ኮሮናቫይረስ፡ ካሜሮናዊው ተማሪ በቻይና

ፓቬል ዳሪል Image copyright Pavel Daryl Kem Senoua

የ 21 ዓመቱ ካሜሮናዊ ኬም ሴኑ ፓቬል በቻይናዋ ጂንግዙ ግዛት ተማሪ ሲሆን በኮሮናቫይረስ መያዙን ካወቀ በኋላ "ተሽሎሃል ወደ አገርህ ተመለስ እንኳን ቢሉኝ አልመለስም" ብሏል። ምክንያቱ ደግሞ ቫይረሱን ወደ አፍሪካ ይዞ ላለመግባት ነው።

'' ምንም ነገር ቢፈጠር ይህን በሽታ ወደ አፍሪካ ይዤ መመለስ አልፈልግም'' ያለው በዩኒቨርሲቲ ዶርምተሪ ውስጥ የ 14 ቀናት ክትትል በሚደረግለት ወቅት ነው።

በመጀመሪያ ከባድ ትኩሳትና ደረቅ ሳል አጣድፎት ነበር፤ በመቀጠል ግን ፈሳሽ ከአፍንጫው መውጣት ጀመረ። ምልክቶቹን ካስተዋለ በኋላ በልጅነት ታሰቃየው የነበረችው ወባው እንደተነሳችበት አስቦም ነበር። ነገር ግን ያላሰበውና ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘው ኮሮናቫይረስ ሆኖ ተገኘ።

የኮሮናቫይረስ ስጋት ባጠላበት በርካቶች በአንዴ ተሞሽረሩ

የኮሮናቫይረስ ተጽዕኖ በቻይናና በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ

'' ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሆስፒታል ስሄድ የምሞትበት ሰአት እንደተቃረበ አስብ ነበር። በቃ መሞቴ ነው እያልኩ ለራሴ ነግሬው ነበር'' ብሏል።

ኬም ሴኑ ፓቬል አሁን በለይቶ ማቆያ ውስጥ 13ኛ ቀኑን ይዟል፤ በአንድ የቻይና ሆስፒታል ውስጥ። ህክምናው በተለይም የኤችአይቪ ታማሚዎችን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉ መድሃኒቶችን በብዛት ይጠቀማል።

ከሁለት ሳምንታት ተከታታይ ህክምና በኋላ እየተሻለው መጥቷል። በሲቲ ስካን በተደረገለት ምርመራም ቫይረሱ ከሰውነቱ እንደጠፋ ምልክቶች ታይተዋል።

ፓቬል በገዳዩ ኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሲሆን ሙሉ የህክምናው ሙሉ ወጪ በቻይናዋ ግዛት ተሸፍኗል።

'' ትምህርቴን ሳልጨርስ ወደ አገር ቤት መመለስ አልፈልግም። ወደ ካሜሩን የምምለስበት ምንም ምክንያት የለኝም፤ ሙሉ የሆስፒታል ወጪዬ በቻይና መንግስት ተሸፍኖልኛል''ብሏል።

በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች፣ ሰራተኞችና ቤተሰቦች እስካሁንም ድረስ በቻይናዋ ሁቤ ግዛት እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ የሚገኙ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከቻይና አስወጡን የሚል ጩኸት እያሰሙ ነው።

ዛምቢያዊቷ ሲልያኒ ሳሊማም ከነዚህ መካካል አንዷ ናት። እሷ እንደምትለው የአገሯ መንግሥት ምንም እያደረገ አይደለም። '' እኛ አፍሪካውያን ተለይተን ቀርተናል፤ እኛ ዜጎች አይደለንም እንዴ?'' ብላለች።

ሲልያኒ ቫይረሱ እንዳይዛመት በመስጋት ለወራት እራሷን ከሰዎች ለይታ ቆይታለች። ቀኑን ሙሉ በመተኛትና ስለቫይረሱ አዲስ ነገር ካለ በማለት ዜና ስትከታተል ታሳልፋለች።

የምግብና አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችም እጥረት እንዳያጋጥማት ከፍተኛ ስጋት አለባት።

Image copyright EPA

80 ሺ የሚሆኑ አፍሪካውያን ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት ዕድሎች አማካይነት ቻይና ውስጥ ይገኛሉ።

እርምጃ ለመውሰድ ከተንቀሳቀሱ የአፍሪካ መንግሥታት መካከል የአይቮሪ ኮስት መንግሥት አንዱ ሲሆን ከሳምንታት ውይይት በኋላ በዉሃን ለሚገኙ 77 ተማሪዎች 490 ዶላር ለመስጠት ተስማምቷል።

በገንዘቡም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ገዝተው እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ አስጠንቅቋል። የጋና መንግሥት ለተማሪዎቹ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።

በዉሃን ከሚገኙ ኢትዮጵያውን ተማሪዎች 95 በመቶ መመለስ ይፈልጋሉ

አፍሪካ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል አቅሙ አላት?

በዉሃን ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎችም 95 በመቶ የሚሆኑት ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ በበተነው መጠይቅ ማረጋገጡን በዉሃን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

የህብረቱ ፕሬዝደንት ዘሃራ አብዱልሃዲ እንደገለፀችው በመጠይቁ ከተሳተፉ ተማሪዎች መካከል 41 በመቶ የሚሆኑት መንግሥት ወጪያችንን ሸፍኖ ወደ አገራችን ይመልሰን ያሉ ሲሆን፤ 54 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በራሳችንም ወጪ እንመለሳለን መንግሥት ግን ጉዟችንን ያመቻችልን ሲሉ ፍላጎታቸውን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የተማሪዎቹን 'ወደ ኢትዮጵያ መልሱን' ጥያቄን ህብረቱ በቻይና ለኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳቀረበ የምታስታውሰው ዘሃራ፤ አሁንም የተማሪው ጥያቄ እጅግ እየገፋ በመምጣቱ መጠይቅ በትነው የተማሪውን ወደ አገራችን መልሱን ጥያቄ በጥናት ማረጋገጣቸውን ታስረዳለች።

ዘሃራ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች፤ እንዲሁም የሟቾችም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በመጥቀስ "ተማሪው ከባድ የስነልቦና ጫና ውስጥ ነው ያለው" ብላለች።

በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥያቄ በቀረበለት ወቅት 'የተማሪዎቹን ጥያቄ ለመመለስ ሁኔታዎችን እያጤንን ነው' የሚል ምላሽ ለቢቢሲ ሰጥቶም ነበር።

በሁኔታዎች መባባስ ምክንያት ስጋት የገባቸው በርካታ ተማሪዎች ወደ ሀገራችን መልሱን እያሉ ቢሆንም ኬም ሴኑ ፓቬል ግን ወደ ሀገሬ የቫይረሱን ስጋት ይዤ መግባት አልፈልግም ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች