ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር በሃገሪቱ ግዛቶች ቁጥር መስማማት አልቻሉም

ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻርና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር Image copyright Getty Images

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሃገሪቱ ግዛቶች ቁጥር ከ32 ወደ 10 ዝቅ እንዲል መስማማታቸውን ይፋ ቢያደርጉም ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር ግን እቅዱ እንደማያስኬድ ተናግረዋል።

ብሄራዊ አንድነትን ለማምጣት ያለመው ግዛቶችን የመቀነስ እቅድ በተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ይቀርብ የነበረ ሃሳብ ነው።

ነገር ግን ሪክ ማቻር እቅዱ ብዙ የተራመደ አይደለም፣ ከነበረው ብዙ አልተቀየረም በማለት እንዳልተቀበሉት ይፋ አድርገዋል።

ማቻር እና ሳልቫ ኪር እርቅ አወረዱ

በደቡብ ሱዳን ግጭት 170 ሰዎች ተገደሉ

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር 32 ግዛቶች የፈጠሩበት ምክንያት ለታማኞቻቸው ስልጣን ለማከፋፈል እንዲመቻቸውና በስልጣንም ላይ ለመደላደል ነው በማለት ሪክ ማቻር ለረዥም ጊዜያት ክፉኛ ሲተቿቸው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር 32 የግዛቶቹን አስተዳደር ከስልጣን አባረው የአስር ግዛቶች አስተዳደርን እንደሚመልሱና ይህም ያለውን ግጭት ቋጭቶ ሰላም እንደሚያሰፍን ተስፋን ሰንቀው ነበር።

ምንም እንኳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አስር ግዛቶች ቢሉም ከነሱ በተጨማሪ ሶስት "አስተዳደራዊ ቦታዎች" በፒቦር፣ሩዌንግና አብዬ መስርተዋል።

ይህም ሁኔታ ነው በሪክ ማቻር ተቀባይነት ያላገኘው።

በደቡብ ሱዳን ጦርነት ሳቢያ ሶስቱ አካባቢዎች በብሄር ግጭት ሲናጡ የነበሩ ሲሆን የሩዌንግ ግዛት ደግሞ በነዳጅ ሃብታም ናት። ሃገሪቷ ወደ ውጭ ከምትልከው ነዳጅም የአንበሳውን ድርሻ የምትይዘው ይህች ቦታ ናት።

በደቡብ ሱዳን ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት ከ380 ሺ በላይ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ፤ ብዙ ሚሊዮኖች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች በጎርጎሳውያኑ 2018 በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚያስችል ስልጣን የሚጋሩበት የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ይታወቃል።

ይሁን እንጂ የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ የስልጣን መጋራት ሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደቱን ሲያራዝሙ ቆይተዋል።

ሁለቱ ተቀናቃኞች እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ የስልጣን መጋራት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጫናዎችም እየደረሱባቸው ነው።

የደቡብ ሱዳኑ ማቻር ሃገር ሊቀይሩ ነው

በቡራዩ የተከሰተው ምንድን ነው?

በቅርቡም ኢጋድ በነበረው ስብሰባም ሱዳን ሊኖሯት ስለሚገባቸው ግዛቶች ብዛት እስከ ቅዳሜ ድረስ መፍትሄ እንዲቀመጥ አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር።

ባለፈው ዓመትም ሁለቱ ሃገራት ይህ ነው የሚባል የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሱና እንቅፋት የሚሆነው አካል ላይ ማዕቀብ ለመጣል አሜሪካ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንትም እንግሊዝ፣ አሜሪካና ኖርዌይ ሁለቱም ተቀናቃኞች ግጭቶችን አስወግደው መስማሚያ ነጥብ ላይ ሊደርሱ ይገባል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።