በደም እጥረት እየተፈተነች ያለቸው ኬንያ

ደም ለጋሾች Image copyright Getty Images

ኬንያ በበርካታ ሆስፒታሎቿ የደም እጥረት እያጋጠመ መሆኑን ተከትሎ የታማሚዎች ቤተሰብና ጓደኞች ደም ለጋሽ ፍለጋ እንደሚንከራተቱ የኬንያ ቀይ መስቀል አስታውቋል።

ማህበሩ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም ትዊተርን በመጠቀም ዜጎች ደም እንዲለግሱ ጥሪውን እያስተላላፈ ነው።

የደም ሻጮችና ለጋሾች ሠልፍ

በሰው ክፋይ ሕይወት መዝራት - የኩላሊት ንቅለ ተከላ

በአጠቃላይ የደም ለጋሾችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ከሚሰራው ቅስቀሳ በተጨማሪ እስካሁን የ 10 ደም ፈላጊዎችን ምስል በትዊተር ገጻቸው ላይ በመለጠፍ ኬንያውያን ሕይወታቸውን እንዲታደጉ እስከመጠየቅ ደርሰዋል።

ለመሆኑ ኬንያ ምን ያል ደም ያስፈልጋታል እጥረቱስ ለምን ተፈጠረ?

በዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት መመሪያ መሰረት ኬንያ ካላት የህዝብ ቁጥር አንጻርና ሊኖሩ የሚገቡ ደም ለጋሾችን ከግምት በማስገባት በዓመት እስከ 1 ሚሊየን ዩኒት ደም ከለጋሾች መገኘት አለበት።

ኬንያ በአሁኑ ሰአት 47 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሲሆን 1 % የሚሆነው ዜጋ ብቻ እንኳን ደም ቢለግስ በዓመት 470 ሺ ዩኒት ደም ማግኝት ይቻል ነበር።

ነገር ግን በፈረንጆቹ 2018/2019 በተሰበሰበ መረጃ መሰረት አገሪቱ በዓመት መሰብሰብ የቻለችው 164 ሺ ዩኒት ብቻ ነው።

በዚህም ምክንያት ኬንያውያን ደም ለመለገስ ብዙም ፍላጎት ከሌላቸው ሀገራት መካከል ሆናለች። ከላይ የተጠቀሰው ቁጥርም በቅርብ ዓመታት ለውጥ የሚያመጣ አይመስልም።

ከዚህ በተጨማሪ በ 2018 ደማቸውን ከለገሱ ኬንያውያን መካከል 77 % የሚሆኑት የመጀመሪያ ጊዜ ለጋሾች ናቸው። ይህ ደግሞ ምን ያክል የደም ልገሳ ባህል በኬንያ የተዳከመ እንደሆነ ያሳያል።

በቋሚነት ደም የሚለግሱ ሰዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ የደም ክምችት እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚለግሱትን ለማግኘትና ለማሳመን የሚፈጀውን ገንዘብና ጊዜም ይቆጥባል።

ባለፉት ዓመታት ኬንያ ከሚያስፈልጋት የደም ክምችት 80 % አካባቢ የሚሆነው የሚገኘው ከለጋሽ ሀገራት በሚገኝ እርዳታ እንደነበር አንድ የመንግሥት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

‘በአስራ አራት ዓመቴ ስደፈር የሚያሳይ ቪዲዮ በወሲብ ፊልም ድረገፅ ላይ ነበር'

ዋነኛው ድጋፍ ሰጪ ደግሞ የአሜሪካ መንግስት ነው። 'ፔፕፋር' በመባል የሚታወቀውና ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር በተገናኘ ለሚሰቃዩ በመላው ዓለም ለሚገኙ በሸተኞች የደምና ሌሎች ድጋፎችን ይሰጥ ነበር ይኸው ፕሮግራም።

ኬንያ ደግሞ የዚህ ፕሮግራም ዋነኛ ተጠቃሚ የነበረች ሲሆን ባሳለፍነው መስከረም ላይ ግን ለፕሮግራሙ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ተቋርጧል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚሰሩትና የመንግሥት ሀላፊ የሆኑት ሩዌይዳ ኦቦ እንደሚሉት ኬንያ በፕሮግራሙ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ነበረች። '' የአሜሪካ መንግሥት የገንዘብ ድጋፉን ሲያቆም ሀገሪቱ መጠባበቂያም ሆነ ሌላ አማራጭ አልነበራትም'' ብለዋል።

Image copyright Getty Images

የኬንያ ብሄራዊ ደም ማዕከል ሀላፊ የሆኑት ዶክተር ፍሪዳህ ጎቬዲ በበኩላቸው መንግስት ድንገት በተፈጠረው ነገር ግራ መጋባቱንና አፋጣኝ እርምጃ ግን መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

'' ልክ መስከረም ላይ ፕሮግራሙ ሲቋረጥ በቀን የምናገኘው ደም 1000 ዩኒት ብቻ ነበር። በቀን ቢያንስ ቢያንስ በትንሹ 1500 ዩኒት የሚያስፈልግ ሲሆን በዓለማቀፍ ደረጃ ግን በቀን 3000 ዩኒት ግዴታ ነው።''

ክትባት ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?

ዶክተር ፍሪዳህ እንደሚሉት አብዛኛዎቹ ኬንያውያን ስለደም ልገሳ የተሳሳተ አመለካከት ነው ያላቸው።

'' አንዳንድ ሰዎች ደም ከለገሱ የሚሞቱ ይመስላቸዋል፤ ወይም ደግሞ ደማቸው ከሌላ ሰው ደም ጋር ከተቀላቀለ ለመንፈሳቸው ጥሩ እንዳለልሆነ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ደም ከሰጡ በኋላ በዛውም የሌሎች በሽታዎች ምርመራ ስለሚደረግ ውጤቱን ለመስማት እሱን ይፈራሉ።''

የኬንያ መንግሥት ዜጎች ደም በፈቃዳቸው እንዲለግሱ የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶችን ያካሂዳል። በተለይ ደግሞ ጎልማሶችን ለማሳተፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

በአሁኑ ሰአት አብዛኛው ደም የሚገኘው ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ነው።

ተያያዥ ርዕሶች