ሮበርት ሙጋቤ እና አራፕ ሞይ: አንጋፋዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ሲታወሱ

ሞይ እና ሙጋቤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ እና የኬንያው ዳንኤል አራፕ ሞይ የተወለዱት በጎርጎሳውያኑ 1924 ሲሆን ሁለቱም ሕይወታቸው ያለፈው በ 95 ዓመታቸው ነው።

እኚህ በአፍሪካ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያላቸው መሪዎች በጸረ ቅኝ ግዛት ፖለቲካ ተሳታፊ ነበሩ፤ ሙጋቤ የትጥቅ ትግል ቢያደርጉም ሞይ ግን ጠመንጃ አላነሱም።

ሁለቱም በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አገራትን የመሩ ሲሆን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ከነጭ ሰፋሪዎች ጋር ሲታገሉ ቆይተዋል።

የእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤጥም ሁለቱን መሪዎች ታደንቃቸው እንደነበር ይገለጻል። ኬንያንም ሆነ ዚምባብዌን በአካል ሄደውም ጎብኝተው ነበር።

ሞይና ሙጋቤ ከገጠሪቱ የአገራቸው ክፍል ያደጉና ከብት በመጠበቅ ልጅነታቸውን ያሳለፉ መሆናቸው ከሚያመሳስሏቸው ነገሮች መካከል ይጠቀሳሉ። ለመሆኑ እነዚህን መሪዎች የሚያመሳስሏለቸው ሌሎች ነገሮች ይኖሩ ይሆን?

የክርስትና ተጽ

ሁለቱም መሪዎች ያለ አባት ሲሆን ያደጉት በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት በሚሽነሪዎች ለመሙላት ጥረዋል። ሞይ መንፈሳዊ መጠለያ ፍለጋ በአንድ የፕሮቴስታንት ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በዛውም ነው የክርስትና ስማቸው ዳንኤልን ያገኙት።

ሙጋቤ ደግሞ በነጮች ቁጥጥር ስር በነበረ የካቶሊክ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን ጀሮም ኦሂያ የተባሉ የሃይማኖት አባት ጋርም ጠበቅ ያለ ግንኙነት እንደነበራቸው ይታወቃል።

ሁለቱም መሪዎች በመጀመሪያ የተሰማሩበት የስራ ዘርፍ መምህርነት ሲሆን የተሳካላቸው መምህራን ነበሩ። በፖሊሲዎቻቸውም ቢሆን ትምህርት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበር።

ሞይ በኬንያ ከሚታወቁበት ነገር አንዱ በትምሀርት ቤት ያስጀመሩት ነጻ የወተት አቅርቦት ሲሆን ሙጋቤ ደግሞ ለሁሉም ዜጎች ትምህርት ነጻ እንዲሆን በማድረግ ሃገሪቱ ያላትን የተማረ የሰው ኃይል ቁጥር ከፍ ማድረግ ችለዋል።።

ፖለቲካዊ ጭቆና

ሞይ በተለይም ደግሞ በጎርጎሳውያኑ ከ1982ቱ መፈንቅለ መንግስት በኋላ ተቃዋሚዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃን ወስደዋል።

በጊዜውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል፤ እንግልትና ስቃይ ተፈፅሞባቸዋል። በዛውም ሙሉ በሙሉ ስልጣን በእጃቸው እንዲሆን አድርገዋል።

ሙጋቤም ቢሆን ተቃዋሚዎች ላይ ፈርጠም ያለ ክንዳቸውን በማሳረፍ ይታወቃሉ። ዚምባብዌያውያን ያለምንም ምክንያት ይታሰሩና ይሰቃዩ ነበር። ሙጋቤ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተቺዎቻቸውን ዝም ለማሰኘት በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋል።

ልክ እንደ ሞይ ሁሉ ሙጋቤም ከታዋቂ ፖለቲከኞች ሞት ጋር ስማቸው አብሮ ይነሳል።

ሙጋቤ በሌላም አንድ አሰቃቂ ነገር ይወነጀላሉ። 'ጉኩራሁንዲ' ተብሎ የሚጠራውና የንዴቤሌ ቋንቋ ተናጋሪዎችን የማጥፋት ዘመቻ አቀነባብረዋልም ይባላል። ዚምባብዌ ነጻነቷን ካገኘች ጥቂት ዓመታት በኋላ በተደረገው ይህ ዘመቻ የንዴቤሌ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተገድለው በማእድን ማውጫ ጉድጓዶች ውስጥ ተቀብረዋል።

ኬንያ ከእንግሊዝ ነጻነቷን ማግኘት ተከትሎ በሺዎች ሄክታር የሚቆጠር መሬት በመንግሥት እጅ ገብቶ ነበር።ፕሬዝደንት ጆሞ ኬንያታም ይሁን ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ መሬቱን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለህዝቡ ለማከፋፈል ፍላጎቱ አልነበራቸውም።

እንደውም በኬንያ እጅግ ሰፋፊና በርካታ መዋእለ ነዋዮች የፈሰሱባቸው መሬቶች የባለስልጣናት ንብረት ናቸው።

በሌላ በኩል ሙጋቤ ግን በነጭ ዚምባብዌያውያን ገበሬዎች ተይዘው የነበሩ መሬቶችን በመንጠቅ ለሀገሬው ዜጋ ለማከፋፈል ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን በዚሁ ምክንያት የእርሻ ስራዎች በመስተጓጎላቸው አገሪቱ የምግብ እጥረትና ኢኮኖሚ መላሸቅ አጋጥሟት ነበር።

ሙጋቤ ስልጣናቸውን ይዘው ለመቆየት እስከመጨረሻው ትግል ቢያደርጉም በኃይል ከስልጣናቸው ተነስተዋል። አንድ የቤተሰብ አባልም 'በጣም አዝነው' ነው ህይወታቸው ያለፈው ብሏል።

ሞይ ደግሞ ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በኋላ በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት እንዳይወዳደሩ ሲደረጉ ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸው ወስነዋል።

ሁለቱም መሪዎች የሞታቸው ዜና ከተሰማ በኋላ የተቀላቀለ ስሜት ነበር የተፈጠረው። አንዳንዶች ጀግኖች እያሉ ሲያሞካሿቸው ሌሎች ደግሞ ስልጣን የሚወዱ ጨቋኞች ነበሩ ሲሉ ተደምጠዋል።

ነገር ግን ሁለቱም መሪዎች የየአገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ሀላፊዎች በተገኙበት በተወለዱባቸው መንደሮች የቀብር ስንስርአታቸው በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል።