በኮሮናቫይረስ ምክንያት የግል አውሮፕላን ተፈላጊነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ

የግል አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የግል አውሮፕላኖች ተፈላጊነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የግል አውሮፕላኖችን የሚያከራዩ ኩባንያዎች ከመንገደኞች በርካታ ጥያቄ እየቀረበላቸውም ነው ተብሏል።

በርካታ የአየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ መሰረዝ እንዲሁም ቁጥሩን መቀነሳቸው ወደየአገራቸው መሄድ የሚፈልጉ መንገደኞችን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።

ወደ ቻይና መሄድ የሚፈልጉ እንዲሁም ከቻይና መውጣት የሚፈልጉ ግለሰቦች በረራዎችን በመፈለግ በተጠመዱበት ሰዓት በግላቸው አውሮፕላን መከራየት የሚችሉት ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከፍለው ባመቻቸው ቀንና ሰዓት መጓዝ እንደቻሉ እየተዘገበ ነው።

ነገር ግን ምንም እንኳን ግለሰቦቹ "ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ" በሚለው እየተመሩ ቢሆንም ጥያቄያቸው ግን በአንዳንድ ኩባንያዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።

ለዚህም ደግሞ እንደ ምክንያትነት የተቀመጠው የአውሮፕላን ሠራተኞች በስጋት ምክንያት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ነው።

በአውስትራሊያ ተቀማጭነቱን ያደረገው ዳሪን ቮይልስ እንዳስታወቀው በእነዚህ ጥቂት ሳምንታት አውሮፕላኖቻቸውን ለመከራየት ከፍተኛ ፍላጎት ያለ ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹን በአውሮፕላንና በሠራተኞች እጥረት ለመመለስ ተገደዋል።

ብዙዎች አውሮፕላኖቻቸውንም ሆነ ሠራተኞቻቸውን ወደ ቻይና መላክ አይፈልጉም። ሠራተኞች በቫይረሱ ይያያዛሉ ብሎ ከመስጋት በተጫማሪ ለቢዝነሱም አዋጭ አይደለም፤ ምክንያቱም ቻይና ደርሰው ከተመለሱ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ያህል ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸው ነው።

ይህም ማለት በእነዚህ ቀናት አውሮፕላኖቻቸው ሥራ ፈትተው ይቆያሉ ማለት ነው።

በሲንጋፖር ተቀማጭነቱን ያደረገው ማይሌት ኤዥያ በበኩሉ ባለፈው ወር ብቻ ከ80-90 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

"የቻይና አዲስ ዓመት በዓል በሚከበርበት ወቅት ብዙዎች ከቻይና ወጥተው ነበር አሁን ደግሞ ወደ ቻይና ለመመለስ ትግል ላይ ናቸው" በማለት የማይሌት ኤዥያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተናግረዋል።

ብዙዎቹንም ወደ ቤይጂንግ፣ ሻንጋይና ሆንግ ኮንግ አድርሰዋቸዋል።

"ምንም እንኳን ወደ ቻይና ብንበርም አንዳንድ ቦታዎች አይፈቀደልንም፤ መንገደኞች ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኛ ቢሆኑም አንዳንድ አየር መንገዶች በነፃነት እንድንቀሳቀስ አይፈቅዱልንም" ብለዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ከቻይና ለመውጣት ቀን ተሌት ትግል ላይ ናቸው። ከደቡብ አሜሪካ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችን ከዉሃን እንዲወጡ የግል አውሮፕላኖችን እንዲከራዩለት ጥያቄ እንደቀረበላቸው የፕራይቬት ፍላይ ሥራ አስፈፃሚው አዳም ቲዊደል ገልፀዋል።

በእንግሊዝ ተቀማጭነቱን ያደረገው ኩባንያ በበኩሉ ከግለሰቦች እንዲሁም በቡድን አውሮፕላን እንፈልጋለን የሚሉ ጥያቄዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚመጡለት ነው።

ቀለል ያለ አውሮፕላን ከ2 እስከ አራት መንገደኞችን የሚያሳፍር ሲሆን በሰዓት 77 ሺህ ብር የሚገመት እንደሚያወጣ ፖራማውንት ቢዝነስ ጄትስ የሚባል ኩባንያ አስታውቋል።

መካከለኛ የሆኑ አውሮፕላኖች ደግሞ ከ8- 10 ሰዎችን የመያዝ አቅም አላቸው፤ በሰዓትም 192 ሺህ ብር ያስከፍላሉ።

ግሎባል ፕራይቬት የተባለው ኩባንያም ምንም እንኳን ምንም ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ የሰረዘ ቢሆንም ጥያቄዎች ግን በእጥፍ እንደጨመሩ ነው።

ምንም እንኳን ፍላጎት በከፍተኛ መጠን ያሻቀበው በተወሰነ መልኩ ከቻይና አዲስ ዓመት ጉዞዎች ጋር የተያያዘ ቢሆንም በዋነኝነት ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ግለሰቦች ከሌሎች መንገደኞች ጋር ለመጓዝ አለመፈለጋቸውን ቪስታ ጄት የተባለው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ይናገራሉ።

በጎርጎሳውያኑ 2003 ከተነሳው ሳርስ ጋር በተያያዘም የግል አውሮፕላኖች ጥያቄ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም በዚያን ጊዜ መውጣት መግባትም ቀላል ስለነበር እንዳሁኑ በርካታ አልነበሩም ተብሏል። በአሁኑ ወቅተት መንግሥታት ከፍተኛ ቁጥጥርም እያደረጉ ያሉበት ጊዜ ነው።