በአፍሪካ የመጀመሪያው የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ህመምተኛ ተገኘ

የህክምና ባለሙያ ሙቀት ስትለካ Image copyright EPA

በአፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ ህመምተኛ ግብጽ ውስጥ መገኘቱ ተነገረ።

ይህም ለግብጽ የመጀመሪያው በበሽታው የተጠረጠረና በሽታው የተገኘበት ሰው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ግለሰቡም በአህጉሪቱ የተገኘ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሆኗል።

የግብጽ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በሽታው የተገኘበት ግለሰብ የውጪ አገር ዜግነት ያለው መሆኑን ቢገልጽም ከየት አገር እንደመጣ ግን አላመለከተም።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አክሎም ስለበሽታው ክስተት ለዓለም የጤና ድርጅት ማሳወቁንና በበሽታው የተያዘው ግለሰብም በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ተለይቶ ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ገልጿል።

የአፍሪካ አገራት ከቻይና ጋር ባላቸው የጠበቀ ግንኙነት ምክንያት በሽታው በአጭር ጊዜ አፍሪካ ውስጥ ሊታይ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ቀደም ሲል ሲያስጠነቅቁ ነበር።

በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱና በተለያዩ አገራት ውስጥ መታየቱ ከተነገረ በኋላ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት፣ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎችን እንዳገኙ ቢገልጹም በኋላ ላይ በተደረጉ ምርመራዎች ግለሰቦቹ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል።

ከቻይናዋ የዉሃን ከተማ ተነስቶ ወደ ተለያዩ አገራት የተዛመተው ይህ በሽታ እስካሁን ድረስ ከ1ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሚበዙት ቻይናውያን ናቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ