የዓለማችን ዋነኛ ሃብታም ለአየር ንብረት ለውጥ 10 ቢሊየን ዶላር እሰጣለሁ አለ

ጄፍ ቤዞስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአማዞን ባለቤትና የበላይ ኃላፊ ጄፍ ቤዞስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ትግል ለማገዝ 10 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገባ።

እንደ ግለሰቡ አስተያየት ከሆነ ገንዘቡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ምርምር የሚያደርጉ ሳይንቲስቶችን ስራ ለማገዝ፣ የመብት ተሟጋቾችን እንዲሁም ሌሎች ቡድኖችን ለመደገፍ ይውላል።

አክለውም " የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ተጽዕኖ ለመዋጋት የሚታወቁ መንገዶችን ለማጠናከርና አዳዲስ መንገዶችን ለመፈለግ በትብብር መስራት እፈልጋለሁ" ብሏል።

ጄፍ በኢንስታግራም ገፁ ላይ እንዳሰፈረው፣ ገንዘቡ በመጪው የክረምት ወር መከፋፈል ይጀምራል።

ሚስተር ቤዞስ አጠቃላይ ሀብቱ 130 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሲሆን ቃል የገባው የሀብቱን 8 በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል።

አንዳንድ የአማዞን ሠራተኞች አለቃቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የበለጠ እንዲሰጥ ሲወተውቱ ነበር።

አንዳንዶቹም በይፋ አደባባይ ወጥተው ይህንን አቋማቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ ድርጅቱን ጥለው ወጥተው ነበር።

ከዚህ ቀደም ሚስተር ጄፍ ቤዞስ 'ብሉ ኦሪጅን' የተባለ የጠፈር ምርምር ፕሮግራምን በገንዘብ ቢደግፍም ለአየር ንብረት ለውጥ ሲባል እጅ ያጥረዋል ተብሎ ይተች ነበር።

ከሌሎች የናጠጡ ሃብታሞች አንጻር ሲታይ ጄፍ ቤዞስ፣ በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ እምብዛም የማይሳተፍ ሲሆን ከዚህ የድጋፍ ተግባሩ በፊት ትልቅ ለልግስና ያወጣው ገንዘብ በ2018 ለቤት አልባዎችና ትምህርት ቤቶችን በሚል የሰጠው 2 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነው።

ከዚህ በፊት ቢሊየነሮች በሕይወት ዘመናቸው ያካበቱትን ሀብት ግማሹን ለበጎ ተግባራት እንዲውል ለመስጠት ተስማምተው ሲፈርሙ፣ እርሱ ባለመፈረሙ ምክንያት ስሙ ሲብጠለጠል ነበር።

መቀመጫውን ሲያትል ያደረገው አማዞን ከማይክሮሶፍት ጋር የሚጎራበት ሲሆን በ2030 ከካርቦን የፀዳ ተቋም ለመሆን ያለውን እቅድም ይፋ አድርጓል።