የአሜሪካው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር በትራምፕ ትዊት ተማረርኩኝ አሉ

ዊሊያም ባርና ትራምፕ Image copyright Reuters

የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር የፕሬዝደንት ትራምፕ የማያባሩ ትዊቶች ሥራዬን እያስተጓጎሉ ነው ሲሉ አማረሩ።

ባር ይህን የተናገሩት የቀድሞ የትራምፕ አማካሪ የነበሩትና የተከሰሱት ሮጀር ስቶን የፍርድ ሂደት ጋር በተያያዘ የአገሪቱ የፍትህ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረ ባለበት በዚህ ወቅት ነው።

አሁን ባልተለመደ መልኩ በትራምፕ ተማርሬአለሁ ያሉት አቃቤ ሕጉ ባር የትራምፕን ትዊት ሊያባራ ይገባል ሲሉ ለኤቢሲ ተናግረዋል።

ጨምረውም "ትራምፕ ስለ ፍትህ ተቋሙ የወንጀል ጉዳዮች ትዊት ማድረግ ማቆም ያለባቸው ጊዜ ይመስለኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ከስር ከስር እየተከተሉ በትዊተር ገጻቸው በሚሏቸው ነገሮቸ ምክንያት ፈፅሞ ሥራ መሥራት እያቃተን ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ሴኔት መሪ ሚች ማክኮኔል "ትራምፕ ለሥራዬ እንቅፋት እየሆኑብኝ ነው የሚለውን የጠቅላይ አቃቤ ሕጉ የባርን ቅሬታ ማድመጥና መቀበል አለባቸው" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት የአሜሪካ የፍትህ ተቋም የትራምፕ የረዥም ጊዜ ወዳጅ የነበሩት ሮጀር ስቶንን የእስራት ጊዜ ለማሳጠር እቅድ እንዳለው ማሳወቁን በብዙዎች ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል።

የትራምፕ የቀድሞ አማካሪ ስቶን እአአ በ2016 በአሜሪካ በተካሄደው ምርጫ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት ነበር በሚል ሲደረግ የነበረውን ምርመራ በማደናቀፍና በሐሰት መስክረዋል በሚል ነው የተከሰሱት።

የፌደራል አቃብያነ ሕግ ስቶን መጀመሪያ ላይ ምርመራውን ለማደናቀፍ በመሞከራቸው ከሰባት እስከ ዘጠኝ ዓመት እስር ይገባቸዋል ሲሉ የፍርድ ሐሳብ ሰጥተው ነበር።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ ትራምፕም "ይህ እብደት ነው፤ ኢፍትሃዊ ሁኔታ ነው" ሲሉ ትዊት አድርገው ነበር። እናም የፍትህ ተቋሙ የርሳቸውን ትዊት ተከትሎ የራሱ አቃብያነ ሕጎች የሰጡትን ብይን ውድቅ አደረገ።

ይህም አቃቤ ሕጉ ሚስተር ባር የትራምፕን ፍላጎት ለማስፈፀም ተንቀሳቀሱ የሚል ከባድ ጥያቄን አስነሳ። አራት አቃብያነ ሕጎችም የፍትህ ተቋሙን ውሳኔ በመቃወም ሥራቸውን ለቀቁ።