"ልጄ በመኪና አደጋ ስለሞተ የትራፊክ አገልግሎት እሰጣለሁ"- ናይጄሪያዊቷ ዳኛ

ሞኒካ ዶንግ ባን

ናይጄሪያዊቷ ሞኒካ ዶንግባን ሜንሴም በዋናነት ስራዋ ዳኝነት ቢሆንም በትርፍ ጊዜዋ በመዲናዋ አቡጃ የትራፊክ አገልግሎት ትሰጣለች። ለዚህ ምን አነሳሳት ብትሉ ከስምንት አመታት በፊት በመኪና አደጋ የሞተውና ቀን ተሌት ሃዘኑ የሚያብሰከስካት ልጇ ነው።

ሞኒካ ቀን ሰማያዊ የትራፊክ መለዮዋን ለብሳ ከየትኛው አቅጣጫ የሚመጡ መኪኖች መቅደም እንዳለባቸው ትዕዛዝ ታስተላልፋለች።

የደምህት ወታደሮች የመኪና አደጋ ደረሰባቸው

• ከአሰቃቂ መኪና አደጋ በተአምር የተረፈችው ሴት

በአካባቢው ያለው ታዋቂ በርገር ቤት አደባባዩን በመኪና እንዲጨናነቅ አድርጎታል። ተራቸውን መጠበቅ ያቃታቸው የመኪና አሽከርካሪዎች ክላክስ አሁንም አሁንም ይሰማል።

"አብዛኛው ናይጄሪያዊ ትዕግስተኛ አይደለም ይህ ባህርይ ደግሞ ሲነዱ ይታያል" ትላለች ዳኛ ሞኒካ

ለልጇ ሞት ማን ተጠያቂ እንደሆነ ባታውቅም፤ በሃገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን መጥፎ አነዳድ ለመቀየር የራሷን አስተዋፅኦ እያደረገች ትገኛለች።

በተለያዩ የአውቶብስ መናኸሪያዎች ስለ ትራፈክ ደህንነት ለማስረዳት በምትሄድበት ወቅት ክፉኛ ያስደነገጣት ጉዳይ ቢኖር፤ አብዛኛዎቹ አሽከርካሪዎች የመንገድ ደህንነትንም ሆነ የትራፊክ ህጎች ላይ ሁነኛ የሚባል ስልጠና አለመውሰዳቸው ነው።

''እግሬን ባጣም ትልቁን ነገር አትርፌ ለትንሹ አልጨነቅም''

በትራፊክ አደጋ የበርካታ ወጣቶች ሕይወት እየተቀጠፈ ነው

እንዲህ አይነት ንህዝላልነት የልጇን ህይወት እንዳሳጣት ሳይታለም የተፈታ ከመሆኑ አንፃር ለመቀየር ቆርጣ ተነሳች።

የ62 አመቷ ዳኛ በልጇ ክዋፕዳ ስም አንድ የእርዳታ ድርጅት ያቋቋመች ሲሆን ለሞተረኞች ስለ ትራፊክ ደህንነት ስልጠና ይሰጣል።

ከዚህም በተጨማሪ መማር ለሚፈልጉ የመኪና አሽከርካሪዎች አጠቃላይ የመኪና አነዳድንም ሆነ የመንገድ ደህንነትን በተመለከተ በነፃ የማስተማርን እቅዷ ውስጥ አስገብታዋለች።

አጠቃላይ አገሪቷ ውስጥ ባለው የትራፊክ ፍሰት ያልረካችው ዳኛ ሞኒካ በሳምንታት ስልጠና ነው የትራፊክነት ስራውን ያገኘችው።

ምንም እንኳን በብዙ የሃገሪቱ ክፍል ብትንቀሳቀስም ልጇ የሞተበትን ቦታ ለመጎብኘት የእናትነት አንጀት አላስቻላትም፤አቅም አጠራት። ከሞተ ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው ልጇን የነጠቃት ጆስ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ የሄደችው።

"ቦታው ስሄድ ዋና እቅዴ የነበረው የልጄን አሟሟት የሚነግረኝ አንድ ሰው ማግኘት ነበር" ትላለች።

ነገር ግን በቦታው ስትደርስ የቦታው ግርግር ካሰበችው በላይ ስለነበር ግራ መጋባትና ድንጋጤ ነበር የተሰማት።

Image copyright Getty Images

መንገዱ የታቀደበት መንገድ ትክክል አለመሆኑ፣ የአሰራሩ ጥራት መጓደል እንዲሁም ጥገና ከማጣት ብዛት መፈራረስ ይታይበታል። የትራፊክ መብራቶችም በአካባቢው የለም።

የቀድሞው ሰላይ ሞቶ ተገኘ

"የልጄ አስከሬን ጎዳና ላይ ነበር"

መንገዱ የ32 አመቱ ልጇ ክዋፕዳ ዶንግባንን ጨምሮ በርካታ አደጋዎች የተከሰቱበት ነው።

"የመንገዱ አሰራር እግረኞችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑ አንፃር አደገኛ ነው። የበርካቶችም ህይወት ተቀጥፏል። የትኛውም የመንግሥት አካል ችግሩን ለመቅረፍ ተነሳሽነት ሲያሳይ አላየሁም" ትላለች።

በጆስ የሚገኙ ባለስልጣናት የተበላሹ መንገዶችን ለመጠገን እቅድ ላይ ቢሆኑም የመንገዱን ሁኔታ በተመለከተ ሞተረኞች እንዲሁም እግረኞች የራሳቸውን ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ለሞቱትም ከማዘን ውጭ ያሉት ነገር የለም።

በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች ለዳኛዋ እንደነገሯት ልጇ ጎዳና ላይ ወድቆ ቢያዩትም ምንም አይነት እርዳታ ሊሰጡት እንዳልቻሉ ነው።

Image copyright Monica Dongban-Mensem
አጭር የምስል መግለጫ የሞኒካ ልጅ ክዋፕዳ

"ሁለቱ እግሮቹ ተጎድተው በህመም እያቃሰተ ነበር። በደም ተለውሶ ቢያዩትም አላፊ አግዳሚው ለመርዳት ፈቃደኛ አልነበረም" በማለት ዳኛ ሞኒካ በንዴት ትናገራለች።

"በራሱ ደም እንደተዋጠ ልጄ ማንም ሳይረዳው ህይወቱ አለፈ፤ ሆስፒታል ቢሄድ ህይወቱ ይተርፍ ነበር" ትላለች።

ልጇ ከጆስ ዩኒቨርስቲ ዲግሪውን በህግ ያገኘ ሲሆን ወደ ከተማውም የተመለሰው የትምህርት ማስረጃውን ለመውሰድ ነበር፤ ነገር ግን ያልታሰበው ሆነና ላይመለስ ቀረ።

"ልጄ አቃቤ ህግ የመሆን ህልም ነበረው፤ ነገር ግን እንደ ዶሮ መንገድ ላይ ተደፍቶ ቀረ" ትላለች መረር ባለ ሃዘን።

የናይጄሪያ የመንገድ ደህንነት መረጃ እንደሚያስረዳው በዓመት ውስጥ ከ5000-6000 የሚገመቱ ሰዎች በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ያጣሉ፤ በየቀኑ 13 ሰዎች ማለት ነው።

አብዛኛዎቹ አደጋዎች ከአሽከርካሪዎች ስህተት ጋር የተያያዙ ሲሆን፤ መንጃ ፈቃድ የሌላቸው በርካታ ናቸው ተብሏል።

በባለፈው ዓመት 60 ሺ የሚሆኑ አሽከርካሪዎች በሌጎስ ያለ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ እንደነበርም ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን መመዝገብ ላይ ያለ ክፍተትና በየመንገዱ ካሜራዎች አለመኖር ገጭተው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎችን ማንነት ለመለየትም አዳግቷል።

በዚህም ምክንያት ነው የዳኛ ሞኒካን ልጅ ገድሎ ያመለጠውን አሽከርካሪ መያዝ ያልተቻለው። ገጭተው ያመለጡ ሰዎች ከተያዙ 14 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል።

ዳኛ ሞኒካ ይሄ በቂ ነው ብላ አታስብም፤ ከበድ ያለ ቅጣት ያስፈልጋቸዋል። ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ አሽከርካሪዎች የእድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድባቸው እንዲሁም ለቤተሰቦች የገንዘብ ካሳ እንዲከፈላቸው መደረግ አለበት ትላለች።

ይህም ቢሆን ያጡትን ቤተሰብ ህመም በምንም መንገድ አይቀንሰውም።

"ልጄ ይመለሳል፤ ሲመጣም ያቅፈኛል እያልኩ በር በሩን እያየሁ እጠብቃለሁ። እንቅልፍ የለኝም፤ ሲመጣ ሊርበው ይችላል ብዬ ምግብ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣለሁ"ትላለች።

የትኛዋም እናት እሷ ባለፈችበት መንገድ እንድታልፍ አትፈልግም ለዛም ነው የመንገዱን ደህንነት ለማስጠበቅ ቆርጣ የተነሳችው።

"ናይጄሪያውያን በመኪና አደጋ መሞት ሲያቆሙ የዛን ጊዜ ነው የእኔ እርካታ" ትላለች።

ተያያዥ ርዕሶች