የወሲብ ሮቦቶች የሥነ ልቦና ጉዳትን ሊያስከትሉ ይችላል ተባለ

ሐርመኒ የተሰኘችው ሮቦት Image copyright Realrobotix

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የወሲብ ሮቦቶች በስፋት መገኘት በግለሰቦችና በማኅበረሰብ ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም ሞራላዊ ደህንነት ላይ እየጨመረ የመጣ ስጋት እየቀኑ መሆናቸውን የአሜሪካ ተመራማሪዎች አስጠነቀቁ።

ቁጥጥር የሚያደርጉት ተቋማት ክትትል ለማድረግ በጣም አሳፋሪ ስለሆነባቸው ቴክኖሎጂውን የሚያቀርቡት ድርጅቶች ከምርመራና ቁጥጥር ትኩረት ለማምለጥ ችለዋል።

ተመራማሪዎቹ ግን ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ሮቦቶች ጉዳይ በተመለከተ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

የዱክ ዩኒቨርስቲዋ ዶክትር ክርስቲን ሄንድረን ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

"አንዳንዶቹ የወሲብ ሮቦቶች እምቢ እንዲሉና ለአስገድዶ መድፈር የሚገፋፉ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩ ፕሮግራም ይደረጋሉ" ብለዋል ዶክተሯ።

"አንዳንዶቹም ህጻናትን እንዲመስሉ ተደርገው ዲዛይን ይደረጋሉ። ጃፓን ውስጥ ይህንን ከሰሩት ሰዎች መካከል አንዱ ህጻናትን የሚያባልግ እንደሆነ አምኖ የነበረ ግለሰብ ነው" ይህንንም የፈጠረው ህጻናት ላይ ጉዳት ከማድረስ ራሱን ለመቆጠብ ሲል እንደሆነ ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው የበዛ ለወሲብ አገልግሎት የሚውሉ ሮቦቶች በበይነ መረብ ላይ ለሽያጭ ይተዋወቃሉ። አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ አንድ ኩባንያ ለዚሁ ተግባር የምትውል 'ሐርመኒ' የተባለች ሮቦትን አምርቶ ከ8 ሺህ እስከ 10ሺህ በሚደርስ ዶላር ለሽያጭ አቅርቧል።

Image copyright REALROBOTIX
አጭር የምስል መግለጫ 'ሐርመኒ' የተባለችው ሮቦት

ሮቦቷ የአንድ ሰው አካላዊ ቁመና እንዲኖራት ተደርጋ የተሰራች ሲሆን ዓይኗ የሚንቀሳቀስ፣ የዓይን ሽፋሎቿ የሚርገበገቡና ስትናገር ከንፈሮቿ የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

ይህችን ሮቦት የሰራው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማት ማክሙለን እንዳለው ሮቦቷ ከባለቤቷ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖራት የሚያስችል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አላት።

"ሮቦቷ አብሯት ያለው ሰው ስለሚወደውና ስለሚጠላው ነገር እንዲሁም ከዚህ በፊት ስላጋጠመው ጉዳይ የተነገራትን ማስታወስ ትችላለች" ይላል ማክሙለን።

ሌስተር ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሮቦቶችና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሥነ ምግባርና ባህል ፕሮፌሰር የሆኑት ካትሊን ሪቻርድሰን በዚህ ዘርፍ ያለው የግብይት ሥራ በሕግ እንዲከለከል ይፈልጋሉ።

"ሮቦቶቹን የሚያመርቱት ድርጅቶች 'ጓደኛ የለህም? የህይወት አጋር የለህም? ስለዚህም አትጨነቅ የሮቦት የሴት ጓደኛ እንፈጥርልሃለን' እያሉ ነው" በማለት ይቃወሟቸዋል።

"ከሴት ጓደኛ ጋር የሚኖር ግንኙነት መቀራረብ፣ የሚጎለብት ትስስርና ሰጥቶ መቀበልን መሰረት ያደረገ ነው። እነዚህን ነገሮች ደግሞ ማሽኖች ሊያደርጓቸው አይችሉም" ይላሉ ፕሮፌሰር ካትሊን።

ፕሮፌሰሯ በእነዚህን ሮቦቶች ምርት መጀመር ዙሪያ ቁጥጥር ለማድረግ የተቋቋመው የተጽእኖ ቡድንን ያማክራሉ። ይህ የወሲብ ሮቦቶች ምርትን የሚቃወመው ቡድን ከፖሊሲ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሮቦቶች ሰዎች ከሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ሊተኩ ይችላሉ በሚል የሚደረገው ቅስቀሳ ለማገድ የሚያስችል ሕግ እንዲወጣ እየሰራ ነው።

"ሴቶችን የወሲብ ቁስ እንደሆኑ አድርጎ የሚያቀርበውን ሐሳብ ችግር የሌለበት አድርገን ተቀብለን ወደ መጪው ዘመን ልንሸጋገር ነው" ሲሉ ፕሮፌሰሯ ይጠይቃሉ።

ጨምረውም "አንድ ሰው ከሰዎች ጋር ከሚኖረው ግንኙነት አንጻር ችግር ካለበት፣ ከሌሎች ጋር በመቀራረብ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል ከማበረታታት ይልቅ፤ ሮቦትን የሰውን ያህል ለህይወቱ መልካም አማራጭ እንደሆነ ማቅረብ ተገቢ አይደለም" ሲሉ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ሮቦት ገበሬዎች የሰዎችን ስራ ሊነጥቁ ነው።