"በአስገድዶ መድፈር ነው የተወለድኩት'' ያለችው በ'አባቷ' ላይ የክስ ሂደት አስጀመረች

Eyes

"በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ነው የተወለድኩት'' ያለችው ሴት በተጠርጣሪው አባቷ ላይ የክስ ሂደት አስጀመረች።

በስም ያልተጠቀሰችው እንግሊዛዊት ሴት ያቀረበችውን ክስ ተከትሎ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በዋስ መለቀቁን ፖሊስ አስታውቋል።

ከሳሿ እንደምትለው ከሆነ እናቷ የ13 ዓመት ሳለቸው ዕድሜው በ30ዎቹ ውስጥ በነበረ ሰው ከተደፈረች በኋላ ነው የተረገዘችው።

የዘረ መል ምረመራ የግለሰቡን ማንነት ያረጋግጣል ስትል እየሞገተች ትገኛለች።

ጉዳዩን እየመረመረ የሚገኘው ፖሊስ የአገሪቱን አቃቢ ሕግ አገልግሎት ምክር እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

ከሳሿ ግን ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ውሎ መፈታቱም ሆነ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምክር ለመጠየቅ መወሰኑ ለጉዳዩ ትኩረት እንደተሰጠው ስለሚያሳይ ደስተኛ ነኝ ብላለች።

ትክክለኛ ስሟ ባልሆነው ቪኪ በሚል በመገናኛ ብዙሃን የምትጠራው ከሳሽ፤ የ7 ወር ጨቅላ ሳለች ነበር እአአ 1970 በማደጎ የተሰጠችው።

18 ዓመት ከሞላት በኋላ ትክክለኛ የወላጆቿን ማንነት ለማወቅ ጥረት ማድረግ ጀመረች።

ከማኅበራዊ ሠራተኞች እና በግል ዶሴዎቿ ውስጥ ያገኘችው መረጃ በአስገድዶ መድፈር መጸነሷን የሚጠቁሙ ሆነው አገኘች።

"በጣም አበሳጨኝ። ለወላጅ እናቴ እና ለእራሴ በጣም አዘንኩ" ትላለች።

ፍለጋዋን ቀጠለችና ከአንድ ዓመት በፊት ከወላጅ እናቷ ጋር መገናኘት ቻለች።

ፖሊስ የዘረ መል ምርመራ በማድረግ እና የግል መረጃዎቿን በመጠቀም በግለሰቡ ላይ የወንጀል ምረመራ ማድረግ መጀመር ይችላል ስትል ቪኪ ትከራከራለች።

ይሁን እንጂ ፖሊስ በተደጋጋሚ 'ጥቃቱ የተፈጸመው በአንቺ ላይ ስላልሆነ' በግለሰቡ ላይ ምርመራ ማድረግ እንደማይቻል በተደጋጋሚ ሲያሳውቃት እንደነበረ ትናገራለች።

"እናቴ ፍትህ እንድታገኝ እፈልጋለሁ፤ እኔ ፍትህ እፈልጋለሁ" ብላለች።