ ተመላትም ውጤት እንደሆነ ነው።

አሁን አዲስ ተደረሰበት የተባለው ውጤት ግን ከዚህ የተለየና ቀላል ነው እንደሆነ ነው። እንዲያውም ከከባቱ ግጭት ይልቅ ቁስ አካላት ዝግ ባለ ሁኔታ በመጠጋጋት የተገኘ ውጤት ነው ይላሉ።

ይህ አዲስ ግኝት አሜሪካ ሲያትል ውስጥ በተካሄደው የሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር ጉባኤ ላይ የቀረበውና በሳይንሳዊ መጽሔት ላይ ታትሟል።

ጥናቱን የመሩት ዶክትር አለን ስተርን ስለግኝቱ እንደተናገሩት "አጅግ የሚያስደንቅ ነበር" ብለዋል።

"ከ1960ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ በስፋት ተቀባይነት ያገኘው ከባድ ግጭት አሁን ደግሞ በዝግታ የተፈጠረ መሰባሰብ ለፕላኔቶች መፈጠር እንደምክንያት ቀርቧል። ይህም በፕላኔቶች ሳይንስ ውስጥ የሚታይ ነገር አይደለም፤ ታዲያ አሁን ለጉዳዩ መቋጫ አግኝተንለታል" ሲሉ ዶክትር አለን ለቢቢሰ ተናገረዋል።

Image copyright NASA
አጭር የምስል መግለጫ የፕላኔቶችን አፈጣጠር ለመረዳት ያገዘው ምሰል

ይህ የአሁኑ ግኝት የተነሳው በፀሐይ ሥርዓት ውስጥ ያለን ቁስ አካል በጥልቀት ከማጥናት የተነሳ ነው። ይህ ቁስ አካል አሮኮት የሚል ስም የተሰጠው ሲሆን ከፀሐይ ስድስት ቢሊየን ኪሎሜትሮች እርቆ በሚገኘውና ኪዩፐር ቤልት ተብሎ በሚጠራው ክፍል ላይ ይገኛል።

ይህም ፕላኔቶች በተፈጠሩበት ጊዜ የነበራቸው ይዘት ያለው ሲሆን ከስድስት ቢሊዮን ዓመታት በፊት ሁለት አካላት ወደ አንድ የመጡበትና የፀሐይ ሥርዓት የተፈጠረበት የተገኘ ነው።

ከዓመት በፊት ናሳ "ኒው ሆራይዘን" የተባለችውን የህዋ መንኮራኩር ወደ አሮኮት ቀረብ ብላ በበረረችበት ጊዜ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ፎቶ ግራፎችን በማንሰቷ ለተመራማሪዎቹ ተጠቅመውበታል።ይህም ሳይንቲስቶቹ ላቀረቡት ቁስ አካላቱ ተላተሙ ወይስ በዝግታ ተቀራረቡ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስና የሁለቱን ተፎካካሪ ንደፈ ሐሳቦች ለመፈተን እድልን ፈጥሮላቸዋል።

በዶክትር ስተርንና በጥናት ቡድናቸው በተሰራው ትንተና በዚህ ሂደት ውስጥ ከባድ ግጭት ስለመከሰቱ የሚያመለክት መረጃን ለማግኘት አልቻሉም። በግጭት ሳቢያ የሚከሰት መሰንጠቅም ሆነ የመደፍጠጥ ምልክት አላገኙም። ይህም ሁለቱ አካላት በዝግታ መያያዛቸውን አመላካች ነው።

"ይህ ምንም የማያጠራጥር ነው" ይላሉ ዶክትር ስተርን። "በአሮኮት አቅራቢያ የተደረገው አሰሳ በአንድ ጊዜ በሁለቱ ንድፈ ሐሳቦች ዙሪያ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አስችሏል።"

ዶክትር ስተርን በተገኘው ውጤት እርግጠኛ ናቸው፤ ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቅሱት ኪዩፐር ቤልት የሚባለው አካል ከፀሐይ ሥርዓት መፈጠር አንስቶ እስካሁን ምንም ለውጥ ሳያሳይ ይህን ያህል ዘመን ባለበት መቆየቱ ነው።

Image copyright Lund Observatory
አጭር የምስል መግለጫ አዲሱ ንድፈ ሐሳብ ከ15 ዓማት በፊት ነበር የተጸነሰው

ይህ አዲሱ በዝግታ የመያያዝ ንድፈ ሐሳብ ብቅ ያለው ከ15 ዓመት በፊት ስዊዲን ውስጥ በሚገኘው ሉንድ የምርምር ማዕከል ውስጥ በፕሮፌሰር አንድሬስ ዮሐንሰን ነበር። በወቅቱ ፐሮፌሰሩ ወጣት የዶክትሬት ተማሪ የነበሩ ሲሆን ሐሳቡም የፈለቀው በኮምፒውተር ላይ በተደረጉ ሙከራዎች ነው።

ፕሮፌሰር ዮሐንሰን ከዓመታት በፊት የቀመሩት ንድፈ ሐሳብ በምርምር መረጋገጡ ሲነገራቸው ስሜታቸውን ለመግለጽ ቃላት አጥረዋቸው "በጣም ደስ ብሎኛል" ብቻ ነበር ያሉት ።

አክለውም "የዶክትሬት ተማሪ ሆኜ እዚህ ውጤት ላይ ስደርስ በጣም ደንግጬ ነበር፤ ምክንያቱም ውጤቱ ቀደም ሲል ከተገኘው የተለየ ነበር። ምናልባትም ኮዶችን ስቀምር ወይም ስሌቶችን ስሰራ ስህተት ፈጽሜ ይሆን ብዬ ተጨንቄ ነበር።"

"ታዲያ እነዚህ ውጤቶች በትክክለኛ ምልከታ ተረጋግጠው ስመለከት ትልቅ እፎይታን ነው የፈጠረልኝ" ብለዋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ስለፕላኔቶች አፈጣጠር የምናውቀውን ይቀይራል የተባለው አዲስ ግኝት

ፕሮፌሰር ዮሐንሰን ይህንን ውጤትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በፒዛና በለስላሳ በኮካኮላ አስበውታል።

በከዋክብት ዙሪያ የሚዘጋጀውን የቢቢሲን "ስካይ አት ናይት" ፕሮግራም ተባባሪ አቅራቢ የሆኑት ኢንጂነር ዶክተር ማጊ አድሪን-ፖኮክ እንደሚሉት ምንም እንኳን የተገኘው ውጤት "በብዙ መልኩ አሳማኝ ቢሆንም" በአንድ ቅኝት ብቻ ቀደም ሲል የነበረን ንድፈ ሐሳብ ውድቅ ማድረግ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

"ይህ ማስረጃ መገኘቱ ጥሩ ነገር ነው። ምንም እንኳን አንዳንድ ጥያቄዎች ቢቀርቡበትም የቁሶች መጋጨትን የሚጠቀመው ንድፈ ሐሳብ ድንቅ ነበረ። ከመለያየት ይልቅ ቁሶቹ ለምን ተያያዙ? የሚሉና ሌሎችም ምላሽ ያላገኙ ነገሮች አሉ" ብለዋል።