በጠምባሮ ወረዳ ከሰማይ ወረደ የተባለው እሳት ወይስ ሚትዮራይትስ?

ከተቃጠሉት የሳር ቤቶች አንዱ Image copyright kKEMBATA TEMBARO PR

ባለፈው ሳምንት አርብ ለሊት 6 ሰዓት አካባቢ ከሰማይ ወረደ የተባለ እሳት በከምባታ ጠምባሮ ዞን፣ ጠምባሮ ወረዳ በአራት ቀበሌ ውስጥ የሚገኙ 30 የሳር ቤቶችን ማቃጠሉን የጠምባሮ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ለመንቾ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ኃላፊው እንደሚሉት ስለአደጋው ሰምተው ጉዳት ወደደረሰባቸው አካባቢዎች በሄዱበት ወቅት ነዋሪዎች እንደነገሯቸው፤ እሳቱ የወረደው ከሰማይ እንደሆነና ከሚቃጠሉት ቤቶቹን ውስጥ እቃ ለማውጣት እንዳልተቸገሩ መናገራቸውን ያስታውሳሉ።

"ቤቱ እየተቃጠለ ሰው እቃውን ለማውጣት ሲሞክር እንደማያቃጥል፤ ነገር ግን በውሃም ሆነ በእርጥብ ነገር ለማጥፋት በሚሞከርበት ጊዜ ግን የበለጠ እየተባባሰ እንደሚሄድ ነግረውናል" ብለዋል።

"ከዚህ በተቃራኒው ግን" ይላሉ ኃላፊው አቶ ደጀኔ "ሰዎች እሳቱን ለማጥፋት ወደ ፈጣሪ ፀሎትና ልመና በሚያደርግበት ወቅት እሳቱ ይቀንሳል" በማለት መናገራቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

የአካባቢው ገበሬዎች እሳት የተነሳበት ቤት አጠገብ የሚገኙ የቆርቆሮ ቤቶች ሳይቃጠሉ አልፎ አልፎ ያሉ የሳር ቤቶች ብቻ በእሳት መያያዛቸውን በመመልከትና የእሳቱን ባህሪ በማስተዋል ይህ "የፈጣሪ ቁጣ እንጂ፤ የሰው ሥራ ወይንም የተፈጥሮ አደጋ ነው ብለው ለማመን መቸገራቸውን" ጨምረው ገልጸዋል።

አተቶ ደጀኔ እንዳሉት እሳቱ ከሰማይ ወረደ የተባለባቸው ዱርጊ ፥ ሲገዞ ቀበሌዎች ኩታ ገጠም ሲሆኑ፣ ዘንባራ እና ሆዶ ደግሞ የተራራቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከቤቶቹ በተጨማሪ 6 የዳልጋ ከብቶች እና የጤፍ ክምርም የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን ተገልጿል።

በአራቱም ቀበሌዎች በተመሳሳይ ሰዓት ተነሳ በተባለ በዚህ የእሳት ቃጠሎ መንስዔውን ፖሊስ ለማጣራት ሙከራ እያደረገ መሆኑን በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

አቶ ደጀኔ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በ2004 ዓ.ም አካባቢ፣ በወረዳው አጎራባች ቀበሌዎች እንዲሁ ከሰማይ ወረደ በተባለ እሳት 80 ቤቶች መውደማቸውን አስታውሰው፤ በ2009 ዓ.ም ደግሞ 8 ቤቶች በሌላ አካባቢ እንዲሁ መቃጠላቸው ክስተቶቹን አደጋ ነው ብሎ ለማመን እንደተቸገሩ ይናገራሉ።

Image copyright KEMBATA TEMBARO PR

ከሰማይ የወረደ እሳት ወይስ ሳንሳዊ ክስተት?

አቶ ነብዩ ሱሌይማን በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ውስጥ የሚሰሩ ሲሆን አስትሮኖሚና አስትሮ ፊዚክስን በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ አጥንተዋል።

ቢቢሲ በጠምባሮ ወረዳ የተከሰተውን በማንሳት ምን ሊሆን ይችላል በማለት የጠየቃቸው ሲሆን እርሳቸውም ሚትዮራይቶች [ከህዋ የሚወርዱ የአለት ስብርባሪዎች] ከደቃቅ አሸዋ እስከ ትላልቅ ድንጋዮች ድረስ እንደሚያክሉ በመግለጽ፣ አብዛኛዎቹ ወደ ምድር ሲመጡ ተቃጥለው እንደሚያልቁ ያስረዳሉ።

እነዚህ ከአሸዋ ቅንጣት እስከ ትልልቅ አለት ድረስ የሚያክሉት ሚትዮራይቶች በምንኖርበት ከባቢ አየር ላይ ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው ቢያልቁም ተቃጥለው ያላለቁ ትንንሽ ስብርባሪዎች መሬት ሊደርሱ ይችላሉ በማለት ያብራራሉ።

እነዚህ አካላት ሰው በተለምዶ ተወርዋሪ ኮከብ ብሎ ይጠራቸዋል የሚሉት አቶ ነብዩ "ማህበረሰቡ ኮከብ ቢላቸውም፤ ኮከብ አይደሉም" በማለት የሚቃጠል አለት በእኛ ከባቢ ላይ ሲያልፍ የምናይ በመሆኑ ኮከብ የሚለውን ስያሜ መሰጠቱን ያስረዳሉ።

እነዚህ ሚትዮራይቶች አንዳንዶች ትልልቅ ሲሆኑ ግዝፈታቸው ከአንድ መኪና በላይ እንደሚሆንም ገልፀዋል።

አክለውም ሩሲያ ውስጥ እኤአ 2012 አካባቢ ከእኛ አገሩ በተለየ በርከት ያሉ ስፍራዎችን የሚሸፍን ስብርባሪ ወድቆ ከፍ ያለ አደጋ ማድረሱን እንደሚያስታውሱ ያስረዳሉ።

እንዲህ አይነት አካል ሲመጣ የመሬት ከባቢ አየር አቃጥሎ ስለሚያስቀረው እንጂ ጨረቃ በቴሌስኮፕ ብትታይ ገጽታዋ የተደበደበ እንደሚመስል በመጥቀስ እነዚህ ሜቶራይትስ ተቃጥለው ሳያልቁ አካሏ ላይ በማረፋቸው ያ መከሰቱን ያብራራሉ።

ሜቶራይትስ የሚባሉት ድንጋያማ አለቶች የኮሜትና አስትሮይዶች ቅሪቶች ናቸው።

Image copyright KEMBATA TEMBARO PR

ኮሜትም አስትሮይድም ግዙፍ አለቶች መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ነብዩ፤ አስትሮይዶች ከጁፒተርና ከማርስ መካከል የሚገኙ አካላት መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ብዙዎቹ ግዙፍ ናቸው በማለትም እነዚህ አካላት ወደ መሬት ወይም ወደ ሌላ አካል ቀረብ ሲሉ እየተሰባበሩ፣ እየተሰባበሩ ይመጡና፤ መሬት በፀሐይ ዙሪያ ስትሽከረከር እነርሱን ስለምትስብ፣ ወደመሬት እየመጡ ብዙዎቹ ተቃጥለው ያልቃሉ በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

እነዚህ ተቃጥለው ያላለቁ አካላት ወደመሬት በከፍተኛ ፍጥነት የሚመጡ ሲሆን እንደ ጎጆ ቤት አይነት ቤት ላይ ካረፉ ቀስ እያሉ እየተፈረካከሱ ተቃጥለው እንደሚያልቁ ይናገራሉ።

"ቅሪቱ ግዙፍ የሚያክል ቢሆን እንኳ ወደ መሬት ሲመጣ እየተቃጠለ፣ እየተቃጠለ ይመጣል። ፍጥነቱም ቢሆን ከጥይት ፍጥነት 20 እና 30 እጥፍ ሊበልጥ ይችላል። ወደመሬት እየቀረበ ሲመጣና ፍጥነቱ እየጨመረ ሲመጣ ይፈረካከሳል" ይላሉ አቶ ነብዩ።

አክለውም "አንድ አካል የነበረው ወደ ብዙ አካላት ሲፈረካከስ አንዱ ፍርካሽ አንድ ቀበሌ ላይ ሲያርፍ ሌላኛው ደግሞ ሌላ ቀበሌ ላይ ሊያርፍ ይችላል" በማለትም በጠምባሮ ወረዳ አራት ቀበሌዎች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት እሳት ወረደ የተባለው ለዚያ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

እሳቱን በእርጥብ ነገርና በውሃ ለማጥፋት አይቻልም? ተብለው የተጠየቁት አቶ ነብዩ "እነዚህ አለቶች ተቀጣጣይ ነገር ይዘው አይወርዱም" በማለት ነገር ግን ፍጥነት ስላላቸው ነገሮች እንዲቃጠሉ ያደርጋሉ በማለት ያስረዳሉ።

"እሳቱ ቤቱ ላይ ሲያርፍ ሰዎቹን ያላቃጠለው ተቀጣጣይ ነገር ስላልሆነ ሰዎቹን ሊጎዳ አይችልም" በማለትም እነርሱ ስለማይታያቸው እንጂ መሬትንም አልፈው ሊገቡ ይችላሉ በማለት ሙያዊ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

ከጎጆ ቤቶቹ ጎን ያሉት ቆርቆሮ ቤቶች ያልተቃጠሉበት ምክንያት ሊሆን የሚችለውም ይኸው ነው ያሉት ባለሙያው፣ አለቶቹ ወደ መሬት ሲምዘገዘጉ ተቀጣጣይ ነገር ይዘው ባለመምጣታቸው መሆኑንም ያክላሉ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ስለፕላኔቶች አፈጣጠር የምናውቀውን ይቀይራል የተባለው አዲስ ግኝት

ሜቲዮሮይዶች፣ የተለያየ ዓይነት ስሪት አላቸው በማለትም በሚቃጠሉበት ወቅት የተለያየ ዓይነት ቀለም እንደሚያወጡ ያስረዳሉ።

"አንዳንዶቹ በካሊሺየም የበለፀጉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በአይረን፣ አንዳንዶቹ በፖታሺየም የበለፀጉ ስለሚሆኑ ሰማይ ላይ በሚቃጠሉበት ወቅት የተለያየ ቀለም ያሳያሉ።"

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በወረዳውና አካባቢው ላይ እንዲሁ ከሰማይ ወረደ የተባለ እሳት ቤቶች ማቃጠሉን በመጥቀስ እነዚህ ሜትዮራይትስ የት እንደሚወድቁ ማወቅ ይቻል እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ነብዩ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነ አመልክተዋል።

ሩሲያ ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ አጋጥሟት ያውቃል በማለት የቅርብ ጊዜ ክስተትን ያስታወሱት አቶ ነብዩ ይህ ሊሆን የቻለው ሩሲያ ግዙፍ በመሆኗ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም በማለት ያብራራሉ።

አክለውም "መሬት በራስዋ ዛቢያ ላይና በፀሐይ ዙሪያ ስትሽከረከር በአጋጣሚ ሆኖ ሜትዮራያቶች ወደኛ ምህዋር ይመጣሉ። እናም የት እንደሚያርፉ ብዙ ጊዜ አይታወቁም። እነዚህ ነገሮች የሚገመቱም አይደሉም። አካባቢ አይመርጡም" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በጉራዋ ወረዳ፣ ሙደና ጅሩ በሊና በምትባል የገጠር ቀበሌ ውስጥ ከሰማይ ወረደ በተባለ እሳት ከ40 በላይ የሳር ቤቶች መቃጠላቸው እንደተነገረ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች