ሐማስ የአማላይ ሴቶችን ፎቶ በመጠቀም የእስራኤል ወታደሮችን ስልክ ጠለፈ

ሃማስ የወታደሮቹን ስልክ ለመበርበር ከተጠቀማቸው የሴቶች ፎቶግራፍ መካከል አንዱ። Image copyright IDF
አጭር የምስል መግለጫ ሐማስ የወታደሮቹን ስልክ ለመበርበር ከተጠቀማቸው የሴቶች ፎቶግራፍ መካከል አንዱ።

የሚሊሻ ቡድኑ ሐማስ የበርካታ የእስራኤል ወታደሮችን ስልክ መጥለፉን የእስራኤል ጦር አስታወቀ።

ቡድኑ ጾታዊ ግንኙነት ፈላጊ ሴት በመምሰል የአማላይ ሴቶች ምሥል በመጠቀም ወደ ወታደሮች ስልክ መልእክት ይልካል፤ ከዚያም የጦሩ አባላት ሳያውቁ በስልካቸው ላይ ስለላ ለማድረግ የሚጠቅም መተግበሪያ (አፕ) ይጭናል።

የእስራኤል ጦር እንዳለው ሐማስ ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትል ብርበራው እንዲከሽፍ ተደርጓል ብሏል።

ጋዛን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ሐማስ ከእስራኤል ጋር ለዓመታት ባላንጣ ሆኖ ቆይቷል።

የእስራኤል ጦር ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ሊውተኔት ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ እንደሚሉት ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሐማስ ተመሳሳይ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ይህ ሙከራው ግን ከዚህ ቀመድ ሲጠቀምባቸው ከነበሩት ስልቶች የተለየ እና የቴክኖሎጂ ይዘቱም የተራቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

"እራሳቸውን እያስተማሩ እና እየሰለጠኑ መምጣቻቸውን አስታውለናል" ብለዋል።

ሊውተኔት ኮሎኔል ጆናታን እንደሚሉት ከሆነ የሐማስ በርባሪዎች ሂብሩ ቋንቋ የማይችሉ እና ወደ እስራኤል በቅርብ የመጡ ሴት የጾታ ግንኙነት ፈላጊ በመምሰል ወንድ ወታደሮችን ዒላማ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ቋንቋ እንደማይችሉ እና በቅርብ ወደ እስራኤል እንደመጡ ማስመሰላቸው በጦሩ አባላት ዘንድ እንዲታመኑ አድርጓቸዋል ብለዋል የጦር አዛዥ።

"ግንኙነቱን ከተጀመረ በኋላ 'ፎቶግራፋችንን ተመልከቱ' በማለት ሊንክ ይልካሉ። ሊንኩን ሲጫኑት ግን ስልካቸውን መበርበር የሚያስችል መተግበሪያ ይጫናል" ብለዋል።

በርባሪዎቹ ይህን ሲያደርጉ በስልካችው ላይ የሚገኙትን የሰዎች ስም እና አድራሻን ጨምሮ ሙሉ መረጃ ማግኘት ያስችላቸዋል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ያለ ስልኩ ባለቤት ዕውቅና የተጠለፈበት ሰው ስልክ ድምጽ እና ምሥል እንዲቀርጽ ማድረግ ይቻላቸዋል ተብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ወታደሮቹ ዘመናዊ ስልኮችን ሲጠቀሙ የበርባሪዎች ዒላማ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲወስዱ የሚያስችል ስልጠናዎችን ሲሰጥ እንደነበረ ተነግሯል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ